ድንቅ ምድር- ኢትዮጵያ

130

ባሕር ዳር: ሕዳር 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የ13 ወራት የፀሐይ ብርሃን ባለፀጋ፤ የገነት ተምሳሌት፣ ከዳሎል እስከ ራስ ደጀን አስደማሚ የተፈጥሮ መልክ፤ ምድረ-ቀደምት የሰውልጆች መገኛ የድንቅነሿ-ድንቅ ሀገር፣ ድንቅ ምድር ኢትዮጵያ፡፡

ኢትዮጵያ ዘመን ያልሻረው የትውልድ አሻራ፤ ዓለምን የሚያስደምም፤ ዛሬም ድረስ የዘመኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ከደረሱበት ውጤት በላቀ ደረጃ አሻራቸው ያረፈባት ምድር ናት፡፡

የሰው ልጅ የፈጠራ ውጤቶች፣ በተለይ ደግሞ የኪነ -ሕንፃ ጠበብቶች በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡

ኢትዮጵያ ውስብስብና ከአዕምሮ በላይ የኾኑ የምህንድስና ውጤት ባለቤት መኾኗን የሚመሠክሩ የታሪክ አሻራዎች ብዙ ናቸው፡፡

አንድ ወጥ ከኾነ ድንጋይ የተፈለፈሉ 11 የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ አክሱምና የጎንደር ቤተ- መንግሥት ኪነ ሕንፃዎች ግንባር ቀደሞቹ ናቸው። ከዳሎል ዝቅታ እስከ ራስ ደጀን ከፍታም የተፈጥሮ ድንቅነትን የተቸረች ሀገር አድርጓታል፡፡ ድንቅ ተፈጥሮ፣ ውብ ምድር፣ ማራኪ ገጽታ፣ ከኢትዮጵያውያን ባሕል፣ ማኅበራዊ ክዋኔ ጋር ተዳምሮ የዓለምን ቀልብ ይስባል፡፡

በዚህም በየዓመቱ ከሁነት እስከ ተፈጥሮ አሻራን ለመጎብኘት የሚመጣው ጎብኝ ቀላል የሚባል ቁጥር አይደለም፡፡ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ሌላ ጸጋን ይቸራል፡፡

አማራ ክልል ደግሞ የበርካታ ተፈጥሮዊና ሰው ሰራሽ ድንቅ የታሪክ አሻራዎች ሁሉ መገኛ ነውና በቱሪዝሙ ዘርፍ አበረክቶው ላቅ ያለ እንደኾነ ነው የሚነገረው፡፡

እርግጥ ነው የቱሪዝም ዘርፉ ለበርካቶችም የእንጀራቸው ገመድ ነው፡፡ ጉዳዩ አምናም ታች አምናም በኮረና ወረርሽኝ፣ ከዚያም ከሁለት ዓመት በላይ የዘለቀው ጦርነት የቱሪዝሙን ዘርፍም ክፉኛ ጎድቶታልና መልሶ ለማነቃቃት ምን አስቻይ ተግባራት እየተከናወኑ ነው የሚለው ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ነው።

በጉዳዩ ላይ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው አበበ እምቢያለ እንደተናገሩት ክልሉ ያለውን ጸጋ በአግባቡ ለመጠቀም ለቱሪዝም ልማትና እድገት በትኩረት እየሠራ ነው፡፡

ቢሮው ከሚመለከታቸው አካላት ጋርም በቅንጅት እየሠራ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
የጎብኝዎችን ፍላጎት የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠትም ዝግጁ መኾናቸውን የደባርቅ ከተማ ባለሆቴሎች መናገራቸውና በጦርነት ምክንያት ስጋት የነበሩ አካባቢዎች በተፈጠረው ሰላም መነቃቃት መጀመሩን አሚኮ ከስፍራው ያደረሳቸው ዘገባዎች ያሳያሉ።

የሰሜን ጎንደር ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ወይዘሮ አስራት ክብረት ለአሚኮ በሰጡት መረጃ አሁን ላይ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ወደ ዞኑ እየመጡ መኾኑን ጠቅሰዋል።

የጎብኝዎች ቁጥር የበለጠ እንዲጨምር ወደ አካባቢው የሚመጡ ቱሪስቶችን እንደ አምባሳደር በመጠቀም መዳረሻ ቦታዎችን የማስተዋወቅ እና አካባቢው ሰላም ስለመኾኑ የማረጋገጥ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል። ለዚኽም ቱሪስቶች ከቅርሶች በተጨማሪ በዞኑ የሕዝቡን መልካም እሴት ጭምር እንዲያውቁ ይደረጋል ነው ያሉት።

የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አበበ በክሉ የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ዘርፍ መልሶ ለማነቃቃት የተለያዩ መርኃግብሮች ተዘጋጅተው ተግባራዊ እየተደረጉ መኾኑንም ነው ለአሚኮ የተናገሩት፡፡

በክልሉ በጦርነት ምክንያት የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ዘርፍ መልሶ ለማነቃቃት አስቻይ እቅዶችና እንቅስቃሴዎች አሉ ባይ ናቸው፡፡

ጦርነት ላይ እንደቆየ ክልል ከገቢው ባሻገር-ቱሪዝሙ መልሶ እንዲያገግም የማነቃቃት ሥራ መሥራት ቀዳሚው ጉዳይ ነው ያሉት አቶ አበበ።

