
ባሕር ዳር: ጥቅምት 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ለታታሪና ምሥጉን ሠራተኞቹ ዕውቅና ሰጥቷል።
በዕውቅና ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ግርማ የሽጥላ፥ “አሚኮ ታላቅ ራዕይ ያለው ለኅብረተሰብ ለውጥ የሚተጋ ታላቅ ተቋም ነው” ብለዋል።
አሚኮ በ2014 ዓ.ም በተለያዩ መስኮች ላስመዘገበው ድል ምሥጋና ይገባዋል ብለዋል። አሚኮ ክብረ ወሰን የሰበረ ሥራ መሥራቱንም ገልጸዋል።
አሚኮ ብቁ ሙያተኞች ያሉበት ተቋም መሆኑንም አንስተዋል። ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን ስንል በገጠርና በከተማ የተለወጠ ከድህነት የወጣ ሕዝብ ማየት መፈለግ ነውም ብለዋል። መሪ ሐሳቡን እውን ለማድረግ አድካሚ ሥራዎች እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።
አማራ እንዳይረጋጋ ለማድረግ በዙሪያው እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት አቶ ግርማ ችግሩን አልፎና በድል ተወጥቶ ለጥቁር ሕዝብ ያበረከተውን አሰተዋጽኦ ለማየት ብቁ መሪዎች ያስፈልጋሉ ነው ያሉት። ወደፊት ያለው የትግል አውድ ከእስካሁኑ ከፍ ያለ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑንም ገልጸዋል። ጦርነት የከፈቱብንን በጦርነት ማሸነፍ ብቻ በቂ አይደለምም ብለዋል። ትልቁ ድል የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲኖር ማድረግና በአስተሳሰብም ማሸነፍ መሆኑንም አንስተዋል።
“በጠላቶቻችን እንዳንደፈር ጠንካራ ምጣኔ ሀብትና ጠንካራ ሠራዊት መገንባት ይባናል” ብለዋል። ዘመኑ የሚጠይቀው ጠንካራ ምጣኔ ሀብትና ጠንካራ ሠራዊት መገንባት እንደሆነም ገልጸዋል። በየግንባሩና በየአውዱ ብቁ አርበኞች ያስፈልጉናልም ብለዋል። አርበኝነት በጦር ሜዳ ብቻ ሳይሆን በየመስኩ ብቁ ተግባር መፈጸምና አርዓያ ሆኖ መገኘት መሆኑንም ተናግረዋል።
በደምና በአጥንት ተከብራ እንድትኖር የምንፈልጋት ሀገር በፅናት እንድትኖር ተቋማዊ አደራን መቀበል እንደሚገባም አሳስበዋል። በጠላቶቻችን ላይ የምንቀዳጀውን ድል በመሃል ሀገር በልማት መድገም ይገባናልም ብለዋል።
ብልሃት፣ ጥበብ፣ ትዕግሥት እና የአባቶቻችን የጀግንነት ታሪክ በመያዝ ለመፍትሔ መሥራት ይገባናል ነው ያሉት አቶ ግርማ።
ብርቱ ሕዝቦችና እየበዛን የምንሄድ መሆናችን በሥራችን ማሳየት አለብንም ብለዋል። የሚዲያ ባለሙያዎች ሕዝብን ከፍ የሚያደርጉ ሥራዎችን እንዲሠሩም አሳስበዋል።
አካታች የሆነው የምክክር ኮሚሽን የታለመለትን ዓላማ እንዲመታ ሚዲያው በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል። አውዳሚ ከሆነ ፉክክር ወጥቶ ተግባብቶ መሥራት አሁን የሚጠበቅ ጉዳይ እንደሆነም አንስተዋል። ለዚህ ደግሞ የሚዲያ ባለሙያዎች በትኩረት መሥራት መቻል አለባቸው ነው ያሉት።
እውነትን አጥብቆ በመሥራት ኢትዮጵያ ከፍ እንድትል የሚሠራ ጋዜጠኛ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። አሁን የገጠመን ችግር ጊዜያዊ ነው ያሉት አቶ ግርማ በአርበኝነት ሜዳው ላይ ተገቢውን ሥራ ሠርቶ ከፍ ማለት ይገባል ነው ያሉት።
አሚኮ የአማራ፣ የመላው የኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያን ወክሎ በምሥራቅ አፍሪካ የሚታይ ሚዲያ ነው ያሉት አቶ ግርማ ለለውጥ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል። ቦርዱ ለሚዲያው እድገት በትኩረት እንደሚሠራም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለሀገር ክብር በትግል እናብር
