
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አብዝተው ታመኑላት፣ ለፍቅሯ ደም አፈሰሱላት፣ አጥንት ከሰከሱላት፣ ሕይወት ገበሩላት፡፡ ታምነው ጠበቋት፣ ጸንተው አጸኗት፣ በርትተው አበረቷት፣ በጀግንነታቸው አስከበሯት፣ በብርቱ ክንዳቸው ነጻ አደረጓት፡፡ ንጉሡ ባልነበሩበት፣ ስንቅ እና ትጥቅ የሚያቀብል በሌለበት፣ ዘመናዊ መሣሪያ ባልታጠቁበት፣ የጠላትን መርዝ የሚከላከሉበት መሳሪያ ሳይኖራቸው፣ በባዶ እግራቸው እየተመላለሱ ከጠላት ተከላከሏት፣ በሕይወት ዋጋ ነጻ አድርገው አኖሯት፡፡ ጠላቶቿን ጥለው አኮሯት፡፡
ለአረንጓዴ ቢጫ ቀዩዋ ሠንደቅ ፍቅር ጸኑላት፣ በመከራ ዘመን አሰቧት፣ በሞት መካከል እያውለበለቡ ተዋደቁላት፣ ጠላትን ድባቅ መትተው በተራራው አናት ላይ ከፍ አድርገው በክብር አውለበለቧት፣ እነርሱ ያውለበለቧትን፣ እነርሱ ከፍ አድርገው የሰቀሏትን፣ እነርሱ ያከበሯትን፣ እነርሱ ያጸኗትን ሠንደቅ ችሎ የሚደፍራት፣ ሆኖሎት የሚያወርዳት የለም፡፡ እንደተከበረች፣ በክብር እንደተውለበለበች፣ ከፍ ከፍም እንዳለች፣ ከሁሉም ልቃ እንደታየች ትኖራለች እንጂ፡፡ መርዝ እየተርከፈከፈበት ማን በጽናት ይዋጋል? እየሞተ ማን ይታመናል? እየቆሰለ ማን ሀገሩን ያፈቅራል? መርዝ በሰማይ እየተርከፈከፈባቸው ሀገራቸውን ማፍቀር እንደምን ያለ ፍቅር ነው? የጥይት አረር እየወረደባቸው ለሀገር መታመን እንደምን ያለ መታመን ነው? እሾህ እየወጋቸው፣ አሜካላው እያሰቃያቸው ሀገሬን ማለት እንደምን ያለ መውደድ ነው? እንደምንስ ያለ ጥልቅ ፍቅር ነው?
ለዓመታት ታመኑላት፣ ለዓመታት መከራዋን ተቀበሉላት፣ ስቃይዋን ተሰቃዩላት፣ መቁሰሏን ቆሰሉላት፣ መድማቷን ደሙላት፤ ከእምነታቸው አልጎደሉም፣ ቃላቸውን አላጠፉም፣ ከክብራቸውም አልወረዱም፣ እንደታመኑ ኖረው እንደታመኑ አለፉ እንጂ፡፡ መከራው ይሰብራቸዋል ሲባል የበለጠ አጸናቸው፣ መከራው ያጠፋቸዋል ሲባል የበለጠ አበዛቸው፣ መከራው ተስፋ ያስቆርጣቸዋል ሲባል የበለጠ ተስፋ አሰነቃቸው፣ መከራው ከጉዞ ያስቆማቸዋል ሲሉ ይባስ ብለው አፈጠኗቸው፡፡ እነርሱ ድንቆች ናቸውና ለሀገራቸው ሁሉንም መከራ ይቀበላሉ፡፡
የኢትዮጵያ አርበኞች በአምስት ዓመቱ የኢጣልያ ጦርነት ሥንቅ ከራሳቸው እየሰነቁ፣ ትጥቅ ከጠላታቸው እየነጠቁ፣ በፍጹም ታማኝነት፣ በበረታ ጀግንነት ተዋደቁ፡፡ ነጻነትንም አስጠበቁ፡፡ ጀግኖች አርበኞች ንጉሡ በዙፋናቸው የሉም፣ እኛም ዘመናዊ መሳሪያ የለንም እና አንዋጋም አላሉም፡፡ ለሀገራቸው ፍጹም ታምነው እና በአንድነት ጸንተው ተዋጉላት እንጂ፡፡
