
ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 21ኛ መደበኛ ስብሰባ የ2016 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ የበጀት አዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡
የፌዴራል መንግሥት የ2016 በጀት በአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ የተቀመጡ ግቦችን ታሳቢ በማድረግ፣ የሀገር ደህንነት ከማስጠበቅ፣ በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጐችን ከመርዳት፣ በሕግ ማስከበር ዘመቻው የወደሙ መሰረተ ልማቶች መልሶ ከማቋቋም፣ በቀጣይ ሊኖር የሚችለውን የማህበራዊና የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን አቅጣጫዎችና ዓላማዎች ከማሳካት አኳያ የተቃኘ ሲሆን የ2016_2020 የመካከለኛ ዘመን የማክሮ ኢኮኖሚ እና የፊሲካል ማዕቀፍን መሠረት በማድረግ ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው፡፡
በዚሁ መሰረትም ለፌደራል መንግሥት መደበኛ ወጪዎች ብር 369.6 ቢሊየን፣ ለካፒታል ወጪዎች ብር 203.9 ቢሊየን፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ ብር 214.07 ቢሊየን፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ ብር 14 ቢሊየን በጠቅላላው ብር 801.65 ቢሊየን ሆኖ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በቀረበው የፌዴራል መንግሥት የ2016 በጀት ረቂቅ አዋጅ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!