በተላይም ይላሉ የሀገር ውስጥ ቱሪስት ላይ የበለጠ ለመሥራት ታቅዷል፤ በበጀት ዓመቱ ከ53ሺህ 87 በላይ የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን ለማስተናገድ የታቀደ ሲኾን በአንፃሩ ደግሞ 128 ሚሊዮን 136 ሺህ 02 የሀገር ውስጥ ቱሪስት ለማስተናገድ ታቅዷል ነው ያሉት አቶ አበበ፡፡

በዚህም ከውጭ ሀገር ቱሪስት 90 ሚሊዮን 905 ሺህ 380 ብር፤ ከሀገር ውስጥ ደግሞ 2 ቢሊዮን 689 ሚሊዮን 804 ሺህ 382 ብር ገቢ ለመሰብስብ እንደታቀደ ነው የተናገሩት፡፡

ታዲያ የተጠቀሰውን የቱርስት ፍሰት ለማስተናገድ እና የታቀደውን ገቢ ለመሰብሰብ አስቻይ መርኃግብሮች ተዘጋጅተዋል ተብሏል፡፡

👉የቱሪዝም ንቅናቄው መርኃግብሮች፡-
ቱሪዝም አዋርድ (የቱሪዝም ሽልማት) የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃት “ወይዘሪት ቱሪዝም” ቆነጃጂቶችን ማወዳደር በሁሉም ዞኖች እየተከናወነ ነው ተብሏል፡፡ በክልል ደረጃ በታሕሣሥ/2015 ዓ.ም በባሕር ርዳር ይካሔዳል ነው የተባለው፡፡

👉እውቅናና ምስጋና፡-በኪነጥበብና በእደ ጥበቡ ዘርፍ ለቱሪዝሙ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላት እውቅና እና ሽልማት የሚበረከትላቸው ይኾናል ተብሏል፡፡ በዚኽም ከግለሰብ እስከ ቡድንና ተቋም እውቅናና ምስጋና ይቸራቸዋል።

👉ሁነት ዝግጅት፡- ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ ባዕላትን ለቱሪዝም በመጠቀም ሁነቶችን አዘጋጅቶ ንቅናቄ መፍጠር ከታሕሣሥ/2015 ዓ.ም ጀምሮ የገና በዓልን በላሊበላ፣ ጥምቀትን ከጎንደር እስከ ኢራንቡቲ፣ ጥር 13 -የጊዎን በዓል በሰከላ የታላቁን ወንዝ አባይ መነሻ፣ ጥር 21 የአስተርዮ በዓል መርጦ ለማሪያምና ግሸን ደብረከርቤ ላይ፣ ጥር 23 -የአገው ፈረሰኞች በዓል፣ ጥር 25- የመርቆሪዎስ በዓል በአጅባር ሜዳ -ደብረታቦር እና ሌሎችንም ዝግጅቶች በተጠና እቅድ ይከናወናሉ ነው የተባለው፡፡

የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አቶ አበበ የአማራ ክልል በዋናነት ሁለት የቱሪስት ፍሰት መስመሮች አሉት ይላሉ፡፡ አንደኛው የምዕራብ አማራ የቱሪዝም መስመር ሲኾን ከአዲስ አበባ ደጀን፣ ማርቆስ፣ ፍኖተሰላም፣ እንጂባራ፣ መርጦለማሪያም፣ ባሕርዳር ጢስ አባይ፣ ጎርጎራ፣ ጎንደር የሰሜን ብሔራዊ ፓርክን የሚያዳርስ ነው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ምሥራቅ አማራ የቱሪዝም መስመር ነው፡፡ ይኽም ከአዲስ አበባ፣ ደብረብርሃን፣ ከሚሴ፣ ኮንቦልቻ፣ ደሴ፣ ወልዲያ፣ ቆቦ፣ ላሊበላ፣ ሰቆጣን ይዞ የሚያካልል መስመር ነው ብለዋል።

በእነዚህ ዙሪያ ሁሉ ታይተው የማይጠገቡ የታሪክ አሻራዎች፣ የተፈጥሮ ጸጋዎች ሁሉ ያሉበት በመኾኑ ሁሉም እንዲጎበኛቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ለቱሪስቶች ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማልማት፣ መሰረተልማቶችን መገንባት፣ አሰተማማኝ ሰላምና ጸጥታ ማስፈን፣ የቱሪስቱን ቆይታ የሚያራዝሙ ምክንያቶች በመኾናቸው የሚመለከተው ሁሉ በትኩረት መሥራት እንደሚገባው ነው የተናገሩት።

ቢሮው ከሚመለከታቸው አካላት ጋርም በቅንጅት እየሠራ ስለመኾኑም ተናግረዋል።

ቱሪዝም ከመንግሥት እስከ አካባቢው ማኅበረሰብ ድረስ ተሳትፎን የሚጠይቅ ነው። መልካም መስተንግዶ፣ መልካም አገልግሎት መስጠት ይጠበቃልም ነው ያሉት። አስጎብኝ ማኅበራት፣ የትራንስፖርት አገልገሎት ሰጭዎችና የሰላም አስከባሪ አካላት ቀና አገልገሎትን በመስጠት በጋራ እንሥራ ሲሉም አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡- ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleመንግሥት በንፁሃን ላይ የሚደረግን ጥቃት እንዲያስቆም ፓርቲዎች ጠየቁ፡፡
Next articleአሸባሪው የሸኔ ቡድን በንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃቶችን እየፈፀመ እንደሚገኝና መንግሥት ሕግን እንደሚያስከብር የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት አስታወቁ፡፡