
ባሕር ዳር : ግንቦት 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሁለተኛ ደረጃ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ያላቸው አርሶ አደሮች መሬታቸውን እንደዋስትና በመጠቀም የብድር አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ የሕግ ማዕቀፍ ወጥቶለት ወደ ሥራ ተገብቷል። ይሁን እንጅ አብዛኛዎቹ አበዳሪ ተቋማት መሬትን እንደዋስትና ተጠቅመው የብድር አገልግሎት እየሰጡ አይደለም ተብሏል። ጸደይ ባንክ እና አንዳንድ አነስተኛ የብድር ተቋማት ብድር እየሰጡ ቢኾንም ከ50 ሺህ ብር የማይበልጥ በመኾኑ አርሶ አደሮች የሚፈለገውን ያህል ተጠቃሚ መኾን ሳይችሉ ቆይተዋል ተብሏል። ይህንን ችግር ለመፍታት የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ከግብርና ሚኒስቴር የገጠር መሬት አሥተዳደርና አጠቃቀም መሪ ሥራ አሥፈጻሚ ጋር በመቀናጀት ከሚመለከታቸው የፋይናንስ ተቋማትን ያካተተ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ ለክልሉ አርሶ አደሮች ሁለተኛ ደረጃ የመሬት ይዞታ ባለቤትነት የምስክር ወረቀት የመስጠት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መኾኑን ገልጸዋል። ይህ የምስክር ወረቀት በመሬት ይገባኛል ሰበብ በአርሶ አደሮች መካከል ይፈጠር የነበረውን ችግር የቀረፈ ከመኾኑም በላይ በመሬታቸው የመጠቀም መብታቸውን ያረጋገጠ ነው ብለዋል። ይሁን እንጅ የፋይናንስ ተቋማት የአርሶ አደሮችን የይዞታ ማረጋገጫ በዋስትናነት በመጠቀም ተገቢውን የብድር አገልግሎት መስጠት ላይ ክፍተቶች አሉ ነው ያሉት። “አርሶ አደርን መደገፍ ሀገርን መደገፍ ነው” ያሉት ቢሮ ኀላፊው የፋይናንስ ተቋማት ለአርሶ አደሮች ተገቢውን ብድር ማቅረብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የመሬት ይዞታ ማረጋገጫቸውን በመጠቀም የብድር አገልግሎት ያገኙ አርሶ አደሮች ቁጥር እስካሁ ድረስ 15 ሺህ ብቻ እንደኾነም አቶ ሲሳይ ገልጸዋል። ይህም አብዛኛው ቁጥር በጸደይ ባንክ በኩል የተሰጠ እንጅ ሌሎች ባንኮች ግን ወደ አሠራሩ አልገቡበትም ብለዋል። በቀጣይ በአማራ ክልል ከ6 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች የመሬት ማረጋገጫ ሰርተፊኬታቸውን በመያዝ የባንክ ብድር ተጠቃሚ እንዲኾኑ እየተሠራ ስለመኾኑም ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል።
የግብርና ሚኒስቴር የገጠር መሬት አሥተዳደርና አጠቃቀም መሪ ሥራ አሥፈጻሚ ትዕግስቱ ገብረመስቀል የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት መሰጠቱ ከመሬት አጠቃቀም ጋር የተያያዙ የመልካም አሥተዳደር እጦቶችን ለመፍታት አግዟል ብለዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ50 ሚሊዮን በላይ ቁርጥራጭ መሬቶች አሉ። ከዚህ ውስጥ 28 ሚሊዮኑ የመሬት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ተሰጥቷቸዋል ነው ያሉት።
የፋይናንስ ተቋማት የአርሶ አደሮችን የመሬት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት በዋስትናነት በመጠቀም ትልቁ ቆጣቢያቸው ለኾነው አርሶ አደር ተገቢውን ብድር ማቅረብ እንዳለባቸውም ተናግረዋል። ይህ ሲኾን ግብርና ሚኒስቴር ስለአርሶ አደሮች የመሬት ይዞታ አስፈላጊውን ሁሉ መረጃ ለባንኮች በማቅረብ በኩል በትብብር እንደሚሠራም ገልጸዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ ከነበሩት የፋይናንስ ተቋማት መካከል የጸደይ ባንክ ሪጅናል ዳይሬክተር ይርጋ ጌትነት ባንኩ የአርሶ አደሮችን መሬት በዋስትና በመያዝ ብድር የመስጠት ሥራውን ቀደም ብሎ እንደጀመረ ተናግረዋል። 14 ሺህ በላይ የሚኾኑ አርሶ አደሮች ሁለተኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀታቸውን በዋስትና በመጠቀም ከ540 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር መውሰዳቸውን ገልጸዋል። ለአርሶ አደሮች ከተሰጠው ብድር ውስጥ ሁሉም መመለሱንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ለአንድ አርሶ አደር ሲሰጥ የነበረው ከፍተኛ የብድር መጠን 50 ሺህ ብር እንደነበር ጠቅሰው አሁን ላይ ወደ 100 ሺህ ብር ከፍ ማለቱን ጠቁመዋል።
ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ የሀርቡ ማይክሮ ፋይናንስ አክሲዮን ማኅበር የአማራ ክልል ተወካይ አሥተባባሪ ስመኘው ውበት ማንኛውም አርሶ አደር ሁለተኛ ደረጃ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት አስይዞ መበደር እንደሚችል በመገንዘብ አገልግሎቱን እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል። በዚህም መሰረት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ለአርሶ አደሮች ተሰጥቷልም ብለዋል። ከፍተኛው የብድር መጠን 40 ሺህ ብር መኾኑን ገልጸው የተቋሙ አቅም ሲያድግ የማበደር አቅሙም ከፍ እንደሚል ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!