“የሰረቁት እና ያልተገባቸውን የሻቱት ሁሉ ወድቀዋል” ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መልአክ

290

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 1/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ትዕዛዛትን ያላከበሩት ከአለቅነት ወደ ሎሌነት ወርደዋል፣ ትዕዛዛትን ያላከበሩት በሰው እጅ ያልተሠራውን አብዝቶም ያማረውን የክብር ልብስ አውልቀዋል፣ በምትኩም የጠቆረውን ማቅ ለብሰዋል፣ ከብርሃን ወደ ጨለማ ተወርውረዋል፣ ተከብረው ሳለ ተዋርደዋል፣ ተከብረው ሳለ ተንቀዋል፣ ታላቆች ሳሉ የእርኩሰትን ግብር ወስደዋል፣ ከታናሽነትም ዝቅ ብለዋል።

ከትዕዛዛት ውጭ ከፍታን የመረጡት፣ ከሕግ ውጭ አለቅነትን የወደዱት ተቀጥቅጠው ወርደዋል፣ የተከበሩ ሳሉ የተናቁ ኾነዋል፡፡ ትዕዛዛትን ያላከበሩት ጨለማው በሚያስፈራ ዓለም ውስጥ ኖረዋል፣ በእሳት ጅራፍ እየተገረፉ ተሰቃይተዋል፣ ብርሃን ናፍቋቸው በጨለማ ቁርበት ተጠቅልለዋል፣ ጥልቀቱ በማይለካ ጉድጓድ ውስጥ ወድቀዋል።

ትዕዛዛትን ያከበሩት፣ አምላክ የሚወድደውን ያደረጉት ግን ከትቢያ ተነስተው በዙፋን ላይ ተቀምጠዋል፣ ከእረኝነት ወጥተው ንግሥናን ተቀብለዋል፣ በረከት ትዕዛዛትን ከሚያከብሩት ጋር ናት፣ ሰላምና ፍቅርም ትዕዛዛትን ከሚያከብሩት ጋር ናት፣ ጥበብም ትዕዛዛትን ከሚያከብሩት ጋር ናት።

በምድርም ትዕዛዛትን የማያከብሩት፣ከውሸት ወገን የኾኑት በሕዝብ ዘንድ ይናቃሉ፣ ይጠላሉ፣ ከተከበረ ማኅበርም ይርቃሉ፣ ከልጆቻቸው፣ ከወገን ዘመዶቻቸው ፊት ተዋርደው በሕግ አስከባሪዎች እየተዳፉና እየተገፉ ይወሰዳሉ፡፡ በሌቦችና በአጭበርባሪዎች ልጆቻቸው ያፍሩባቸዋል፣ ወገኖቻቸው አንገታቸውን ይደፉባቸዋል፡፡ የከበረ እሴት ባለባት በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ሌብነት ይሉት ግብር ሕዝብን አሰቃይቷል፡፡ ሙስና ይሉት ስም ወገንን አማርሯል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን የባሕርዳር ሀገረ ስብከት የአራቱ ጉባዔያት መምህር ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መልአክ ክፉ ሥራ ባለባት ምድር የእግዚአብሔር በረከት ትርቃለች ይላሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፉ አስርቱ ትዕዛዛት መካከል አትስረቅ የሚለው አንዱ ነው፣ ሌብነት በእግዚአብሔር ፊት አጸያፊ ነው፣ ሌብነት በእግዚአብሔር ፊት የተጠላች ናት ነው ያሉት ሊቁ፡፡

ሌብነት በተለያዬ መንገድ እንደሚገለጽ የሚናገሩት ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ ሌብነት የራስ ያልኾነን ነገር ወይም ገንዘብ መፈለግ ነው፣ ዲያብሎስ ሌባ ነው፣መልአክ ስለነበር ገንዘብ አይሰርቅም ነገር ግን ያልተገባውን ሻተ እንጂ፣ ይሁዳ ሌባ ነው፣ የእርሱ የገንዘብ ሌብነት ነው፣ ሌብነቱም ስግብግብነት ነው ብለውኛል፡፡ የሰረቁት እና ያልተገባቸውን የሻቱት ሁሉ ወድቀዋል፣ ተንቀዋል፣ ከተከበረው ሁሉ ርቀዋል፡፡

ለሌቦች እግዚአብሔር በረከት ይነሳቸዋል፣ ከመንግሥቱም ያርቃቸዋል፣ አዳም የተቀጣው ያልተሰጠውን እና ለእርሱ ያልተገባች ነገርን ሲያደርግ በመገኘቱ ነውም ይላሉ፡፡ ሌቦች ለራሳቸው ጥቅም ሲፈልጉ ለሌሎች ያዘኑ መስለው እንደሚሰርቁም ነግረውኛል፡፡ አስመሳይነት እና አጭበርባሪነት ሌቦች የሚጠቀሙባቸው ዜዴዎቻቸው መኾናቸውንም ሊቁ ይናገራሉ፡፡ ይሁዳ በሌብነቱ ከሀዋርያት ተነጥሏል፣ ዛሬም ድረስ ካህናት ባልተገባቸው ነገር ከተገኙ ቤተክርስቲያን ታስተምራለች፣ ትመክራለች ካልተማሩና ካልተመለሱ ግን ክህነቱን እስከመሻር ትደርሳለች ነው ያሉት፡፡

