ባለፈው 9 ወር የግብርናው ዘርፍ 2 ቢሊዮን የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት መቻሉን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

62

አዲስ አበባ: ሚያዝያ 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የግብርና ሚኒስቴር የሀገሪቱን የ9 ወር የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ የሁሉም የክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊዎች እና ተወካዮች በተገኙበት በሳይንስ ሙዚየም እያካሔደ ነው።

በውይይቱ አዲስ የተጀመረው የሌማት ቱርፋት 26 ሺህ መንደሮችን መፍጠር መቻሉ ተገልጿል።

በእቅድ ግመገማው መነሻ ንግግር ያደረጉት የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ በሀገራች ትልቅ መነቃቃት እያሳየ ያለው ግብርና በዓመቱ 2 ቢሊዮን የውጭ ምንዛሬ አስገኝቷል ብለዋል፡፡ ይህም የሀገሪቱን የውጭ ንግድ 80 በመቶ ይሸፍናል ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ ግብርና የሀገራችን ትልቁ አቅም ከመኾኑ አንጻር በክረምቱ ወቅት የማዳበሪያ ችግር እንዳያጋጥም ቅደመ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።

በዘርፉ አንድ ሚሊዮን የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ 900 ሺህ ያክል ወይም 90 በመቶ ማሳካት ተችሏል።

በዓመቱም ከፍተኛ የበልግ ዝናብ እየዘነቡ ከመኾኑ አንጻር የበጋ ስንዴን በፍጥነት መሰብሰብ ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሩ በዚህ የበልግ ወቅትም 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን አስታውሰዋል፡፡

የዘንድሮው እና ሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በጥራት ላይ ያተኩራል። በዚህ መሰረት ችግኝ ሲፈላ ለየትኛው አየር ኹኔታ እንደሚመች ተጠንቶ እንደየአካባቢው ኹኔታ የሚላመድ ችግኝ ላይ ትኩረት ይደረጋል ። የመትከያ አካባቢዎችም ቀድመው ተለይተው የጉድጓድ ቁፋሮ ይካሔዳል ብለዋል።

እንደ ዶክተር ግርማ ገለጻ በ2014/15 የመኸር ወቅት 472 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ታቅዶ 480 ሚሊዮን ኩንታል መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።

26 ሺህ የሌማት ትሩፋት መንደሮች መፍጠር መቻሉን ያነሱት ሚኒስትሩ የእንስሳት ውጤቶችን ከፋብሪካዎች ጋር የማስተሳሰር እና ስጋን ከቄራዎች ጋር የማስተሳሰር ሥራ መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።

ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleብሔራዊ ባንክ አምራች ኢንዱስትሪውን የሚደግፍ ማሻሻያ እያደረገ መሆኑን ገለጸ።
Next articleበኩር ጋዜጣ ሚያዝያ 30/2015 ዓ.ም ዕትም