ኢትዮጵያ ከረመዷን ጾም እዝነትን፤ ከሁዳዴ ጾም ምኅረትን አብዝታ ትጠብቃለች፡፡

37
ባሕር ዳር :መጋቢት 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በመፈናቀል እና ግጭት፣ በእርስ በእርስ ጦርነት እና ድርቅ ፣ በውጭ ጫና እና በኑሮ ውድነት ቀላል የማይባል ጊዜን ያሳለፈችውና እያሳለፈች ያለችው ኢትዮጵያ ከረመዷን ጾም እዝነትን፤ ከሁዳዴ ጾም ምኅረትን አብዝታ ትጠብቃለች፡፡
ሁዳዴ እና ረመዷን በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ዘንድሮም አብረው መዋል ጀምረዋል፡፡ በዚህ ወቅት በአብያተ ክርስቲያናት የዐቢይ ጾም ፣ሰርክ ጸሎት፤ ቅዳሴ እና ስግደት ፤ በመስጂዶቿ በረመዷን የጾም ወቅት ስግደት ፣ ጾም እና ዱዓ ከወትሮው በተለየ መልኩ በመከወን ኢትዮጵያ እጆቿ ወደ ፈጣሪ ተዘርግተዋል። ከአጽዋማቶቿም ለፈተናዋ መቋጫን፣ ለመከራዋ ፍጻሜን እና ለህመሞቿ መድኃኒትን አጥብቃ ትሻለች፡፡
ነብዮ ሙሐመድ( ሰ.ዐ.ወ) “ታላቁ ጦርነት ወይም ጅሃድ ራስን መግዛት ነው” እንዳሉት በዚህ የጾም ወቅት ኢትዮጵያዊያን ከገጠሟቸው ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች ለመውጣት ራሳቸውን የሚገዙበት ነው፡፡ ጾም እና ጸሎት የተለየ ኅይል እና ጉልበት እንዳላቸው የሚያምኑት ኢትዮጵያዊያን ሊቀ ነብያት ሙሴ እስራኤላዊያንን ከግብጽ ባርነት ነጻ እንዳወጣቸው ፣ የማስተሰሪያ ጾምን እንደታዘዙት አይሁዳዊያን፣ ከባቢሎን ምርኮ ነጻ እንደወጡት እስራኤላዊያን፣ እንደነነዌ ሰዎችም በጋራ ይጾሙ ዘንድ ጊዜው አሁን የኾነ ይመስላል፡፡
ጾም ሃይማኖታዊ ሥርዓት ያለው፤ መንፈሳዊ ትጋትን የሚጠይቅ ፣ መንፈሳዊ ትሩፋት እና ውጤት እንዳለውም ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ በጾም የተጠቀሙ ሁሉ ጾምን የጸሎት እናት፣ የእምባ ምንጭ እና የጽድቅ መሠረት የኾነች ደገኛ ሥርዓት ናት ይሏታል፡፡ “ጾም ተድላ ሥጋን የምታጠፋ የሥጋን ጾር የምታደክም ቁስለ ነፍስን የምታደርቅ፣ ለጎልማሶች ጸጥታንና እርጋታን የምታስተምር ፤ግብረ እንስሳዊነትን የምትከለክል፣ ሰው መላእክትን መስሎ የሚኖርባትና ኃይል መንፈሳዊ የሚጎናጸፍባት ደገኛ መሣሪያ ናት” /ጾመ ድጓ/ ኢትዮጵያም ከአጽዋማቶቿ እርጋታ እና ስክነትን፤ ሰላም እና መረጋጋትን የምትጠብቅበት ወቅት ላይ ትገናለች፡፡
ጾም በክርስትናም ሆነ በእስልምና የእምነት ተከታዮች ዘንድ ሥጋዊ ፈቃዳቸውን በመተው የነፍሳቸውን ፈቃድ ሁሉ በሙሉ ልባቸው በማስገዛት የሚፈጽሙት ሥርዓት ነው፡፡ ጾም በምግብ ወይም በመጠጥ ላይ የሚደረግ አድማ ብቻ አይደለም፡፡ ጾም ከምድር እስከ ሰማይ የተሳሰረ፤ ከነፍስ እስከ መንፈስ የተንሰላሰለ ረቂቅ ትርጉም፣ ኃያል ጉልበት እና ዘላለማዊ ትሩፋት ያለው ሃይማኖታዊ ሥርዓት ነው፡፡ በጾም እና ጸሎት ሀገር ከምድረ በዳነት፤ ሕዝብም ከባርነት ነጻ እንደወጡ ቅዱሳት መጻሕፍት ይነግሩናል፡፡