የማይሰርቅ፣ የሰው ገንዘብ የማይመኝ ካህን ሹም እንደተባለ ሌባ የኾነ ሁሉ ከክብሩ ተዋርዶ ይቀጣል፡፡ አሁን ላይ በተቋማት በእግርህ ትተህ በእጅህ ና፣ የጉዳይ ማፍጠኛ አምጣ የሚባሉ አስነዋሪ ነገሮች መኖራቸውን ወገኖች እንደሚያነሱ የተናገሩት ሊቁ ያልተገባ ክፍያ ሁሉ ሌብነት ነው ብለዋል፡፡ ሕግ ያልፈቀደውና ሕግ ያላዘዘው ሁሉ ሌብነት ነው፣ ሰውን በሰውነቱ የመርዳት ልምድ ሊኖር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ በሃይማኖት ትዕዛዛት አንደኛው አትስረቅ ነውና ሃይማኖተኛ የኾነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሃይማኖቱን ትዕዛዛት ሊያከብር ግድ ይለዋል ነው ያሉት፡፡ ትዕዛዛት ይከበሩ ዘንድም የሃይማኖት አባቶች ታላቁን ድርሻ መውሰድ አለባቸው ብለዋል፡፡

አምላክ ሌቦችን በመቅሰፍት ቀጥቷል፣ ሌቦችን ክብራቸውን ገፍፎ ያዋርዳቸዋል፣ በሌቦች ምክንያትም ሰዎች ይጠፋሉ፣ አምላክ ሌቦችን እንደሚቀጣ ሁሉ መንግሥትም ሌቦችን መቅጣትና ማስተማር አለበት ነው ያሉት ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ፡፡

ሊቁ ክፉ ሥራን ሲገልጹት ከአንድ እርሻ በአንድ ጊዜ አረምን ማጥፋት አይቻልም፣ ነገር ግን አረሙ እህሉን እንዳይጎዳው ማድረግ ይቻላል፣ ምስጥ ባለበት ሥፍራ ላይ እያወቅን ተክል እንተክላለን፣ ለምን ከተባለ ምስጡን እንከላከለዋለን ብለን ስለምናስብ ነው፣ ሕግ የሚረቅቀው አረሞችን ወይም ምስጦችን ለመከላከል ነው፡፡

መንግሥት መቅጣት ያለበትን ሕዝብ በሚያውቀው ደረጃ መቅጣት አለበት፣ ማን ማንን ይናገራል፣ ማንስ ማንን ይቀጣል፣ ከላይ እስከ ታች ድረስ አንድ ነው የሚል ሮሮ በሕዝብ ዘንድ ይሰማል፣ ይህም ከኾነ ሕዝቡ ጥቆማ ከመስጠት ይቆጠባል፣ መንግሥትም ሳይታመን በሕዝብ ዘንድ እየታማ ይኖራል፣ አለመታመንን ለማስወገድ ደግሞ የሚታይ እርምጃ መውሰድ ግድ ይላል ነው ያሉኝ፡፡

እርምጃ ሲታይ ሕዝቡ ጥቆማ ለመስጠት ይበረታልም ብለውኛል፡፡ ሌቦች እርምጃ ሲወሰድባቸው ሕዝብ ቢያይ ሕዝብና መንግሥት ይተማመናሉም ነው ያሉት፡፡ እንደ ሃይማኖት ሌብነት በምድር ሀገርንና ሕዝብን፤ በሰማይ ነብስን እንደሚጎዳ እናስተምራለን ብለዋል ሊቁ፡፡

ሰው ገንዘብ መውደድ ሲጠናወተው ከራሱ ይሰርቃል፣ ከኢትዮጵያ የሚሰርቅ ሰው ከራሱ ነው የሚሰርቀው፣ ከእናት እና ከአባቱ እየሰረቀ እንደኾነ ይወቅ፣ ከሴት ልጅ ያልተገባ ገንዘብ ከተቀበለ ከእናቱ፣ ከእህቱ እንደሠረቀ ይወቅ፣ ይረዳ፡፡ በተጨካከንን ጊዜ አምላክ ይጨክንብናል፣ አምላክ በነፃ ነው ዝናብና ፀሐይ የሚሰጠን፣ በነፃ ማገልገል እንኳን ባይቻል በሚከፈለው ብቻ መሥራት ቢቻል እግዚአብሔር ይባርከናል ነው ያሉት፡፡

ለሰውም ለእግዚአብሔርም ታማኝ ኾነን እንሥራ፣ ጌታ እንዳስተማረው በየገንዘባችን እንኑር የሊቀ ሊቃውንቱ ምክር ነው፡፡ በተከበረች ሀገር በተወደደች ምድር የተወደደውን ብቻ እናደርግ ዘንድ ግድ ይላል፡፡

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአለውሃ ወንዝ የብረት ድልድይ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር ገለጸ።
Next articleʺጉቦ የሚሰጥ፣ ጉቦ የሚቀበል እና ሁለቱን ደላላ ኾኖ የሚያገናኝ ሦስቱም የተረገሙ ናቸው” ኡስታዝ ባሕሩ ዑመር