“በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞንና ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አዋሳኝ አካባቢዎች የሚከሰቱ አለመረጋጋቶችን በመቅረፍ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እየሠራን ነው” የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ

96

ደሴ: ሰኔ 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በአጣየ ከተማ የሰላም ኮንፈረንስ አካሂዷል። በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞንና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አዋሳኝ አካባቢዎች የሚስተዋሉ አለመረጋጋቶችን በማስቀረት ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሚያስችል ሥራ እያከናወነ መኾኑን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ገልጿል።

ቢሮው ከመከላከያ ሠራዊት፣ከክልሉ ጸጥታ መዋቅር፣ከአካባቢው የሃይማኖት አባቶችና የሐገር ሽማግሌዎች ጋር ባካሄደው የሰላም ኮንፈረንስ ችግሩን ለመቅረፍ ያስችላሉ ያላቸውን የመፍትሔ አቅጣጫዎችም አስቀምጧል። በአካባቢው ሰላም ባለመስፈኑ ሕዝቡ ለከፋ ችግር ሲጋለጥ መቆየቱን የገለጹት የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮማንደር መንገሻ አውራሪስ በሕዝቡ ውስጥ ተሰግስገው በስሙ የሚነግዱ ጸረ ሰላም ኃይሎችን ሴራ በማክሸፍ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን ያለመ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።

የክልሉ መንግሥት ለአካባቢው ብሎም ለክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል። የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ በሰሜን ሸዋ ዞንና ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አዋሳኝ አካባቢዎች የሚያጋጥሙ ግጭቶችን ለማስቆም የሚያደርገውን ጥረት እናግዛለን ያሉት የሰሜን ሸዋ ዞንና የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰላምና ጸጥታ መምሪያዎች የግጭት መከላከል ሥራ ቡድን መሪዎች በሁለቱም አካባቢዎች ወንጀል ፈጽመው የተሰወሩ አካላትን ለጸጥታ ኃይሉ አሳልፎ በመስጠት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ነው የተናገሩት።

ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ እንሠራለን ብለዋል። ኀብረተሰቡን በማሳተፍ የአካባቢዉን ሰላም እና ጸጥታ አስተማማኝ ብሎም ዘላቂ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል ኮማንደር መንገሻ።የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊው እንዳሉት በተለያዩ ወንጀሎች ላይ የተሳተፉ አካላትን ተከታትሎ በቁጥጥር ስር ለማዋል፣ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም፣ በእርሻና ግጦሽ ምክንያት የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለማስቀረት ከሁለቱም አዋሳኝ አካባቢዎች የጋራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ መገባቱንም ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥት የአካባቢዉን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ እየሠራ ያለውን ሥራ ሕዝቡ እንድያግዝም ኮማንደር መንገሻ ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ:- አሊ ይመር

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ እና የሩሲያ ኢምባሲ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ።
Next articleባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዕውቅና ሰጠ።