“ኢየሱስ በስድስት ሠዓት ሲሆን ቀራንዮ ላይ ተሰቀለ” የቅኔ እና የአዲስ ኪዳን መምህር ጥቀኄር ወርቄ

187
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 6/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከወንበዴዎች ይቆጠራል ተብሎ የተጻፈው ይፈጸም ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ በሁለቱ ወንበዴዎች መካካል ተሠቀለ፡፡
በስድስት ሠዓት ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቀለ፡፡ አይሁድ ኢየሱስ ክርስቶስን ከመስቀላቸው በፊት አምስት ቅንዋት ወይም ችንካር አዘጋጅተው ነበር፤ የችንካሩ እርዝማኔ አንድ ክንድ ከስንዝር ይረዝም እንደነበረ መጽሕፍት ከትበውታል፡፡
መስቀሉን በምድር ላይ አስተኝተው ቀኝ እጁን፣ ግራ እጁን፣ እግሮቹን አጣምረው፣ መሀል ልቡን እና አናቱን በመዶሻ መቱት፡፡ በኋላም መስቀሉን ባዘጋጁት እንጨት ላይ ሰኩት፡፡ በዚህ ሠዓት በሰማይ ሦስት በምድር አራት ታምራት ታይተዋል፡፡
ፀሐይ ጨለመች፣ ጨረቃ ደም ለበሰች፣ ከዋከብት በምድር ረገፉ፡፡ የአምላካቸውን እርቃን አናሳይም አሉ፡፡ በምድር ድንጋዮች ተሰነጣጠቁ፣ ሙታን ተነሱ፣ የቤተክርስቲያን መጋረጃ ለሁለት ተከፈለ “ሚካኤል አርመመ ገብርኤል ተደመመ” እንዳለው መጽሐፍ ሚካኤል ተደመመ ገብርኤል ግን ቁጣውን መቋቋም አልቻለም እና የያዘውን ሰይፍ በአላውያን ሊያሳርፈው ሲል የአብ ቸርነቱ የወልድ ትዕግስቱ ከለከለው እና ወደ ምድር ወረወረው የተወረወረው ሰይፍ የቤተ ክርሲቲያኒቱን መጋረጃ ቀድዶ እስከ እለተ ምጽአት ድረስ ወደ ምድር ሲወርድ ይኖራል ነው ያሉት መምህሩ፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ በለበሰው የአዳም ሥጋ ተጠማሁ አለ፡፡ አይሁድም ስጋውን በጥብጦ የሚጥል ሀሞት እና ከርቤ በጥብጠው በንስናስ ነክረው አቀረቡለት ቀመሰ እና ተፋው ሀጢያት መራራ ነው ሀጢያት በሠራችሁ ጊዜ አታውሉ አታሳድሩት ለመምህረ ንስሃችሁ ተናዘዙት ሲል ምሳሌ በመኾን ተፋው ብለዋል መምህሩ፡፡
ዘጋቢ፦ ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ጠዋት በነጋ ጊዜ በቃ ይሠቀል ብለው ደመደሙ” የቅኔ እና የአዲስ ኪዳን መምህር ጥቀኄር ወርቄ
Next article“ዘጠኝ ሠዓት ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድስት ነፍሱ ከቅዱስ ሥጋው የተለየችበት ሠዓት ነው” የቅኔ እና የአዲስ ኪዳን መምህር ጥቀኄር ወርቄ