
ጥቅምት 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የመከላከያ ሰራዊት ቀን ነገ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ ይውላል።
ቀኑን አስመልክቶ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ባስተላለፈው መልዕክት “የጥንካሬያችን ምንጭ ሕዝባችን ነው” ሲል ገልጿል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል:-
ሀገራችንና ተቋማችን የጀመሩት የሰራዊት ግንባታ አቅጣጫ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅነት የሚመጥን በቀጣናው ላለብን ከፍተኛ ኃላፊነት ብቁ የሆነ፣ የሕዝብ አሜነታን የተጎናፀፈ፣ ወታደራዊ ዕውቀትና ክህሎትን የጨበጠ፣ በፈጠረው አስተማማኝ ዝግጁነት ጦርንትን በሩቁ ማስቀረት የሚችል፣ በዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተገቢውን ሚና የሚጫወት ኃይል የመፍጠር ራዕያችን ሲሆን ተቋማችን መከላከያም ይህንን ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት በብቃት እየተወጣው ይገኛል፡፡
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሰራዊት ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አብራክ የወጣ ለሕዝብ ደኅንነትና ለሀገር ሉዓላዊነት የአካልና የህይወት መስዋእትነት የሚከፍል ብሔራዊ ኃይል ነው፡፡ ይህ የሕዝብ ልጅ የሆነው ሰራዊታችን ከሕዝቡ ጋር ያለውን ትስስርና አንድነት ለማጠናከርና የሕዝቡን የባለቤትነት ስሜት ይበልጥ እንዲጎለብት ለማድረግ የሰራዊት ቀን ትልቅ መድረክ ሆኖ ያገለግላል፡፡
የሕዝብን ደኅንነት ለማረጋገጥ እና የሀገራችንን አንድነት ለማስቀጠል ሰራዊታችን በተለያዩ ጊዜያት ከውስጥ እና ከውጪ ጠላቶቻችን ጋር ያደረገውን ተጋድሎና የከፈለውን አኩሪ መስዋእትነት እንዲገነዘብና ለዚህ ታላቅ መሰዋእትነት ዕውቅና በመስጠት በክብር እንዲዘክረው ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ዕለቱን ማክበር ፋይዳው የጎላ ነው፡፡

የሀገራችን የሰራዊት ቀን አከባበር እንደሌሎች ሀገራት ረዥም እድሜ ባይኖረውም ከኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የሰራዊት ቀን ለማክበር ሙከራዎች እንደነበሩ ታሪክ ይነግረናል፡፡
ኢትዮጵያ በዘመናዊ ሰራዊት ግንባታ ታሪክ ከአክሱም ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የራሷን ሰራዊት ለመገንባት ብዙ ርቀትን የተጓዘች ሲሆን በተለይ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ብሔራዊ ጦር ለመገንባት መሠረት የተጣለበት ወቅት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በዘመናዊ ሰራዊት ግንባታ ሂደት ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረ ታሪክ ቢኖራትም በባለፈው ሥርዓት የኢትዮጵያ የዘመናዊ ሰራዊት ባለቤትነት ተረስቶ ኢትዮጵያ የካቲት 7 ቀን 1987 ዓ.ም ሰራዊት እንደመሰረተች ተቆጥሮ ቀኑ ሲታሰብ ቆይቷል፡፡
የኢትዮጵያን የሰራዊት ግንባታ ታሪክ ወደኋላ ተመልሶ በመመልከትና የታሪክ ሰነዶችን በመዳሰስ ኢትዮጵያ በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅምት 15/1900 ዓ.ም የጦር ሚኒስቴር በመሾም ሰራዊቱ በአዋጅ እንዲቋቋም አድርገዋል፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በየዘመኑ የነበሩ ሥርዓቶች ቢቀያየሩም ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ ሰራዊት ባለቤት ሆና መቀጠሏ ግን በታሪክ የተረጋገጠ ሃቅ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የራሷን ሰራዊት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ያቋቋመችበትን ጥቅምት 15/1900 ዓ.ም መነሻ በማድረግ በየዓመቱ ጥቅምት 15 ቀን የሠራዊት ቀን ሆኖ እንዲከበር ተወስኗል፡፡ ስለሆነም ከዚህ ዓመት ጀምሮ ጥቅምት 15 ቀን የሰራዊታችን ቀን ሆኖ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
