
ባሕር ዳር: ሰኔ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጀፓይጎ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ለአማራ ክልል ጤና ቢሮ 8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
በአማራ ክልል በነበረው የወረራ ጦርነት በርካታ የጤና ተቋማት ተዘርፈዋል፣ ወድመዋል። በጤና ተቋማት ላይ በደረሰው ጉዳት በርካቶች ለጤና ችግር ተዳርገው ቆይተዋል። የአማራ ክልል መንግሥት ከጦርነቱ ማግሥት የተዘረፉ እና የወደሙ የጤና ተቋማትን ወደ ቀደመ ይዞታቸው ለመመለስ እና አስበልጦ ለመሥራት እየሠራ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል። የጤና ተቋማቱን መልሶ ለማቋቋም ከመንግሥት ባለፈ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ በተደጋጋሚ ጥሪ ማድረጉም ይታወሳል።
ጀፓይጎ የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት ድጋፍ ያደረገው የጤና ተቋማቱን መልሶ ለማቋቋም እና የጤና ሥርዓቱን ለማሻሻል የሚደረገውን አስተዋጽኦ ለመደገፍ ነው። የጀፓይጎ ሥራ አስኪያጅ ሸዋ ግርማ የጤና አገልግሎት ወደነበረበት ለመመለስ በዩኤስአይዲ የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ድርጅቱ በአማራ፣ በአፋር እና በትግራይ ክልሎች ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል። የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል 8 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የሕክምና ድጋፍ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
ማይክሮስኮፕ፣ ማዋለጃ አልጋ፣ ጄኔሬተር፣ ፍሪጅ እና ሌሎች የሕክምና መሳሪያዎች ናቸው ድጋፍ የተደረጉት።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ በጦርነቱ በርካታ ተቋማት ተጎድተዋል ነው ያሉት። የሰው ኃይላችን ላይም የሞራል ጉዳት ደርሷል ብለዋል። በጤና ተቋማት ላይ በደረሰው ጉዳት በርካታ ወገኖች ለጉዳት ተዳርገው መቆየታቸውንም ተናግረዋል።
የጤና ተቋማቱን ወደነበሩበት ለመመለስ እና ከነበሩበት የተሻለ ለማድረግ ሳይንሳዊ ጥናት በማድረግ ጥሪ ማቅረባቸውንም አስታውሰዋል። ለተደረገላቸው ድጋፍም አመሰግነዋል። ድርጅቱ ከሕክምና ድጋፍ ባለፈ ለባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት እና ሌሎች ድጋፎች እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።
ከደረሰው ጉዳት አንፃር የተደረገው ድጋፍ በቂ አይደለም ያሉት ኃላፊው ከጀፓይጎም ሆነ ከሌሎች ተቋማት ድጋፍ እንሻለን ነው ያሉት። በተሠራው ሥራ የጤና ተቋማቱ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ገልጸዋል። በሙሉ አቅማች በበቂ ሁኔታ አገልግሎት እንዲሰጡ ድጋፎች እንደሚያስፈልጉም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!