
ባሕር ዳር: ሰኔ 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን ባለፉት ሁለት ዓመታት የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ባደረገው ድጋፍ በፎገራ ወረዳ በሁለት ቀበሌዎች በሩዝ ማሳ ላይ ዓሣ የማራባት ሥራ ተሠርቷል፡፡
በሁለት ቀበሌዎችና በስምንት አርሶአደሮች የተጀመረው ሥራ አሁን ላይ በሦስት ወረዳዎች በስምንት ቀበሌዎች ላይ ተግባራዊ ተደርጎ ውጤት ተገኝቶበታል።
አርሶአደር ማሩ አለምነው በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ የቋራ አቦ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በተደረገላቸው ድጋፍ በሩዝ ማሳቸው ላይ ዓሣ እያራቡ ሲጠቀሙ ቆይተዋል፡፡ አርሶ አደር ማሩ በ625 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እስከ ሁለት ሺህ የሚደርሱ የዓሣ ጫጩቶችን በማራባት ነበር ተጠቃሚ መኾን የቻሉት፡፡ አርሶ አደሩ ያደጉትን አሳዎች ከ22 ሺህ ብር በላይ በመሸጥም ገቢያቸውን አሳድገዋል፡፡ የዓሣ ጫጩቶችን ለሌሎች አርሶአደሮች በመሸጥ ተጠቃሚም አድርገዋል።
አርሶ አደሩ የአሳ ጫጩቶቹ ዘርፈብዙ ጠቀሜታ እንዳላቸው ገልጸው በተለይ አሳዎቹ አረሙን እየበሉ ስለሚያድጉ አረም ከአንድ ጊዜ በላይ እንዳላረሙ ነው የነገሩን፡፡ ያገኙትም ምርት ከዚህ በፊት ከነበረው በ10 ኪሎ ግራም ብልጫ እንደነበረው ነው ያስረዱት፡፡ በዚህ ክረምትም ሥራውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነግረውናል፡
አርሶ አደር አስራት ታከለ የፎገራ ወረዳ ቴዋዛቀና ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ለሁለት ዓመት ያክል የዓሣ ጫጩት በማራባት ሥራው ላይ ቆይተዋል። ገቢያቸውም ከዓመት ዓመት ጨምሯል። የሚያስገቡት የዓሣ ጫጩት ብዛት ከ1 ሺህ 600 ወደ 2 ሺህ አድጓል። ከ14 ሺህ ብር በላይም በሽያጭ አግኝተዋል። ቤተሰቦቻቸው በሳምንት ሦስት ጊዜ ዓሣ ይመገባሉ። የሩዝ ምርታቸውም ከመደበኛው ጋር ሲወዳደር በ20 ኪሎ ግራም ብልጫ ማሳየቱን ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
የፎገራ ወረዳ እንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት የዓሳ ሀብት ልማት አሥተዳደር ባለሙያ ሳለሁ ባዬ ሥራው በሁለት ቀበሌዎች በስምንት አርሶ አደሮች ማሣ ተሞክሮ ውጤት አምጥቷል ብለዋል። ባለፈው ዓመት 19 አርሶ አደሮች በሥራው ላይ ተሠማርተው እያንዳንዳቸው ከ14 ሺህ እስከ 22 ሺህ ብር የሚደርስ ገቢ አግኝተዋል ነው ያሉት።
አርሶ አደሮች ስለ ሥራው ሥልጠና እንዳገኙ የተናገሩት ባለሙያው ሥራው ጥብቅ ቁጥጥር የሚፈልግ በመኾኑ በቀጣይ ለሚሠራው ሥራ አጋዥ እንደኾነ ነው ያብራሩት። በሂደት የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታትም ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። ከዓሳ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ እንደሰዎች ክትትል የሚወሰን እንደኾነም ተናግረዋል፡፡
ሥራው ዓመቱን ሙሉ እንዲሠራ የውኃ አቅርቦቱን ችግር ለመቅረፍ በወረዳው ውስጥ ያሉ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች በፀሐይ ኀይል የሚሠራ የውኃ ጉድጓድ እንዲቆፈር እገዛ እንዲያደርጉ እየተነጋገሩ ስለመኾኑም ነው ያብራሩት።
በአማራ ክልል የእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት የእንስሳት እርባታ ተዋጽኦ እና መኖ ልማት ዳይሬክተር መኳንንት ዳምጤ በዚህ ዓመት 21 አርሶ አደሮችን በሥራው ለማሳተፍ መታቀዱን ነግረውናል።
ለአርሶ አደሮች በማሣ ላይ የተግባር ሥልጠና እየተሠጠም እንደኾነ ገልጸዋል። አስተማማኝ ውኃ የሚያገኙ አርሶ አደሮች ወደ ሥራው እየገቡ ቢኾንም ሌሎች አርሶ አደሮችም ወደ ሥራው እንዲገቡ እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል። በጣና ዙሪያ የሚገኙ ሁሉንም ወረዳዎች ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ ስለመኾኑም ነው ያስገነዘቡት።
ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!