የዘንድሮውን ታሪካዊ በዓል የምናከብረው ኅልውናችንን ለማስጠበቅ ተገደን የገባንበትን ጦርነት አብርን ለሺህ ዘመናት የኖርንባትን ኢትዮጵያ ከነ ሙሉ ክብሯ ለማስቀጠል አያሌ መስዋእትነቶች በጋራ የከፈልን፣ የተዋለድን፣ ተመሳሳይ ሥነ-ልቦና አለን ብልን የምናምን፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት፣ የባህልና የእሴት መስተጋብር ያለን ወንድማማች የሆን አንድ ሕዝብ መካከል በከሃዲ አሜከላዎች/በአሸባሪው የህወሓት ቡድን/ አማካኝነት ደም ተቃብተን እንደ ሀገር የታሪካችን ጥቁር ጠባሳ የሆነው አሰከፊ ጦርነት ውስጥ ሆነን ነው፡፡
የታሪካዊ ጠላቶቻችን ፈረስ በሆነው የህወሓት አሸባሪ ቡድን ጦረኝነት ተሽቀንጥሮ ተጥሎብን በፍፁም በማንፈልገው ጦርነት ውስጥ ተገደን ገብተናል፡፡ የኅልውና እና የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ሆኖብን እንጂ ለእንደኛ አይነት ጥቅሙንና ጉዳቱን በሚገባ ለሚረዳ ደሃ ሀገር ጦርነት በፍፁም አስፈላጊ አልነበረም፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ የውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን በአቅራቢያችን ካሉ ሀገራትና ከውስጥ ተላላኪ ባንዳዎች የተላላኪነት ይሁንታን ስላልተነፈጉና ከተደጋጋሚ የክህደት አባዜአቸው ሊፋቱ ስላልቻሉ ጦርነትን አጥብቀን ያለመሻታችን ሊሰምርልን አልቻለም፡፡
ጀግናው ሰራዊታችን አሸባሪው የህወሓት ጁንታ ከአንዴም ሦስቴ በጠብ አጫሪነቱ አባዜ የሰነዘረበትን ውጊያ መክቶ ድል በማስመዝገብ አስተማማኝ የሕዝብና የሀገር አለኝታነቱን አረጋግጧል፡፡
ሰራዊታችን የኢትዮጵያን ኅልውና፣ ሉዓላዊነት፣ የብሔራዊ ጥቅምና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ በወደር የለሽ ጀግንነት በሚከፍለው መስዋእትነት በድል ላይ እየተረማመደ ወደ ግቡ እየተቃረበ ነው። እያስመዘገበ ያለው ድል ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖረው፣ አስተማማኝና ዘላቂ እንዲሆን ከመቼውም ጊዜ በላይ በከፍተኛ ጥንቃቄ እየሠራ ነው፡፡
የሰራዊታችን የአሸናፊነት ሥነ-ልቦና ከፍታና የድል ምንጩ ጠንካራውና ነጻነቱንና ብሔራዊ ክብሩን አሳልፎ የማይሰጠው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ ከደጀን እስከ ግንባር የሕዝባችን የማይነጥፍ አጋርነትና ድጋፍ ምክንያቱ ጦርነቱ በአጭር ጊዜ ተቋጭቶ ሰላም፣ ልማት፣ እድገትና ብልጽግናችን እንዲቀጥል ያለው እጅግ ከፍተኛ መሻት ነው፡፡
ሕዝባችን ይህን ጦርነት በአጭር ጊዜ በድል አጠናቆ በሙሉ አቅሙና ቀልቡ ወደ ሰላምና ልማት እንዲገባ አጥብቆ ይፈልጋል፡፡
ሕዝባችን በታሪኩ ለዘመናት ያካሄዳቸው ጦርነቶች ነጻነትና ክብሩን ያስጠበቁ ቢሆንም በተቃራኒው ደግሞ እድገትና ብልጽግናውን የኋልዮሽ ጎትተው የዓለም ጭራ አድርጎት ዛሬም የብሔራዊ ደኅንነቱ አደጋ ድህነቱና ኋላ ቀርነቱ እንደሆነ በውል ይረዳል፡፡
የሕዝብና መንግሥታችን ከፍተኛ ፍላጎት የሆነውን የጦርነቱን ጊዜ እጅግ አጭር ማድረግ እና በአስተማማኝ ብሎም በዘላቂ ድል መቋጨትን እውን ማድረግ የግድ ይለናል፡፡ ስለዚህም ከመቸውም ጊዜና ሁኔታ የላቀ ሁለንተናዊ አፈጻጸም ማለትም እጅግ ለላቀ ድልና ስኬት የሚጠይቀንን ዋጋ ወይም መስዋእትነት ሁሉ በጀግንነትና ቆራጥነት በመክፈል ታሪክ ሠርተን ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሸጋገር ወቅቱና ሁኔታው ከእኛ የሚጠብቀው ግዴታ ነው፡፡ ይህን የማድረግ ልምድ፣ ችሎታ፣ አቅምና ታሪካዊ ኃላፊነት ያለው እኛ ጋር ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም እንደ እድል ሆኖ ይህ በታሪክ አጋጣሚ በእኛ ላይ የወደቀውን ኃላፊነት በሕዝብና መንግሥታችን ፍላጎት ልክ ለመፈጸም የሚጠይቀውን ሁሉ መስዋእትነት በመክፈል ሕዝብና መንግሥታችን የለመዱትን ደማቅ ድል አስመዝግበን ልናኮራቸው ይገባል፡፡ ለዚህም ከእኔ ካንቺ ከሁላችን እንደ ግለሰብ፣ የጦር ክፍልና እንደ ተቋም በሁሉም ተግባር የድልና ስኬት ምክንያት ብቻ የሆነውን መስዋእትነት በቁርጠኝነት በመክፈል ታሪካዊ ኃላፊነታችንን እንወጣለን፡፡
“ዘላቂና አስተማማኝ ድል በሰራዊታችን አኩሪ መስዋእትነት ይረጋገጣል!!”
ለሀገር ክብር በትግል እናብር !!