“108 ኪሎ ሜትር መንገዶችን ገንብተን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል” የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ

83

ባሕር ዳር: ሰኔ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ የ11 ወራት ዕቅድ አፈጻጸምን አስመልክቶ መግለጫ ሠጥቷል። የኤጀንሲዉ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ጌትነት ዘውዱ በበጀት ዓመቱ 8 የጠጠር መንገዶችን እና 37 ድልድዮችን በ900 ሚሊዮን ብር ለመገንባት ማቀዱን አንስተዋል።

እስከ 11 ወር ማጠናቀቂያ 108 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር መንገድ እና 5 ድልድዮች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል። አቶ ጌትነት እስከ ሰኔ 30/2015 ዓ.ም ደግሞ 2 መንገዶች እንደሚጠናቀቁም ጠቁመዋል።

ኤጀንሲው በበጀት ዓመቱ ከፌዴራል መንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት በተፈቀደለት 343 ሚሊዮን 254 ሺህ 525 ብር የጥገና በጀት 3 ሺህ 806 ነጥብ 36 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መንገድ ጥገና አከናውኗል። ኤጀንሲው ከ70 በመቶ በላይ አፈጻጸም በማሳየቱ በተደረገለት 10 በመቶ ድጎማ 389 ነጥብ 85 ኪሎ ሜትር መንገድ በ34 ሚሊዮን 325 ሺህ 452 ብር መጠገኑን ኀላፊው አንስተዋል።

በክልሉ መንግሥት በተደረገ የበጀት ድጋፍ 26 ድልድዮች እና 18 ቱቦዎች ደረጃቸውን የማሳደግ ሥራ በ73 ሚሊዮን 422 ሺህ ብር መሥራቱን አንስተዋል።

የመንገድ ግንባታው እና የጥገና ሥራው ለ1 ሺህ 440 ሴቶች እና ለ 5 ሺህ 428 ወንዶች በቋሚ፣ በጊዜያዊ እና በኮንትራት የሥራ እድል መፍጠሩንም ተናግረዋል።

በጦርነቱ ምክንያት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ዘግይተው መጀመር፣ የኮንስትራክሽን ተሽከርካሪ ማሽኖች አቅርቦት ችግር መኖር፣ የሲሚንቶ አቅርቦት ችግር፣ በሀገሪቱ ላይ የተከሰተው የዋጋ ግሽበትና የወሰን ማስከበር ሥራ አፈጻጸም ደካማ መኾን ኤጀንሲው ያጋጠሙት ችግሮች መኾናቸውን አቶ ጌትነት አንስተዋል።

ማሽኖችን በኪራይ ማስገባት፣ ፕሮጀክቱ ያለበት ወረዳ የወሰን ማስከበር ሥራውን እንዲሠራ ማድረግ ለችግሩ የተወሰዱ መፍትሔዎች ናቸው። ኤጀንሲው የወደፊት የትኩረት አቅጣጫዎችን ማስቀመጡንም የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው ጠቁመዋል።

ዘጋቢ ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሀገራችንን ነባር እሴቶች እና የሽግግር ፍትሕን በመጠቀም ዘላቂ ሰላም መገንባት ያስፈልጋል ተባለ።
Next article“ኢጋድ የሱዳን ችግር ፈች ኮሚቴ አቋቁሞ በአዲስ አበባ እንዲካሔድ አቅጣጫ ማስቀመጡ ታሪካዊ ውሳኔ ነው” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር