አርሶ አደሮች በሕገወጥ የግብርና ግብዓት አቅራቢዎች እንዳይታለሉ ግብርና ቢሮ አሳሰበ፡፡

125

ባሕር ዳር : ግንቦት 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት ችግር ሰሞነኛ አጀንዳ ኾኖ ሰንብቷል። የክልሉ ግብርና ቢሮ በበኩሉ ያጋጠመው የአፈር ማዳበሪያ የአቅርቦት ችግር በገጠመው ሀገራዊ ጉዳይ ግዥ የተፈጸመበት የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ወደ ክልሉ አለመግባት እና የገባውም በአግባቡ አለመሰራጨት እንደኾነ እየገለጸ ነው።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻው ለአሚኮ እንደተናገሩት የአቅርቦት ችግሩን ለመፍታት ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል። የስርጭት ችግሩን ተጠቅመው በሕገወጥ መንገድ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮቹ በመሸጥ ላይ ያሉ አካላት እንዳሉም ደርሰንባቸዋል ነው ያሉት አቶ አጀበ።

እነዚህ አካላት በሕገወጥ መንገድ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች መሸጣቸው ብቻም ሳይኾን የማይጠቅም የአፈር ማዳበሪያ እያሰራጩ መኾናቸውም አሳሳቢ እንደኾነ ነው ያስረዱት።

እንደማሳያም ለአማራ ክልል ጥቅም ላይ የማይውለው ፖታሽ ማዳበሪያ በሕገወጦች እየተሸጠ ከአርሶ አደሮች እጅ ገብቶ ተገኝቷል ነው ያሉት።

በተደረገው ክትትል ዩሪያ፣ኤን ፒ ኤስ እና ሌላም ምንነቱ ያልታወቀ ዱቄት መሰል በዓድ ነገር የተቀላቀለበት በአንድ ታሽጎ ተገኝቷል ነው ያሉት።

ትክክለኛውን የአፈር ማዳበሪያ የያዙትም በተጋነነ ዋጋ እየሸጡ አርሶ አደሮችን ላልተፈለገ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እየዳረጉ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

በሕገወጦች በሚቀርበው የአፈር ማዳበሪያ አርሶአደሮች ከሚደርስባቸው ኢኮኖሚያዊ ኪሳራም ባሻገር የእርሻ ማሳቸውን በዘላቂነት ለሚጎዳ በዓድ ነገር ጭምር ተጋላጭ እንዳይኾኑ መጠንቀቅ አለባቸው ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኀላፊው።

መንግሥት የአቅርቦት ችግሩን እየፈታ ሕገወጦችንም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ፣በሕግም እንዲጠየቁ እየሠራ ነው ብለዋል አቶ አጀበ። አርሶ አደሩም ሕገወጦችን መታገል እንዳለበት አሳስበዋል። ሕገወጦችን በማጋለጥና ለሕግ እንዲቀርቡ በማድረግ ጥቅምና መብታቸውን እንዲያረጋግጡም ጠይቀዋል።

በየሰፈራቸው “መሬት አለኝ ፣አርሳላሁ ፣እዘራለሁ” እያሉ ምንም ሳይኖራቸው በሕጋዊ መንገድ የወሰዱትን የአፈር ማዳበሪያ ለሽያጭ ገበያ ላይ ሲያውሉ ከመግዛት ይልቅ ማጋለጥን መምረጥ አለባቸው ነው ያሉት።

በተያያዘም በአማራ ክልል የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር እንደሌለ ነው የክልሉ ግብርና ቢሮ ያስታወቀው።

ምክትል ቢሮ ኀላፊው አጀበ ስንሻው እንደሚሉት በክልሉ ውስጥ ዋና ዋና ምርጥ ዘሮች፣ የበቆሎ የጤፍና የስንዴ ምርጥ ዘር በከፍተኛ ደረጃ የሚመረት ነው።

ለዘንድሮው የመኸር ምርት ዘመን 350 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለማቅረብ ታቅዶ አስከ አሁንም 214ሺህ ኩንታል በላይ መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።

በአርሶ አደሮች ዘንድ እየቀረበ ያለው የበቆሎ ምርጥ ዘር አቅርቦት ቅሬታና ጥያቄ የዘር ዓይነት ምርጫ ጉዳይ ነው ብለዋል። በበቆሎ ምርጥ ዘር የሊሙ፣ የሾኔ፣ የዳሞት ምርጥ ዘር አቅርቦት ላይ ውስንነት ቢኖርም ይህን የሚተካ ቢ. ኤች.546፣ ቢ.ኤች.661 የተባሉ በቂ የበቆሎ ምርጥ ዘሮችን አቅርበናል ሲሉ ተናግረዋል።
እናም ለምርት ዘመኑ የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር እንደሌለ ነው ያስታወቁት።

ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በማይካድራ እና በሁመራ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።
Next article“አማራ ነን እንጅ አማራ እንሁን አላልንም” የዳንሻ ከተማ ነዋሪዎች