ከ161 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ።

131

ባሕር ዳር ፡ ግንቦት 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የጉምሩክ ኮሚሽን ከግንቦት 11 ቀን እስከ 17 /2015 ዓ.ም ባደረገው ክትትል 92 ነጥብ 5 ሚሊዮን የገቢ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች እና 68 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የወጭ፤ በድምሩ ከ161 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ተይዘዋል፡፡ በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድኃኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ ዕቃዎች የጦር መሣሪያዎች፣ አደንዛዥ ዕጾች፣የምግብ ዘይትና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል ሲል የዘገበው ኢፕድ ነው፡፡

በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ የወጭ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር የላቀ አፈጻጸም የተመዘገበ ሲሆን በዚህም አዋሽ ፣ ጅግጅጋ እና ድሬድዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ሲሆኑ በቅደም ተከተላቸው 46 ሚሊዮን፣ ዘጠኝ ሚሊዮን እና ስድስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በመያዝ ከፍተኛውን ድርሻ ወስደዋል፡፡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ኅብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ የተያዙ ሲሆን የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹን ሲያዘዋዉሩ የተገኙ አምስት ግለሰቦች እና ስድስት ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን በዚህ የሕግ ማስከበር ሥራ ላይ ለተሳተፉ የኮሚሽኑ ሰራተኞች ፣ የክልልና የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ለመላው ሕዝባችን ምስጋናውን ያደርሳል፡፡ የኮንትሮባንድ እና ሕገወጥ ንግድ የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ኅብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የጉምሩክ ኮሚሽን ጥሪውን ያቀርባል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበዓባይ ግድብ ሰው ሠራሽ ሐይቅ ላይ ዓሣ ማስገር ተጀመረ።
Next article“በቀጣዩ የመኸር እርሻ ከ508 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል” የግብርና ሚኒስቴር