የአለውሃ ወንዝ የብረት ድልድይ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር ገለጸ።

139

ባሕር ዳር፤ ታኅሳስ 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ከወልድያ ወደ ቆቦ በሚወስደው መንገድ ላይ የሚገኘው የአለውሃ ወንዝ የብረት ድልድይ ሥራ ተጠናቅቆ ዛሬ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

በኮንክሪት ደረጃ በጣልያኖች ተገንብቶ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ነባሩ የአለውሃ ድልድይ 102 ሜትር ርዝመት ነበረው፡፡

ጉዳቱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ትንንሽ እና መለስተኛ ተሽከርካሪዎት በኮምቦልቻ ዲስትሪክት የተሠራውን ተለዋጭ መንገድ በመጠቀም እና ወንዙን በማቋረጥ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ለከባድ ተሽከርካሪዎች ወንዙን አቋርጦ ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ መሻገር አስቸጋሪ የነበረ በመሆኑ የድልድይ ጥገናው እስከሚጠናቀቅ ድረስ ለሁለት ወራት ከዚህ ቀደም የተለመደው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ተስተጓጉሎ ቆይቷል።

በጦርነቱ ወቅት ጉዳት ደርሶበት የነበረ ሲሆን ፣ በወቅቱ 54 ነጥብ 86 ሜትር ርዝመት ያለው የብረት ድልድይ ተሰርቶለት አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

ነሐሴ 09/2014 ዓ.ም ምሽት ላይ የተፈጠረው ድንገተኛ ጎርፍ የድልድዩን ተሸካሚ ምሶሶዎች በማፍረሱ ፣ በጊዜያዊነት የተሠራው የብረት ድልድይ ላይ የመውደቅ ስጋት አስከትሎ ቆይቷል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የብሪጅ ስትራክቸር ዳይሬክቶሬት እና ኮምቦልቻ ዲስትሪክት ባለፉት ሁለት ወራት አስፈላጊውን የጥገና ቁሳቁስ ወደ ቦታው በማንቀሳቀስ ድልድዩን ሲገነቡ ቆይተዋል።

አዲሱ የብረት ድልድይ 109 ነጥብ 73 ሜትር ርዝመት ያለው ነው። የብረት ድልድይ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ላለፉት ሁለት ወራት ሌት ከቀን እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቷል።

ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት የነበረውን ድልድይ በአሁኑ ወቅት በብረት ድልድይ በመተካት በአዲስ መልኩ ተገንብቶ ከዛሬ ታኅሳስ 01 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለትራንስፖርት አገልግሎት ክፍት ሆኗል።

የብረት ድልድዩ እስከ 400 ኩንታል ወይም 40 ቶን ድረስ መሸከም የሚችል አቅም እንዲኖረው ተደርጎ የተገነባ ነው።

በዘላቂነት ሊሠራ ዲዛይኑ የተጠናቀቀው 120 ሜትር ርዝመት ያለው የኮንክሪት ድልድይ ግንባታ ለማስጀመር፤ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ከኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የተገኘው መጃ ያሳያል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተሻሻሉ የጥራጥሬ ሰብልን በማዕከላዊና በሰሜን ጎንደር ዞኖች ለአርሶ አደሮች ምርጥ ዘር በማቅረብ ምርትን ለማሳደግ እየሠራ መኾኑን የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ ።
Next article“የሰረቁት እና ያልተገባቸውን የሻቱት ሁሉ ወድቀዋል” ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መልአክ