የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በውሕድ ፓርቲው እንደሚመለሱ የአዴፓ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ገለጹ፡፡

260

ውሕደቱን አስመልክቶ ከአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ጋር ቆይታ ያደረጉ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) የአስቸኳይ ጉባዔ ተሳታፊዎች ለረጅም ጊዜ ትግል ሲደረግበት የነበረው የውሕደቱ ጉዳይ በሙሉ ድምጽ መጽደቁ ጥሩ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አባል ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የአዴፓ መተዳደሪያ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት አስቸኳይ ጉባዔ መጠራቱን እና በፓርቲው የውሕደት ሐሳብ ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን ተናግረዋል፡፡ በተለይ ከዚህ ቀደም በሀገራቸው ዕጣ ፈንታ ላይ በቀጥታ የመወሰን እድል ተነፍጓቸው የነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ወደ ባለቤትነት የሚያስጠጋ መሆኑን ወይዘሮ ዳግማዊት ተናግረዋል፡፡ ውሕደቱ አሐዳዊነትን ለመመመለስና ግለሰቦችን ለማንገሥ እንደሆነ የሚናገሩ አካላት መኖራቸውን በማመላከት ውሕደቱ አካታችና በሕግና ሥርዓት የሚመራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

አደረጃጀቱ የራሱ ማዕከላዊ እና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያለው መሆኑንና እነዚህ ኮሚቴዎች እንደየሥራ ድርሻቸው በሚወስኑት አግባብ አሠራሩ ተግባራዊ ስለሚደረግ ግለሰቦች ብቻቸውን የሚወስኑበት ሁኔታ እንደማይኖር አስታውቀዋል፡፡ ይልቁንም ብልጽግና ፓርቲ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች አካታች በመሆኑ የጠቅላይነትን አስተሳሰብ እና አካሄድ እንደሚያስቀር ተናግረዋል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ የቡድን እና የግለሰብ መብትን ሚዛናዊ አድርጎ የሚያስጠብቅ ስለመሆኑም በማብራሪያቸው አመላክተዋል፡፡ አዲሱ ውሕድ ፓርቲ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና በውጭ ግንኙነት ፖሊሲዎች ላይ ያለውን አውንታዊ እሳቤም አስገንዝበዋል፡፡

አብዮታዊ ዴሞክራሲ አሁን ላለው ተራማጅ የፖለቲካ ምኅዳር የሚመጥን ባለመሆኑ ሀገራዊ አስተሳሰቦችን ማራመድ የሚያስችል ርዕዮተ ዓለም እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በማዕከላዊ ኮሚቴ እና በሥራ አስፈጻሚ ደረጃ በተደጋጋሚ ሲነሱ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡ ቀጣይም የትግል አጀንዳ እንደሚሆኑ ነው የገለጹት፡፡

ዶክተር አህመዲን ሙሐመድ ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ ዓላማው የበለጸገች ኢትዮጵያን መፍጠር መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ ለዚህም ኅብረ ብሔራዊነት፣ ለዜጎች ክብር መስጠት እና ነጻነትን መሠረት ያደረገ አሰራር ለመፍጠር ምቹ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ ውሕድ ፓርቲው መላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

“መጤ ርዕዮተ ዓለም ለኢትዮጵያ አይጠቅምም” ያሉት ዶክተር አህመዲን ሀገር በቀል ችግሮችን በሀገር በቀል ሀገራዊ አስተሳሰብ ምላሽ ለመስጠት አብዮታዊ ዴሞክራሲን መቀየር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ከአብታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ጠቃሚ የሆነውን መውሰድ ተገቢነት እንደሚኖረውም አስገንዝበዋል፡፡

የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባሉ ዶክተር ስንታየሁ ወልደሚካኤል ደግሞ ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ ከዘመኑ ጋር አብሮ የማይሄድ ኅብረተሰቡን በመደብ ከፋፍሎ የሚሠራ በመሆኑ ይህንን አስተሳሰብ በመሠረታዊነት መቀየር አስፈላጊ ነው›› ብለዋል፡፡

‹ከኅብረ ብሔራዊነት ወደ አሐዳዊነት ለመመለስ የሚደረግ ጥድፊያ ነው› ለሚሉ አካላትም ዶክተር ስንታየሁ በሰጡት ማብራሪያ ብልጽግና ፓርቲ ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ የተመሠረተ በመሆኑ አሐዳዊነትን ሊያስከትል የሚችልበት ምንም ዓይነት እድል የለውም ብለዋል፡፡ ሌሎች ሀገራትም የዚህን ዓይነት አደረጃጀት ተጠቅመው ውጤታማ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡

ደክተር ተስፋ እንዳሉት ደግሞ በግንባር አደረጃጀት የፌዴራል ስርዓትን ተግባራዊ ማድረግ በራሱ ስህተት ነው፡፡ የግንባር አደረጃጀት ፈጥረው የፌደራል ስርዓትን በስኬት የተገበሩ ሀገራት አለመኖራቸውንም ነው ዶክተር ተስፋ የተናገሩት፡፡ ብልጽግና ፓርቲ በፌደራል አደረጃጀቱ እንደሚዋቀር እና እውነተኛ ፌዴራሊዝምን ተግባራዊ ለማድረግ ምቹ አደረጃጀት መሆኑንም በማብራሪያቸው አካትተዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች በአስቸኳይ ጉባዔው ትኩረት ተሰጥቷቸው ውይይት በማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል፡፡ በ12ኛው የአዴፓ ድርጅታዊ ጉባዔ ጎልተው የወጡ የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች በውሕድ ፓርቲው በትኩረት የሚሠራባቸው መሆኑን ነው በ12ኛው የአዴፓ ድርጅታዊ ጉባዔ ተሳታፊ የነበሩት ዶክተር ደስታ ተስፋው ማብራሪያ የሰጡት፡፡

ውሕደቱ ፓርቲ መሠረታዊ ጥያቄዎቹ ምላሽ እንዲያገኙ ምቹ በመሆኑ ብልጽግና ፓርቲ በፕሮግራሙ እና በአደረጃጀቱ አካትቶ ከሌሎች አካላት ጋር በጋራ በመሆን የሚሠራባቸው ይሆናል፡፡ በአማራ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ድርጅቶች ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችም በተመሳሳይ መልኩ ምላሽ የሚሰጣቸው ይሆናል ነው ያሉት ዶክተር ደስታ፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Previous articleፕሬዝዳንት ሳኅለወርቅ ዘውዴ ከሩዋንዳው ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ ጋር ተወያዩ፡፡
Next articleደኢሕዴን አስቸኳይ ድርጅታዊ ጉባዔ ማካሄድ ጀመረ።