
👉በባሕር ዳር ከተማ ከገጠር መንገድ እሰከ ኤርፖርት ያለው መንገድ በጀግኖች አርበኞች ተሰይሟል።
ባሕር ዳር:ሚያዝያ 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአምስት ዓመቱን የአርበኝነት ተጋድሎ የሚዘክረው፣ 82ኛው የጀግኖች አርበኞች ቀን በባሕር ዳር ከተማ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብሯል። በ1888 ዓ.ም ጣሊያን በእብሪት ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለማንበርከክ ያደረገችው ሙከራ ዓድዋ ላይ መከነ። ታዲያ በኢትዮጵያውያን ክንደ ብርቱ ጀግኖች ድል የተመታቸው ጣሊያን ዓድዋ ላይ የደረሰባትን ውርደትና ሽንፈት ለማወራረድ ከ40 ዓመታት በኋላ ለበቀል ጦርነት ዓወጀች።
በግልጽ ወረራዋን ኢትዮጵያ ላይ ጀመረች ፣ ጠላት በዘመነ የጦር መሣሪያው ጊዜያዊ ድልን ቢቀዳጅም ፣ በየአቅጣጫው “እንቢ ለሀገሬ” ባሉ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ግን ድሏን ማጽናት አልተቻላትም። ከአምስት ዓመት ተጋድሎ በኋላ በ1933 ዓ.ም ጣሊያን ድጋሜ በሐበሻ ምድር ድል ተነሳች። የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና ነጻነት ለማንበር ጀግኖች የኢትዮጵያ አርበኞች በአምስት ዓመቱ የአርበኝነት ዘመን ታሪክ የማያደበዝዘው ጀብዱ ፈጽመዋል።
ውለታቸውን የሚዘክር፣ለከፈሉት መስዋዕትነትና ሀገር ከነክብሯ ለትውልድ እንድትዘልቅ ላደረጉት የጀግንነት ገድል ምስጋና በየዓመቱ ሚያዚያ 27 ቀን የጀግኖች አርበኞች ቀን ይዘከራል። ዘንድሮ ለ82ኛ ጊዜ በተከበረው የጀግኖች አርበኞች መታሰቢያ ቀን በባሕር ዳር በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብሯል። በዕለቱ ንግግር ያደረጉት በአማራ ክልል የጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዳኝነት አያሌው ጀግናን ማክበር ፣ ለሀገር በመስዋዕትነት ከፍለው ሀገር ያጸኑ ጀግኖችን መዘከር እንደሚገባ በአጽንዖት ተናግረዋል።
“ጀግናን መፍጠር ጀግናን ከማክበር ይጀምራል” ያሉት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት የሀገርን ነጻነት፣የሀገርን ሉዓላዊነት ያጸኑ ጀግኖቻችን እንኮራባቸዋለን፣ እናከብራቸዋለን ነው ያሉት። የዚህ ዘመን ትውልዶች ከድል ታሪኩ በመማር በመከባበር፣በመደጋገፍ፣በአንድነት ሀገርን ማጽናት ይገባናል ሲሉም ተናግረዋል።
በአንድ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ በመተባበር ሀገርን ማሻገር ይገባል የሚሉት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት “ሀገሩን የማያውቅ ከብዙ ሴቶች መካከል እናቱን ለይቶ የማያውቅ ሕጻን እንደማለት ነው” እና ሀገራችን በምንና እንዴት እንደቆመች መረዳት ይገባናል ብለዋል። በሚጠበቅብን ዘርፍ ሁሉ የአርበኝነት ሚናችን መወጣት ይገባናል ሲሉም አሳስበዋል።
ዛሬ የምናከብረው ጀግኖች አርበኞቻችን ወራሪ ጠላትን አሳፍረው የመለሱበትን የኢትዮጵያን የድል ቀን ፣ጀግኖች ነጻ ሀገር ያጸኑበትን የጀግንነት፣የአርበኝነት ጥግ ማሳያ ቀን ነው ያሉት ደግሞ በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ናቸው። ከጀግኖቻችን ትምህርት ወስደን ሀገርን መጠበቅ፣ሀገርን ማስከር ይገባል ያሉት ከንቲባው በተለይም አሁን እንደ ሀገር ከገጠመን ችግር ለመውጣት የተጠቀሙበትን የአንድነት፣ የመደማመጥና የመደጋገፍ ባሕል ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።
በዚያ ወቅት አባቶቻችን ዘመናዊ መሣሪያ ባይኖራቸውም ከዓለት የጠነከረ ፍቅርና አንድነት ነበራቸውና የድሉ ባለቤት ለመኾን በቅተዋል ይላሉ ድረስ ሳህሉ ( ዶ.ር)። ዛሬም ወጣቱ ከአባቶቹ ጽናትን፣መከባበርን፣ተጋግዞ ጠላትን መመከትን ባሕል በማድረግ የተከበረች፣በኢኮኖሚም የጠነከረች ሀገር ማንበር ይኖርበታል ነው ያሉት።
ሀገርን ከነክብሯ ላስረከቡን ጀግኖቻችን ምስጋና ይገባል ያሉት ደግሞ በባሕር ዳር ከተማ በተከበረው የጀግኖች አርበኞች ቀን ከአባት አርበኞች ሰንደቅ ዓላማውን የተቀበሉ ወጣቶች ናቸው። ወጣት ፍሬገነት ደሴ እና ወጣት እሸቴ ገበየሁ ለአሚኮ እንደተናገሩት የአባቶቻችን የድል ጥበብ ለትውልድ የማይነጥፍ ትምህርት የሚኾን ነው። ሉዓላዊነቷ የተከበረች ሀገር ለማስቀጠል፣ ወጣቱ በሰከነ መንገድ የአባቶቻችን አርዓያነት መውስድ አለበት ነው ያሉት ወጣቶቹ። በዝግጅቱ ላይ በባሕር ዳር ከተማ ከገጠር መንገድ እሰከ ኤርፖርት ያለው መንገድ በጀግኖች አርበኞች ስም መሰየሙን የማሕበሩ ፕሬዚዳንት ዳኝነት አያሌው አብስረዋል።
ዘጋቢ:- ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!