
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ለዚህ ስኬት የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ለመላው የከተማዋ ነዎሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
የከተማዋ መሪዎች ባደረጉት ያለሰለሰ ጥረት በ71ሚሊየን 720ሺ ብር ግዥ የተፈፀመው የአስፓልት ፕላንት ማምረቻ ማሽን ግዥ ተፈፅሞ ወደ ደሴ ከተማ መግባቱ ተገልጿል።
ደሴ ከተማ የገባው የአስፓልት ፕላንት ግዥ የተፈፀመው የተሟላ ክሩ ነው፤ አስፓልት ፕላንት፣ ኖማቲክ ማሽን፣ አስፓልት ማንጠፊያ ማሽን (Asphalt Pever) ፣ አስፓልት ሮለር እና ሌሎች ለአስፓልት ሥራ የሚያስፈልጉ ማሽነሪዎችን ያካትታል።
ደሴ ከተማን ላለፉት ዓመታት በከተማዋ በአስፓልት መንገድ መሠረተ ልማት ዙሪያ ወደኋላ ካስቀሯት አንዱ የአስፓልት ፕላንት ባለመኖሩ መኾኑን ከተማ አስተዳደሩ ገልጿል።
በመሆኑም የደሴ ከተማ አስተዳደር አመራር ለከተማው ዕድገት ወሳኝ ሥራ ሠርቶ ለማለፍ ካቀዳቸው መሠረታዊ ዕቅዶች አንዱ የከተማዋን የመሠረተ ልማት ችግር ለመቅረፍ አስፓልት ፕላንት በመግዛት ለደሴ ቅርስ አስቀምጦ ማለፍ መኾኑን የከተማዋ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።
ይህ አስፓልት ፕላንት ግዥ መሳካት ጠቀሜታው ለደሴ ከተማ ብቻ ሳይሆን በቀጣናዋ ለሚገኙ ዞኖች፣ ከተሞችና ወረዳዎች ጭምር እንደሚሆን ተገልጿል። በዋናነትም በደሴ በዙሪያ ለሚገኙ ቀጣናዎች ሁሉ በዝቅተኛ ኪራይ እንዲጠቀሙ ዕድሉን ማመቻቸትና ማገዝን ታሳቢ ያደረገ ተግባር መኾኑን በማሰብ ጭምር የተሠራ ሥራ ነው ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!