
ባሕር ዳር : ግንቦት 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የራስ ገዝ አስተዳደርነቱን ወደ ተግባር ለመቀየርና ውጤታማ ለማድረግ አሰራሩን እያዘመነ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ገለጹ። ዩኒቨርሲቲው የሚያሰራቸው የምርምር ውጤቶች ተጠቃሽነታቸው እያደገ መምጣቱን አመልክተዋል።
ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ዩኒቨርሲቲው የሚያከናውቸው የጥናትና ምርምር ውጤቶች ካለፉት አምስት ዓመታት ጀምሮ በጥራትና በብዛት በሶስት እጥፍ ጨምሯል። ለውጤታማነቱ የቴከኖሎጂ አጠቃቀምና የኢንተርኔት ተደራሽነት ማደጉ ዋነኛው ምክንያት ነው ያሉት ፕሮፌሰር ጣሰው፤ የክፍያ ሥርዓቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ኦንላይን ሥርዓት አስገብቷልም ብለዋል።
አንድ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የአስተማሪ ተማሪ ግንኙነትን በማቀናጀት ማስተማር፣ ምርምሮች ለትምህርት፣ ለኢንዱስትሪው የሚያገለግሉና የሀገርን ችግር የሚፈቱ ለማድረግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን
መጠቀም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ያሉት ፕሮፌሰር ጣሰው፤ቀድሞ የነበረው አሰራር አንድ መምህር ምርምር ለማድረግ ተዛማጅ ጽሁፍ ለማግኘት በማንዋል የተዘጋጁ ጽሁፎችን ይፈልግ ነበር።
አሁን ላይ ግን ባለው ኢንተርኔት ተደራሽነትና ፍጥነት የተነሳ ማንኛውንም መጽሃፍ፣ ጆርናልና ሌሎች መረጃዎችን በኢንተርኔት አማካኝነት በቀላሉ ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ የኢንተርኔት ተደራሽነት መጨመር ለዩኒቨርሲቲው ዕድገት ወሳኝ ነው። የዩኒቨርሲቲው 80 በመቶ የሚሆነው ውጤት የኢንተርኔት ተደራሽነት ጋር የተያያዘ ነው። ዩኒቨርሲቲው ከምሥራቅ አፍሪካ አንደኛ፤ በአፍሪካ 6ኛ ደረጃን ይዞ ይገኛል። ይህ የሆነው በሚያደርጋቸው ምርምሮች፣ በሚሰጠው የትምህርት መርኃ ግብርና መሰል ተግባሮቹ ነው።
ምርምሮች ተሰርተው ለሪፖርት ብቻ የሚቀርቡ ካልሆኑና በሶስተኛ አካል ተረጋግጠው ለችግሮች መፍቻ ካልሆኑ ዋጋ የላቸውም። ምርምሮች በከፍተኛ ወጪ እንደመሰራታቸው መጠን ችግር ፈቺ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ላለፉት ስድስት ዓመታት ማንኛውም ምርምር ውጤት በዓለም አቀፍ ደረጃ በታወቁ ጆርናሎች ወጥተው ፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ ተመራማሪዎች እንዲጠቅሱት ታትመው እየወጡ ነው። በየዓመቱ 400 ምርምሮች የሚታተሙ ሲሆን አሁን ላይ ቁጥራቸው ሶስት ሺ 144 ደርሷል ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ውጤት የሚለካው በሌሎች ተመራማሪዎች ምን ያህል ይጠቀሳል በሚል ሲሆን የሚሰሩ ምርምሮች ተጠቃሽነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። ለምሳሌ ካይሮ ዩኒቨርሲቲ በህትመት ብዛት 5 እጥፍ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይበልጣል። ነገር ግን በተጠቃሽነት አዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ እንደሚልቅ አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲው የራስ ገዝ መሆኑ በቅርቡ ይታወጃል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ይህን በተግባር ለተመርጎም እየተሰራ ነው። ያገኘውን የአካዳሚክስ ነጻነት ወደ ተግባር እንዲቀየር አሰራሩን ማዘመን ያስፈልጋል። አሰራሩ ካልዘመነ ውጤት አይመጣም ነው።
የዩኒቨርሲቲው ዋና ዓላማና ግብ ተማሪዎችን የተግባርና የንድፈ ሀሳብ ትምርት በማስያዝና ሙሉ ሰብዕና በማላበስ አስመርቆ የመቀጠር ምጣኔያቸው እንዲያድግ ማስቻል መሆኑን የጠቀሱት ፕሮፌሰር ጣሰው፤ በተጨማሪም ምርምሮች የበለጠ የኢንዱስትሪውን ችግር፣ የፖሊሲ አውጪዎችን እንደ ግብዓት የሚያገለግሉና የበለጠ ተጠቃሽ የሆኑ የምርምር ውጤቶችን ማውጣት መሆኑንም ተናግረዋል። የዘገበው ኢፕድ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!