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ ባልቻ (ዶ.ር) አርበኞች እንደተጋድሏቸው ሀገር እንደማጽናታቸው ልክ ታሪካቸው ጎልቶ አልወጣም ይላሉ፡፡ በባርነት ላለመውደቅ፣ ነጻነትን ላለመነጠቅ፣ ክብርን ለመጠበቅ የተዋደቁት ቁጥራቸው የበዛ ነው፡፡ ብዙዎች ተሰውተዋል፣ ቆስለዋል፣ ደምተዋል፡፡ ልጆቼን አላሉም፣ ለሀብትና ንብረትም አልጓጉም፣ ለሕይወታቸውም አልሳሱም ሁሉንም ነገራቸውን ለኢትዮጵያ ክብር፣ ለሠንደቃቸው ፍቅር ሰጡ እንጂ፡፡ ኢጣልያ ከዓድዋ ሽንፈቷ በኋላ በጦር ቴክኖሎጂ አብባለች፣ ፈጣን የጦር አውሮፕላኖች፣ ዘመናዊ መድፎች፣ መትረጊሶች፣ የነብስ ወከፍ መሳሪያዎችን በገፍ አዘጋጅታለች፣ ፈጣን የጦር አውሮፕላኖቿን ገዳይ ቦንቦችና መርዞች ጭናቸዋለች፡፡ በዓድዋ ሰማይ ሥር የተንኮታኮተ ዝናዋን ከአፈር ለማንሳት የምትችለውን ሁሉ አዘጋጅታለች፡፡
እኒያ ጀግና ኢትዮጵያውያን ግን መርዝ የሚተፉ አውሮፕላኖች፣ በአሻገር እያጓሩ ጠላትን የሚደመስሱ ዘመናዊ መድፍና ታንኮች፣ ብሬን እና ዘመናዊ የነብስ ወከፍ መሳሪያዎች አልነበሯቸውም፡፡ ነገር ግን መርዝ ከሚተፉ አውሮፕላኖች የላቀ የልብ ጀግንነት፣ መከራ የማይፈተው ጽናት ነበራቸው፡፡ ያ ጽናታቸውን የትኛውም መከራ አይሰብረውም፣ ያን ጀግንነታቸውን የትኛውም ጦረኛ አይችለውም፣ ሁሉንም በልበ ሙላታቸው በፍጹም ጀግንታቸው ድል ይነሱታል እንጂ፡፡ ኢጣልያ ከዓድዋ ሽንፈት በኋላ ለበቀል ስትመጣ የኢትዮጵያ ጀግኖች የዓድዋው ድል ስሜት በልባቸው እንደጋለ ነበር፣ በዓድዋ የዘመቱ ጀግና የጦር መሪዎችም ከእነ ጀግንነታቸው ነበሩ፡፡ በዓድዋ የዘመቱ ጀግኖች፣ በሁለተኛው የኢጣልያ ወረራ ጊዜም ዘመቱ፣ አዘመቱ፡፡ ተዋጉ አዋጉ፡፡ የኢትዮጵያውያን ጀግንነት በኢጣልያ ወረራ ጊዜ የሚደንቅ ነበር፣ ነገር ግን በኢጣልያ ልክ ዝግጅት አላደረጉም ነበር ነው ያሉኝ ዶክተር አሰፋ፡፡ መኳንንቱና መሳፍንቱ በጀግነት ተዋጉ፣ ጦርነቱ እየከበደ ሄደ፡፡ ንጉሡም በመኳንንቱና በመሳፍንቱ ምክር ወደ ውጭ ሄዱ፡፡ አርበኞች ግን ወደ በረሃ ወረዱ፡፡ ጦርነቱም ያለ ማቋረጥ ቀጠለ፡፡
በሰማይ በምድር እሳት ለብሶ፣ እሳት ጎርሶ የመጣውን ጠላት በጀግንነት ገጠሙት፡፡ በአንድነት እና በጽናት ተናነቁት፡፡ የኢጣልያ የመርዝ ጭፍጨፋና ግፍ አርበኞችን ይበልጥ አጠነከራቸው፡፡ ኢጣልያ አርበኞች መከራው ሲበዛባቸው ፣ ወገኖቻቸውን በመርዝ እና በጥይት አረር እያቃጠልኩ ስጨርስባቸው ተስፋ ቆርጠው ጦርነቱን ይተውታል፣ እጅም ይሰጣሉ ብላ አስባ ነበር፡፡ ዳሩ ኢትዮጵያውያንን መከራና ስቃይ ያበረታቸዋል እንጂ ተስፋ አያስቆርጣቸውም፡፡ የኢጣልያ ግፍ በበረታ ቁጥር የአርበኞች ጅግንነት እና ጽናትም የበለጠ ጠነከረ፡፡ ይባስ ብለው በስስት የሚታዩትን ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስን ኢጣልያኖች ገደሏቸው፡፡ የአቡነ ጴጥሮስን ሞት የሰሙ አርበኞች ከዚሕ በኋላ ጠላትን ብንምረው አይማረን አያሉ የበለጠ አመረሩ፣ በጀግንነት እየፎከሩ፣ እያነጠሩ እየተኮሱ ጠላትን ይጥሉት ጀመር፡፡
