
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቁልፍ እሴት ከሆኑት ቀዳሚውና ዋናው ከራስ በፊት ለሕዝብና ለሀገር ጥቅም መቆም መሆኑን የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ዩ ኤስ ኤ አይ ዲ (USAID) ሰሞኑን አጣርቻለሁ ብሎ ባወጣው መግለጫ ለሰብአዊ እርዳታ የመጣን እህል ከሌሎች መንግስታዊ አካላት ጋር በመሆን መከላከያ ሰራዊታችንም እንደተጠቀመ አድርጎ ያቀረበውን ሪፖርት የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መዘገባቸውን ዛሬ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በጥብቅ ድስፕሊን የሚመራ ዘመናዊ ሰራዊት ነው ያለው መግለጫው፥ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚደረግላቸውን ወገኖቹን ቀለብ ሊቀማ ቀርቶ፤ ከቀለቡ ቀንሶ የሚያካፍል ሠራዊት መሆኑን አስታውቋል።
የሃገሩ ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ በአጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሰላም ማስከበር በተሰማራባቸው ቦታዎች ሁሉ የዕለት ከዕለት ተግባሩ መሆኑን የደረሰላቸው ሕዝቦች፤ መንግስታት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሁሉ የሚያውቁት ሰመ ጥር ሕዝባዊ ሠራዊት ነው ብሏል።
ኢትዮጵያ ለሠራዊቷ ደመወዝና ቀለብ መስጠት ከጀመሩት ሀገራት መካከል በቀዳሚነት የምትሰለፍ ነፃ እና ታሪካዊት ሀገር መሆኗን አመልክቷል።
የችግረኞችን ስንዴ የማይሻማ ፕሮፌሽናል እና ኩሩ ሠራዊት አለን ያለው መግለጫው፥ የእርዳታ ስንዴ የሚጠቀም ተቋም ወይም ዩኒት ወይም ወታደር የለንም ሲል አረጋግጧል።
ዩኤስኤአይዲ በሠጠው መግለጫ መሠረት ምናልባት የመከላከያ አባል የሆነ ወታደር በማይመለከተው ገብቶ ከመዋቅር ውጪ ሕግ የማስከበር ሥራውን ተጠቅሞ ከሌቦች ጋር በመተባበር እርዳታ ተሰርቆ እንዲወጣ በግል የተባበረ ካለ እና ተጣርቶ ከተገኘ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አመራር የማያዳግም እርምጃ ይወስዳል ብሏል።
መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል፦
የኢፌዴሪ መከላከያ ሰኔ 03 ቀን 2015 ዓ.ም
ከኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር የተሰጠ መግለጫ
ሰኔ 03/2015 ዓ.ም
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቁልፍ እሴት ከሆኑት ቀዳሚውና ዋናው ከራስ በፊት ለህዝብና ለሀገር ጥቅም መቆም ነው፡፡
ዩኤስኤአይዲ (USAID) ሰሞኑን አጣርቻለሁ ብሎ ባወጣው መግለጫ ለሰብአዊ እርዳታ የመጣን እህል ከሌሎች መንግስታዊ አካላት ጋር በመሆን መከላከያ ሰራዊታችንም እንደተጠቀመ አድርጎ ያቀረበውን ሪፖርት የተለያዩ ሚዲያዎች ሲዘግቡት አስተውለናል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በጥብቅ ድስፕሊን የሚመራ ዘመናዊ ሰራዊት ነው፡፡ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚደረግላቸውን ወገኖቹን ቀለብ ሊቀማ ቀርቶ፤ ከቀለቡ ቀንሶ የሚያካፍል ሠራዊት መሆኑን የሀገሩ ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ በአጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሰላም ማስከበር በተሰማራባቸው ቦታዎች ሁሉ የዕለት ከዕለት ተግባሩ መሆኑን የደረሰላቸው ሕዝቦች፤ መንግስታት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሁሉ የሚያውቁት ሰመ ጥር ሕዝባዊ ሠራዊት ነው፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ለሠራዊቷ ደመወዝና ቀለብ መስጠት ከጀመረች፤ ቀዳሚ ነን ከሚሉ ሀገራት ተርታ የምትሰለፍ ነፃ እና ታሪካዊት ሃገር ናት፡፡
ሠራዊታችን ዘመናዊ ነው ከሚያስብሉት አንዱ ደግሞ ይኸው ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የሎጅስቲክ ግዥ እና አቅርቦት ጉዳይ ነው፡፡
የሠራዊታችን ቀለብ ለሀገር ውስጥ ነጋዴዎች እድሉን በመስጠት በግልፅ ጨረታ ተወዳድረው ስንዴም ሆነ ሌሎች ምግብ ነክ ፍጆታዎች የሚቀርብለት በተሟላ አሰራር እና አመራር የሚመራ ሰራዊት ነው፡፡
የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት፡-
1ኛ/ ሠራዊታችን በቂ ሎጄስቲክ ያለው በዓለም አቀፍና በአገር ውስጥ ለተፈናቀሉትና በድርቅ ለተጎዱት በዓይነትና በገንዘብ የሚረዳ እንጂ ተቸግሮ ከአሠራር ውጭ የሚጠቀም አይደለም።
2ኛ/ ሠራዊታችን ማንኛውንም ዓይነት ምግብ በበጄቱ በሕግና በግልፅ ጫረታ ገዝቶ የሚጠቀም እንጂ ተቸግሮ የሕዝብ እርዳታ አካባቢ ሄዶ እርዳታ ላይ የሚሻኮትበት ዓይነት ድህነት የለበትም። ጥቆማ የሰጠ አካል እንኳ ቢኖር እስኪጣራ ሳይጠበቅ፤ እንደ ተቋምና እንደ ሠራዊት ስም የሚያጠፋ የሚዲያ ሽፋን መስጠት የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት ክብር ይነካል።
3ኛ/ ምንም እንኳ አገራችን በሚሊዮን የሚቆጠር እርዳታ ጠባቂ ሕዝብ ቢኖራትም ሠራዊቷን መመገብ የምትችልና በቂ ምግብና በጄት በመመደብ ሠራዊቱ ራሱ በሕግና በተቋም ሎጄስትክ አማካኝነት የምትመግብ አገር ናት። ሠራዊታችንም ኩሩና የችግረኞችን ስንዴ የማይሻማ ፕሮፌሽናል ሠራዊት ነው። ስለሆነም የእርዳታ ስንዴ የሚጠቀም ተቋም ወይም ዩኒት ወይም ወታደር የለንም።
4ኛ/ ዩኤስኤአይዲ (USAID) በሠጠው መግለጫ መሠረት ምናልባት የመከላከያ አባል የሆነ ወታደር በማይመለከተው ገብቶ ከመዋቅር ውጪ ሕግ የማስከበር ሥራውን ተጠቅሞ ከሌቦች ጋር በመተባበር እርዳታ ተሰርቆ እንዲወጣ በግል የተባበረ ካለ እና ተጣርቶ ከተገኘ የአገር መከላከያ ሠራዊት አመራር የማያዳግም እርምጃ ይወስዳል።
መከላከያ ሰራዊት ለሀገሩም ሆነ ለዓለም አቀፍ ሰላም መከበር መሰዋትነት የሚከፍል ምስጉን ሰራዊት ሆኖ እያለ፤ በሀገራችን ውስጥና በውጪ አገር ያሉ ጥቂት የአገር መከላከያ ሠራዊት ጥላቻ ያላችው ፅንፈኞች እንዳሉ እናውቃለን። መካላከያን የማጠልሸት ሥራ የቆየና የለመድነው ነው።
የመከላከያ ሠራዊታችንን ሕዝባዊ ተፈጥሮ፣ አሰራርና ሥርዓት ሳይታወቅና መረጃ እንኳ ቢመጣ፤ አጣርቶ ሳይታወቅ፤ መረጃ የቀረበበት አካል ሳይጠየቅ፤ የሚዲያ ሽፋን መሰጠት ትክክል አይደለም ብለን እናምናለን። የሚመለከታቸው የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶችና የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲያጣሩ እንተባበራለን። ከተጣራ በኋላ ሁሉንም ለሕዝብ ይፋ እናደርጋለን።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!