ʺጉቦ የሚሰጥ፣ ጉቦ የሚቀበል እና ሁለቱን ደላላ ኾኖ የሚያገናኝ ሦስቱም የተረገሙ ናቸው” ኡስታዝ ባሕሩ ዑመር

221

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 1/2015 ዓ.ም (አሚኮ ) በተረገመ ተግባር የገቡት ሁሉ የተረገሙ ይኾናሉ፣ ከሚያምኑት ከፈጣሪያቸው ይርቃሉ፣ ፈጣሪ ወደ አዘጋጀላቸው መልካም ሥፍራ ከመሄድ ይከለከላሉ፡፡ ሌቦች በማኅበረሰብ ዘንድ የተወገዙ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን የሚሰርቅን ያወግዛሉ፣ ከማኅበርም ይለያሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ቅንነትን፣ ታማኝነትን፣ ጀግንነትን እና መልካምነትን ያስተምራሉ፡፡

ያለው ለሌለው እንዲያካፍል ይመክራሉ፡፡ ከራስ በላይ ለሰውና ለሀገር ይኖራሉ፡፡ ታማኝነታቸው፣ ቅንነታቸው፣ አንድነታቸው፣ ከራስ በላይ ለሰውና ለሀገር መኖራቸው፣ ጀግንነታቸው እና አትንኩኝ ባይነታቸው ነው አስከብሮ ያኖራቸው፣ በጠላት ፊት ግርማ ያላበሳቸው፣ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት የሚታወቁበት በታማኝነታቸው፣ በቅንነታቸው፣ በመልካምነታቸው እና በጀግንነታቸው ነው፡፡

ኢትዮጵያዊያን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የማይመስላቸው እና የማይገልጻቸው ተግባር እየፈተናቸው ነው፡፡ ሙስና እና ሙሰኞች ሕይዎታቸውን አክብደውባቸዋል፣ ሌብነት በሚጠላባት ምድር ሌቦች አላላውስ ብለዋቸዋል፡፡ ሌብነት በሃይማኖት፣ በባሕልና በእሴት የተወገዘ ተግባር ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ክፉ ተግባርን የሚያወግዙበት ሃይማኖት፣ ባሕልና እሴት አላቸው፡፡

የሃይማኖት መምህሩ ኡስታዝ ባሕሩ ዑመር በእስልምና ሃይማኖት የሰው ልጅን ሕይዎት መጠበቅ፣ ሃይማኖትን መጠበቅ፣ ክብር መጠበቅ፣ የሰውን ገንዘብ አለመንካትና ሰውን በማንነቱ አለመንካት በጥብቅ የሚታዘዙ ናቸው ይላሉ፡፡ አንደኛው የአንደኛውን ገንዘብ ያለ አግባብ እንዲወስድ አይገባም የሚል ትዕዛዝ መኖሩንም ተናግረዋል፡፡

የሰዎችን ገንዘብ ለመውሰድ ብላችሁ ለባለስልጣናቱ የእጅ መንሻ አትስጡ እንደሚልም ገልጸዋል፡፡ ሙስና በእስልምና ሃይማኖት የተረገመ ተግባር መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ ኡስታዝ ባሕሩ ሙስናን በእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮ ሲገልፁት ʺጉቦ የሚሰጥ፣ ጉቦ የሚቀበል እና ሁለቱን ደላላ ኾኖ የሚያገናኝ ሦስቱም የተረገሙ ናቸው፣ ድርጊቱ እርጉም ነው፣ ተቀባዩም እርጉም ነው፣ ሰጭውም እርጉም ነው፣ ደላላውም ወይም አገናኙም እርጉም ነው”

የሚሰርቁ ወንድም ሴት ሌቦች ምስክር ከተገኘባቸው እና መስረቃቸው ከተረጋገጠ መቀጣጫ ይኾኑ ዘንድ በጥብቅ ይቀጡ እንደሚልም ነግረውናል፡፡ የነብዩ መሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ልጅ እንኳን ቢሰርቅ ሊቀጣ እንደሚገባ በጥብቅ ማስተማራቸውንም ገልጸዋል፡፡ ሙስና በምንም ዓይነት መልኩ ተቀባይነት የሌለው የተረገመና የተወገዘ ተግባር መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

ሙስና ባሕል እስኪመስል ድረስ በመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማትና በሌሎች ተቋማት እየተዘወተረ መምጣቱን የተናገሩት ኡስታዝ ባሕሩ እንደ ቋሚ ሥራ አድርገው የሚሠሩ መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡ ሙስና በሃይማኖት የከፋ ሐጥያት መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ሰዎች እየተላመዱት ሲሄዱ ሐጥያትን እያቀለሉ እንደሚሄዱም ነው ያስረዱት፡፡

የአለፈው ሥርዓት ሙስናን በኢትዮጵያ አስፋፍቶታል ብለው እንደሚያምኑም ኡስታዝ ባሕሩ ተናግረዋል፡፡ ፖለቲከኞች ሌሎችን የራሳቸው ባሪያ ለማድረግ ሲፈልጉ በሙስና ውስጥ እንደሚዘፍቋቸው የተናገሩት ኡስታዝ ባሕሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሉኝታ የሚይዘው፣ ይሄስ ግፍ ነው የሚል ነበር፣ ከይሉኝታ እያወጡት የሄዱት መሪዎች ናቸው ነው የሚሉት፡፡ ሰዎች በሙስና ከተዘፈቁ ለአለቆቻቸው አሽከር ኾነው እንደሚኖሩም ገልጸዋል፡፡ አለቆችም ታዛዥ አሽከሮች እንዲበዙላቸው በሙስና እንደሚያስሯቸው ነው የተናገሩት፡፡

ሰዎች ከይሉኝታ እና ከሃይማኖት ትዕዛዛት እየራቁ ባልተገባ ተግባር ውስጥ እየገቡ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶች እንደዬ ሃይማኖታቸው ድርጊቱን ማውገዝና ማስተማር እንደሚገባቸውም ተናግረዋል፡፡ ሌብነት በሞራል ብቻ የሚቆም ባለመኾኑ መንግሥትም ተግባራዊ የኾኑ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባው ነው የተናገሩት፡፡ መንግሥት ጥብቅ የኾነ እርምጃ ሲወስድ ሌቦች እጆቻቸውን እንደሚሰበስቡና እንደሚያፍሩም ገልጸዋል፡፡

የሃይማኖት ሀገር ናት በምትባለው ኢትዮጵያ በሙስና ያልተገባ ነገር ማድረግ ነውር ነውም ብለዋል፡፡ ሁሉም ራሱን መፈለግና ወደ ፈጣሪው መቅረብ እንደሚገባውም አመላክተዋል፡፡ ራስን መቆጠብና ሌሎችንም ማስተማር ይገባልም ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
ዲስከቨር አማራ አሚኮ https://www.facebook.com/DiscoverAmharaAMECO
አሚኮ ስፖርት https://www.facebook.com/AMECOSport
አሚኮ መረጃ ማጣሪያ https://www.facebook.com/AMECOFactCheck

Previous article“የሰረቁት እና ያልተገባቸውን የሻቱት ሁሉ ወድቀዋል” ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መልአክ
Next articleየሴቶች ጥቃትን ለመከላከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕጎችን በማሻሻል በወንጀለኞች ላይ እርምጃውን ማጠናከር እንዳለበት ተገለጸ።