
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ብሔራዊ ባንክ አምራች ኢንዱስትሪውን በፋይናንስ መደገፍ የሚያስችሉ ማሻሻያዎችን እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የፋይናንስ ተደራሽነት ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በሚል መሪ ቃል የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምኅረቱ፣ ሚኒስትሮች፣ የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ፣ ባለሃብቶችና ሌሎች በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ባላድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
የፓናል ውይይቱ በማምረቻ ኢንዱስትሪው ዘርፍ በሚስተዋሉ የፋይናስ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ፤ አምራች ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ የተለያዩ የማሻሻያ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚና የገበያ ስርዓት መፍጠር ፣ የውጭ ምንዛሬ ስርዓቱን ማስተካከል እና የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነት ማረጋገጥ ባንኩ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት መሆናቸውን አንስተዋል።
የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የልማት ባንክ ለአምራች ኢንዱስትሪውና ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ፋና ዘገባ፤ በዝቅተኛ ወለድ ብድር ማቅረብን ጨምሮ ለዘርፉ በቂና ቀልጣፋ የፋይናንስ አገልገሎት ለመስጠት አዳዲስ የሥራ ክፍሎች እንዲቋቋሙ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!