የአቡነ ጴጥሮስ ጽናት፣ ሀገሬን ማለት፣ ከጠላት ፊት በእውነት፣ ለእውነት እና ስለ እውነት መሟገት፣ በኋላም በግፍ መሰዋት አርበኞችን የበለጠ እንዲሰባሰቡ አድርጓቸዋል፣ አሻፈረኝ እንዲሉም አድርጓቸዋል ነው ያሉኝ፡፡ ከንጉሡ ጋር የተቀያየሙ አርበኞች ሁሉ ሀገርና ንጉሥ የተለያዩ ናቸው በማለት በአንድነት እና በጀግንነት ከጠላት ጋር መዋደቃቸውንም ዶክተር አሰፋ ነግረውኛል፡፡
የኢጣልያ ጦር መርዝ የሚተፋ አውሮፕላን ይዞ፣ ዘመናዊ መሣሪያ ታጥቆ ከከተሞች አልፎ ወደ ገጠሩ መግባት አልቻለም፣ አርበኞች አላላውስ ብለውት ከከተማዋ ወጥቶ መግባት አይችልም ነበርም ብለውኛል፡፡ በጦርነቱ ጊዜ አብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል በአርበኞች ቁጥጥር ሥር ነበር፡፡ አርበኞች ጠላት ከገባበት እስከ ወጣበት ጊዜ ድረስ በጀግንነት ተዋድቀዋል፣ ክብራቸውንም አስጠብቀዋል፡፡ ጀግኖች የሚታጠቁት ከጠላት ማርከው፣ ጠላትን አንበርክከው ነው፡፡ የጦር መሳሪያ ፋብሪካ አልነበራቸውም፣ ጥይት የሚያቀርብም አልነበረም፣ በጀግንነት ተዋግተው ከጠላት ትክሻ ላይ መሳሪያ ይነጥቃሉ፣ በነጠቁት መሳሪያ መልሰው ጠላትን ይዋጋሉ፡፡ ድልም ያደርጋሉ እንጂ፡፡
አርበኞች ነጻነቷ የተከበረች ሀገር ያስረከበሩት በታላቅ ጀግንነት ነው፡፡ የዘመኑ ኢትዮጵያውያንም ከአርበኞች ጽናትን፣ አንድነትን እና ጀግንነትን መማር አለባቸው ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከቆሙ ምድራዊ ኃይል አይበግራቸውም፤ የትኛውም ጠላት አያሸንፋቸውም ብለውኛል፡፡ ጠላቶች ኢትዮጵያውያንን አንድነታቸውን አሳጥተን፣ አቅመ ቢስ ማድረግ አለብን፣ አቅማቸውን ሲያጡም እንበታትናቸዋለን ብለው እንደሚሠሩም ዶክተሩ ነግረውኛል፡፡ በጽናት የመቆም፣ ጠላትን ድል የማድረግ እና አልሸነፍም ባይነት ከዘር እየተወራረሰ የመጣ ነውም ብለውኛል፡፡ ኢትዮጵያ በነጻነቷ የኮራች ሀገር እንደሆነች ሁሉ በሃብቱ እና በእድገቱም የኮራች እንድትሆን ዛሬ ላይ መሥራት ይገባል ነው ያሉት፡፡
የጠነከረ ሕዝብ ማንም አይነካውም፣ ማንም አይገፋውም፣ ልግፋው ቢል እንኳን አይጥለውም ነው ያሉኝ፡፡ ከአባቶቻችን ጽኑ የሀገር ፍቅር ከተማርን የምናስቀና ሕዝቦች እንደሆን እንቀጥላለንም ነው ያሉት፡፡ አባቶች ስለ ሀገር እና ስለ ሀገር ፍቅር ብቻ ነው ያስቀመጡት፡፡ የአሁኑ ትውልድም የሀገር ፍቅሩን ማስቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን እኒያ ጀግኖች በጽናት አጽንተዋታል፣ በጀግንነት ጠብቀዋታል፣ በፍጹም ታማኝነት ከፍ አድርገዋታል፡፡ አንተም እንደ አባቶችህ አጽናት፣ እንደ አባቶችህ በደምና አጥንት ጠብቃት፣ ከሥርዓት በላይ አድርገህ ተመልከታት፣ ሀገር ከማንም ጋር የማትነጻጸር ልዩ ስጦታ ናትና፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!