በመኸር እርሻ 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም እንደሚሸፈን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

170

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገር አቀፍ ደረጃ በ2015/16 የመኸር ምርት ዘመን 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም እርሻ እንደሚሸፈን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በግብርና ሚኒስቴር የብርዕና አገዳ ሰብሎች ዴስክ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ቢረዳ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በ2015/16 የመኸር ምርት ዘመን በክላስተርና በመደበኛ ከሚሸፈነው 16 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታሩ መሬት በኩታ ገጠም እርሻ ይሸፈናል፡፡

በሚኒስቴር ደረጃ በተመረጡ አስራ ሁለት ሰብሎች ላይ የኩታ ገጠም እርሻ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አቶ ፍቃዱ ጠቁመዋል፡፡

በኩታ ገጠም ከሚለማው 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት 299 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ አቶ ፍቃዱ አመላክተዋል፡፡ ስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍ፣ በቆሎና ማሽላ በኩታ ገጠም እርሻ ከሚመረቱ መካከል ዋነኞቹ መሆናቸውን አቶ ፍቃዱ አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ፍቃዱ ገለፃ፤ የኩታ ገጠም እርሻ በዋናነት አርሶ አደሮች ከተበጣጠሰ የማሳ አጠቃቀም በመውጣት በአንድ ላይ እንዲያመርቱ ለማደራጀትና አስፈላጊው የግብርና ሜካናይዜሽን ግብዓት ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ያግዛል።

የግብርና ባለሙያዎችም በተናጠል ከሚከናወን የግብርና ስራ ይልቅ በኩታ ገጠም የሚለማ እርሻ ላይ ድጋፍና ክትትል ለማድረግ የተሻለ አቅም ይፈጠርላቸዋል ብለዋል።

በየወረዳው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎችም አርሶ አደሩ የኩታ ገጠም እርሻ ዘዴን እንዲያዘወትር ግንዛቤ በመፍጠር፤ የክህሎት ስልጠና በመስጠትና ለአርሶ አደሩ የገበያ ትስስር በመፍጠር አይነተኛ ሚና እየተወጡ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ በኩታ ገጠም እርሻ ተጠቃሚ እንዲሆን ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ የግብርና ባለሙያዎች ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ ነው ያሉት አቶ ፍቃዱ፤ አርሶ አደሩን የመደገፍ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

አቶ ፍቃዱ እንደገለጹት፤ ኩታ ገጠም ግብርና በአንድ የተወሰነ አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮች አብረው የሚሰሩበት፣ አጎራባች መሬቶችን አንድ ላይ በማሰባሰብ፣ ምርታማነታቸውን ለማሳደግ፣ ሀብትና ዕውቀት የሚጋሩበት እንዲሁም ልምድ የሚለዋወጡበት በመሆኑ በስፋት ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።

የኩታ ገጠም እርሻ ዋና አላማ በኢትዮጵያ አብዛኛው የግብርና ድርሻ ያላቸውን አነስተኛ አርሶ አደሮች ምርታማነትና ትርፋማነት ማሻሻል እንዲሁም የአፈርና የውሃ ሀብትን የሚንከባከቡ ዘላቂ የግብርና አሰራሮችን ለማስተዋወቅ የሚረዳ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ከስድስት ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች በክላስተር ተደራጅተው የግብርና ሥራ በማከናወናቸው በቀላሉ የሜካናይሽንና የመስኖ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ ገበያ ላይ የመደራደር አቅማቸው መጨመሩን አቶ ፍቃዱ አስታውቀዋል።

ኢፕድ እንደዘገበው፤ ሚኒስቴሩም ግብርናውን ከማዘመን አንፃር የተሻሻሉ አሰራሮች ተግባራዊ እያደረገ ነው ያሉት አቶ ፍቃዱ፤ ለኢንዱስትሪ ግብዓት አቅርቦትና በአግሮ ፕሮሰሲግ ሥራ ከተሰማሩ የተለያዩ ባለሃብቶች ጋር የገበያ ትስስር የመፍጠር ስራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ቢደረጉም ዋጋቸው ቀንሶ ወደ ማኅበረሰቡ መድረስ አልቻሉም” የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር
Next article11ኛው የአማራ ክልል የመስሪያ ቤቶች ስፖርታዊ ውድድር በደሴ ከተማ ሊካሄድ ነው።