
ደባርቅ ፡ ግንቦት 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን” በሚል መሪ መልዕክት በወቅታዊ ችግሮችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ተኩረት አድርጎ በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ ሲካሄድ የቆየው ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ተጠናቅቋል።
ኮንፈረንሱ የውይይት ሰነድ ቀርቦና ተሳታፊዎችም በሰነዱ ላይ ጥያቄዎች አንስተው ውይይት በማድረግና መግባባት ላይ በመድረስ ነው የተጠናቀቀው።
የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ የሽወርቅ ሞላ በመድረኩ በአማራ ብልጽግና ፓርቲ ተዘጋጅቶ በቀረበው ሰነድ ላይ ጠንካራ ውይይት ተደርጎበታል።
ወይዘሮ የሽወርቅ “ሰነዱ ለውጡ የአማራ ሕዝብ ከአመራሩ ጋር ተቀናጅቶ በመሥራቱ የመጣና ብልጽግና ፓርቲ ከተመሠረተ በኋም እንደ መንግሥት በክልሉና በሀገሪቱ ስለተከናወኑ የልማት ሥራዎች ግንዛቤ በመፍጠር አመራሩ ለብልጽግና እና ለለውጡ ወጥ አመለካከት እንዲይዝ አድርጓል ብለዋል።”
ሌላኛው ተሳታፊ አቶ ከልለው መንግሥቴ፤ሰነዱ የክልሉን መሠረታዊ ችግሮች፤በፈተናዎች ውስጥ ኾነን ያመጣናቸውን ለውጦችና መውጫ መንገዳችን ምን ሊሆን እንደሚገባ በአግባቡ የተተነተነ እንደመኾኑ ኮንፈረንሱ ክልሉ የገጠመውን ችግር በአግባቡ ይፈታል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል። ለዚህም የተግባር ምላሽ በመስጠትና ጠንካራ ፓርቲ፣ሕዝብና መንግሥት በመመስረት ጫናን ተቋቁሞ ለውጤት መብቃት ያስፈልጋል ብለዋል።
ከሰነዱ ባለፈም ያደሩና ወቅታዊ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በተሳታፊዎች ተነስተዋል የሚሉት አቶ ከልለው፤ በተለይም የወሰንና ማንነት ጉዳዮችን በፍጥነት ሕጋዊ ምላሽና ዕውቅና እንዲያገኙ ከማድረግ፤የክልሉን ሕዝብ ፍትሐዊ የመሠረተ ልማት ተጠቃሚ ከማድረግ፤የአማራ ሕዝብ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብትን ከማስከበርና ከማክበር፤በጦርነት የወደሙ አካባቢዎችንና የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ከመገንባትና ከማቋቋም፤የፕሪቶሪያው ስምምነት አተገባበር ለሕዝብ ግልጽ ከማድረግና በፍጥነት ከማጠናቀቅ አኳያ የፌዴራል መንግሥት ምን እየሠራ ነው? የሚሉት ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል ናቸው ብለዋል።
ሕዝባችን የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ከታች እስከላይ ያለው የመንግሥት መሪ ወጥ አቋም ይዞ የሚጠበቅበትን ኀላፊነት መወጣት እንዳለበት፤ የችግሮች ኹሉ መፍቻ ቁልፍ ደግሞ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የትግል ስልት መኾኑን በኮንፈረንሱ መግባባት እንደቻሉ ነው ተሳታፊዎቹ የተናገሩት።
የሰሜን ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይመር ስዩም ፤ሕዝቡንና አመራሩን በተለያዩ አጀንዳዎች የመጥመድና የዕለት ተዕለት ተግባሩንና ልማቱን እንዳያከናውን የማድረግ፤የክልሉ ሕዝብ ልማትን በማፋጠን ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር አብሮ የሚኖርበትንና የሚቀጥልበትን መንገድ ከመፍጠር አንጻር ክፍተቶች መኖራቸው፤ብልሹ አሠራርና የሌብነት መስፋፋት እንደ ክልል ከገጠሙን ወቅታዊ ችግሮች መካከል ናቸው ብለዋል።የአመራርና የአባላት አንድነት በመፍጠርና ሕዝቡን በማስተባበር ችግሮችን ለመፍታት በኮንፈረንሱ መስማማታቸውንም ገልጸዋል።
ለሦስት ቀናት በቆየው ኮንፈረንስ ዞናዊ፣ክልላዊና ሀገራዊ ጥያቄዎችን ላይ በዝርዝር በመወያየት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን አስቀምጠናል ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ልዩ አማካሪ አቶ ደሳለኝ አስራደ ናቸው ።
“ከለውጥ በኋላ የአማራ ክልልን አመራር ልዩ የሚያደርገው የሕዝብና የአመራር ጥያቄ የሚባል የለም የሚሉት ልዩ አማካሪው የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የአማራ ክልል አመራር የመታገያ ጥያቄዎች ናቸው” ብለዋል።የክልሉ መንግሥት የሚታገልባቸው ከ 8 የሚበልጡ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች መኖራቸውንም ነው የተናገሩት።
አቶ ደሳለኝ “ጥያቄዎቹ ድሮ የአማራ ሕዝብ አጀንዳ ብቻ የነበሩ አሁን ላይ የብልጽግናም የፌዴራል መንግሥትም አጀንዳ የኾኑ ናቸው።ሥለኾነም የውስጥ ሰላምና አንድነትን በመጠበቅ፤ፍረጃን በማስወገድ ጤናማ የኾነ፤ ሌሎች ኢትዮጵያዊያንን ያማከለ፤ኀይል የሚያሰባስብ፤ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የትግል ስልት በመከተል ምላሽ እንዲያገኙ ማድረግ ከኹሉም ይጠበቃል ነው ያሉት።
ሦስት ቀን በቆየው ኮንፈረንስ አመራሩ ንድፈ ሀሳብን ብቻ ሳይኾን ወደ ተግባር የሚለውጥ ዕቅድ የያዘበትና መግባባት ላይ የደረስበት ውይይት መደረጉንም አስረድተዋል።
ዘጋቢ :-አድኖ ማርቆስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!