ኢትዮጵያ በእምነት የበረታ ሕዝብ እና በእምነት የጸና ማንነት ያቆማት የሀገር ምሳሌ እና አርዓያ ናት፡፡ ሃይማኖት ኢትዮጵያን እንደ መሪ አቅንቶ እንደ አስተማሪ አስልቶ የተለየች ሀገር ካደረጓት እሴቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ የሌላው ዓለም ሕዝብ ኢትዮጵያዊያንን የተለየ አድርጎ ከሚመለከትባቸው መንገዶች አንዱ “ኢትዮጵያዊያን፣ አማኞች እና ለሃይማኖታቸው ፍጹም ታዛዥ የኾኑ ሕዝቦች ናቸው” የሚለው እሳቤ ነው፡፡
በኢትዮጵያ በርካታ ተከታዮች ካሏቸው ጥንታዊ ሃይማኖቶች መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እና እስልምና ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ሁለቱንም ሃይማኖቶች ካጸኗቸው መሰረቶች መካከል ጾም አንዱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ካሏት ዋና ዋና ዐበይት አጽዋማት መካከል ዐቢይ ጾም ተጠቃሽ ነው፡፡ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ደግሞ ታላቁ የረመዷን ወር ጾም አንዱ ነው፡፡
በመላው ዓለም የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በሰፊው የሚታወቁት እና የዝምባብዌ ዜግነት ያላቸው የእስልምና አስተምህሮ ምሁር ሙፍቲ ኢስማኤል ሜንክ (ዶ.ር) በአንድ ወቅት ስለ ታላቁ የረመዷን ወር ሲናገሩ “ሰዎች ረመዷን የጾም ወር ብቻ ይመስላቸዋል፤ ጾም ግን የረመዷን አንዱ ተግባር ብቻ ነው። ረመዷን የሰላም፣ የመረጋጋት፣ የመፈወሻ፣ የቸርነት፣ የእዝነት፣ የምህረት፣ የይቅርታ እና ጀነትን የምናገኝበት ወር ነው፡፡ ይህ ወር ሙስሊም መኾናችንን የምናከብርበት ወር ነው፡፡ ሙስሊም ስለመኾናችን ራስን መግዛትን የምንለማመድበት፤ የፈለግነውን ብቻ ሳይኾን ሁሉን ቻይ የኾነው አሏህ የወሰነውን የምናደርግበት ወር ነው፡፡ በረመዷን ለአሏህ ቃል ለመገዛት ጥረት ማድረግ ግዴታችን ነው” ነበር ያሉት፡፡
አንዋርን እና ራጉኤልን፤ ሽዋ በር እና ገብርኤልን ከሀረር እስከ ጎንደር፤ ከሶማሌ እስከ ሚሌ መስጅዶቿን እና አብያተ ክርስቲያናትን መሳ ለመሳ አስቀምጣ በአዛን እና በቅዳሴ የምትባረከው ኢትዮጵያ ዘንድሮ ደግሞ ታላቁን ወር ረመዷንን እና ዐቢይ ጾምን በአንድ ላይ ተቀብላለች፡፡ አማኞች እንደኾኑ የሚነገርላቸው ኢትዮጵያዊያን በዚህ ቅዱስ እና ታላቅ ወር ራሳቸውን ለፈጣሪያቸው ያስገዛሉ፡፡ ኢትዮጵያም በዐቢይ እና በረመዷን አጽዋማት ዜጎቿ ከሚያደርጉት ጾምና ጸሎት፤ ስግደትና ዱዓ ምኅረትን እና በረከትን ትጠብቃለች፡፡
ምንጮች፡- ሐመረ ኖህ እና ኢስላማዊ ትሩዝ ድረ ገጽ
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleከሁለት ሚሊዮን በላይ የኀብረተሰብ ክፍሎችን በአማራጭ የኃይል ምንጭ ተጠቃሚ ማድረጉን የአማራ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ፡፡
Next article“አሁን ላይ ከመደበኛ ህክምና ባሻገር ከ10 ሺህ በላይ ዜጎች ለልብ ቀዶ ጥገና ህክምና ወረፋ እየጠበቁ ነው” ዶክተር በቀለ ዓለማየሁ