“በአቶ ግርማ የሺጥላ ላይ የተፈፀመው አሰቃቂ ግድያ የፅንፈኛ ኃይሎቹን ትክክለኛ መልክና ገፅታ ለሕዝቡ በይፋ ያጋለጠ ነው” የጸጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል

90
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 21/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በማፍረስ ክልላዊ ስልጣንን በኃይል ለመቆጣጠር በሚጥሩ ጽንፈኛ ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ እየወሰደ መሆኑን የጸጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል፡፡
የጸጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል እንዳስታወቀው ለአማራ ሕዝብ እንታገላለን በሚል በውስጥም በውጭም በመቀናጀት የራሳቸውን ህቡዕ አደረጃጀት የፈጠሩ አካላት ከመሰል ቡድኖች ጋር በመቀናጀት የሕዝቡን የቁርጥ ቀን ልጆች መልሰው እየበሉ ይገኛሉ፡፡
እነዚህ ፅንፈኛ ኃይሎች የአማራ ክልል ብልፅግና ጽሕት ቤት ኃላፊ እና የክልሉ የቁርጥ ቀን ልጅ የሆነውን ግርማ የሺጥላን በመግደል አስነዋሪ ድርጊታቸውን አስመስክረዋል ብሏል ግብረ ኃይሉ፡፡
ይሄንን እኩይ የጥፋት ሴራ እየፈፀሙ ያሉ ፅንፈኛ ኃይሎች የአማራ ሕዝብ የልማትና የሰላም ተጠቃሚ እንዳይሆንና የተረጋጋ ሕይወት እንዳይኖረው እንዲሁም በመንግሥት የሚወሰኑ ውሳኔዎች እንዳይተገበሩ እንቅፋት ሲፈጥሩ መቆየታቸውን የጋራ ግብረ ኃይሉ መግለጫ አመልክቷል፡፡
በየአካባቢው የተደረጉ የሽምግልና ሂደቶችን በመግፋት እንዲሁም የተቀበሉ በመምሰል በህቡዕ ተደራጅተውና ተቀናጅተው ሕገ ወጥ ተግባራቸውን መቀጠላቸውንም ነው ግብረ ኃይሉ ያስታወቀው፡፡
በአማራ ክልል ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን በማፍረስም ክልላዊ ስልጣንን በኃይል ለመቆጣጠርም ሲጥሩ መቆየታቸውን መግለጫው ጠቅሷል፡፡
የጸጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይልም ይህን ተከትሎ አስፈላጊና ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ነው የገለጸው፡፡
ይሄ ጽንፈኛ ኃይል በአማራ ክልል ሳይገደብ እንደ ሀገርም መንግስትን በኃይል ከስልጣን ለማስወገድ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም ያለው የጋራ ግብረ ኃይሉ መግለጫ ከዚህ የጥፋት መንገዳቸው እንዲመለሱ በተደጋጋሚ የተሰጣቸውን ዕድል ከመጠቀም ይልቅ አሁንም በሕገወጥ ተግባራቸው መቀጠላቸውን አመልክቷል፡፡
በዚህ ህገ ወጥ ተግባራቸውም በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በሕግ እየታየ የሚገኙ በርካታ የቡድኑ አባላት መኖራቸውንም ግብረ ኃይሉ አስታውቋል፡፡
መንግስት በሀገሪቱ ብሎም በክልሉ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ በሌሎቸም የሕገ ወጥ ቡድኑና ቡድኑን በገንዘብና በሐሳብ በህቡእ በሚደግፉ አካላትና ግለሰቦች ላይ የማያዳግም እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ ነው ያስታወቀው፡፡
በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ የፅንፈኛ ቡድኖቹ ደጋፊዎች በዚህ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጅ ላይ የተፈፀመውን ግድያ ከመኮነን ይልቅ አሳፋሪ በሆነ መልኩ ገዳይ ቡድኖቹን ሲደግፉ ተስተውለዋል ብሏል መግለጫው፡፡
ሐሳብን በሐሳብ ከማሸነፍ ይልቅ ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት ባፈነገጠ መልኩ በአሰቃቂ ሁኔታ ግድያ የፈጸሙትን ፅንፈኛ ቡድኖች ሕዝቡ በአንድነት በማውገዝ ኢትዮጵያዊ ጨዋነቱን ሊያስመሰክር ይገባልም ብሏል፡፡
በአቶ ግርማ የሺጥላ ላይ የተፈፀመው አሰቃቂ ግድያ የፅንፈኛ ኃይሎቹን ትክክለኛ መልክና ገፅታ ለሕዝቡ በይፋ ያጋለጠ ነው ብሏል የደኅንነትና የጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል፡፡
መንግስት ለሕዝቡ ሰላምና ደኅንነት መረጋገጥ ግዴታውን ለመወጣት አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ የጀመረ በመሆኑ ሕዝቡም ይሄንን ተገንዝቦ የፌደራል እና የክልል የፀጥታ አካላት ተጠያቂነትን ለማስፈን የጀመሩትን እንቅስቃሴ ጥቆማና መረጃ በመስጠት እንዲደግፍ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የፅንፈኛ ኃይሎቹን አስነዋሪ ተግባር በመሸፋፈን በተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገፆች መሰረተ ቢስ ወሬዎችን ከሚያሰራጩ የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች ሕብረተሰቡ ራሱን እንዲጠብቅ ግብረ ኃይሉ አሳስቧል፡፡
ግብረ ኃይሉ እየወሰደ ያለውን እርምጃ በቀጣይ ለሕዝቡ የማሳወቅ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያረጋገጠው፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የጋራ እሴቶቻችን ለማሳደግ እንታትራለን፣ በሴራ ምሳር ቀስ እያለ እሴቶቻችን ለመመንጠር የሚሠራ ደግሞ አለ” አቶ ግርማ የሽጥላ
Next articleየአቶ ግርማ የሽጥላ የመጨረሻ ቃለ መጠይቅ