
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በየዘመኑ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የተዳፈሩ ሁሉ እድል አልቀናቸውም፤የተሳካ ታሪክም የላቸውም፡፡ በጀግኖች ኢትዮጵያውያን ድል እየተመቱ ተመልሰዋልና፡፡ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አርበኞች በፍጹም የሀገር ፍቅር፤በፍጹም ታማኝነት በደማቸው የሀገርን ሉዓላዊነት አጽንተዋል፡፡ የአምስት ዓመታቱ የእምቢተኝነት ተጋድሎ ኢትዮጵያውያንን በኀይል አንበርክኮ መግዛት እንደማይቻል ከዓድዋ ቀጥሎ፤ለዓለም ትምህርትን ሰጥቶ ያለፈ ስለ መኾኑ ይነገራል።
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህሩ ዶክተር ዓለማሁ እርቅይሁን ኢትዮጵያውያን ጀግንነትን ከታሪክ፤ጀግንነትን ከማንነታቸው፣ጀግንነትን በደም የወረሱ ስለመኾናቸው ነው የሚያስረዱት፡፡ በየዘመኑ የውጭ ወራሪ በእብሪት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ተዳፍረው ሽንፈትን ተከናንበው፤በጀግኖች ኢትዮጵያውያን ድል የተመቱበት የታሪክ አንጓ የሚያስረዳው ኢትዮጵያ ጀግና የማይነጥፍባት የአርበኞች ምድር ስለመኾኗም ነው፡፡
በእርግጥም የ1888ቱ የጥቁር ሕዝብ ሁሉ የነጻነት ተምሳሌት- ዓድዋ፤ የአይበገሬዎቹ የድል አምባ- ካራማራ፤ የአምስት ዓመቱ እልሕ አስጨራሽ የአርበኝነት ትግል፤ ለኢትዮጵያውያን የጀግንነት ጀብዱ ጥግ የትውልድ መስታወት ናቸው፡፡
“ማንም ወራሪ ኃይል ቢመጣ ኢትዮጵያውያንን ሊያምበረክክ፣ኢትዮጵያንም ሊያሸንፍ አይችልም” የሚለው አስተሳሰብ የጀግንነት የአባት ውርስ ስለመኾኑ ማሳያ እንደኾነ ነው የታሪክ ባለሙያው የሚያስረዱት፡፡
ደራሲ ጳውሎስ ኞኞ “የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት” በተሰኘው መጽሐፋቸው ከአውሮፓ እስከ እስያ፤ በአፍሪካም ጭምር በየጊዜው በተነሱ ታላላቅ መንግሥታት ኢትዮጵያ ተፈትናለች፡፡ሉዓላዊነቷን ተዳፍሮ በቅኝ ግዛት ለማንበርከክ ከ2 ሺህ ጊዜ በላይ ሙከራ ተደርጓል፡፡ ኢትዮጵያ ግን በጀግኖች ልጆቿ ሳትበገር ሉዓላዊነቷንም፤ክብሯንም አስጠብቃ ቀጥላለች ይሉናል።
መንግሥታት ገና ከክርስቶስ ልደት በፊት በ336 በግሪክ ነግሶ የነበረው ታላቁ አሌክሳንደር ግዛቱን ሲያስፋፋ መዳረሻው ኢትዮጵያም ጭምር እንደነበረች በታሪክ ተጠቅሷል፡፡ በዘመኑ የኢትዮጵያዊቷ ንግሥት በህንደኬ ብልሕነትና ጥበብ፤የወታደሮቿንም ብዛትና አቅም፤የሰላዮቹንም ጥበብ ፤የሕዝቡን አንድነት ከተረዳ በኋላ ግን እቅዱን እንደቀየረ ጳውሎስ ኞኞ በመጽሐፋቸው ሰንደዋል፡፡
በየዘመኑ አርፈው የማይተኙ ጠላቶች ያሏት ኢትዮጵያም አይደፈሬነቷን በጀግኖች ልጆቿ አስቀጥላለች፡፡ጣሊያን በመጀመሪያውም፤ በሁለተኛውም ወራራ በከፈተችው ጦርነቶች ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ያደረገችው ሙከራ አልተሳካም፡፡
ጳውሎስ ኞኞ በመጻሕፋቸው እንዳሰፈሩት ጣሊያን ኢትዮጵያን ስትወርር ያላትን የጦር ዝግጅት አስመልክቶ “በቅኝ ግዛት ታሪክ ተወዳዳሪ የሌለው ታላቅ ጦርነት ነው” ሲሉ የጣሊያን ንጉሥ ቪቶሪዮ ኢማኑኤል ተናገሩ። በኋላም ሞሶሎኒ “ኢትዮጵያን ለ40 ዓመታት ታገስን፤አሁን ግን በቃ” ሲሉ እልሃቸውን ተነፈሱ፡፡ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ግን ለጠላት የሚደፈሩ አልኾኑም፡፡ ሀገርን በመስዋእትነት አጽንተው አይበገሬነትን ለትውልድ አሻገሩ፡፡
ጣሊያን ለበቀል በጀመረችው ወረራ ድጋሜ ሽንፈትን ቀምሳ ተመለሰች፡፡ ጠላትን በዱር በገደሉ እየገቡ ያርበደበዱ ጀግኖች አርበኞችም ለሀገር ታሪክ የማይዘነጋ አሻራ አስቀምጠዋል፡፡ እንኾ የጀግኖች አርበኞች የድል መታሰቢያ ቀን ጥንታዊ ጀግኖች አባቶቻችን በዱር በገደሉ ተዋድቀዉ ሀገራችንን ከጠላት ነጻ ያደረጉበትን ገድል እየዘከረ 82ኛ ዓመቱን አስቆጥሯል፡፡
በነፍጣቸው ሀገር ያስከበሩ፤ጦርነቱ ለኢትዮጵያውያንና ለኢትዮጵያ ጠባሳው ሕመም እንዳይኾን በጀግንነት የድል ሐውልት ታሪክ ላቆሙ ሁሉ ክብርና ሞገስ ይገባቸው፡፡
“የጀግኖች ደም ጥሪ ቃሉ ቀሰቀሰኝ፤
ለታሪክ አደራ ለድል ታጠቅ አለኝ”
እንዲል ገጣሚው፤ ጀግንነትና አርበኝነት የኢትዮጵያውያን የአባት ውርስ ነውና ትውልድ የሚኮራበት፣ትውልድ የሚቀረጽበት ኢትዮጵያዊ እሴት ለመኾን በቅቷል፡፡
ዘጋቢ፡-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!