
ተገቢ ያልኾነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን የሚቆጣጠር ጠንካራ ተቋም ሊኖር እንደሚገባም አመላክተዋል።
የካቲት 30/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የምጣኔ ሀብት ባለሙያ አማንይሁን ረዳ እንደገለፁት ዓለም አቀፍ የዋጋ ንረት ጫናን በዘላቂነት መቋቋም የሚቻለው በሀገር ውስጥ ገበያ ለምግብ ፍጆታና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚኾን የተትረፈረፈ የግብርና ምርት ሲኖር ነው። በገበያው ውስጥ የተትረፈረፈ ምርት እንዲኖርም መንግሥት የግብርናን ምርታማነት በማሳደግ ረገድ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት ብለዋል።
መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት አሁንም ይበልጥ ማሳደግ ይኖርበታል ያሉት አቶ አማንይሁን፤ በግብርናም ኾነ በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ የሚስተዋለውን ዓለም አቀፍ የዋጋ ንረት በዘላቂነት ለመቋቋም የሚቻለው በሀገር ውስጥ ገበያ የተትረፈረፈ የግብርና ምርት ሲኖር እንደኾነ አስረድተዋል።
ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ጥሬ እቃና ለሸማቹ ማኅበረሰብ የምግብ ፍጆታ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ ለማድረግ የግብርና ምርታማነትን በእጅጉ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡ የመስኖ ልማትን ከማስፋፋት ጎን ለጎን አርሶ አደሩ ምርታማ እንዲኾን ግብርናውን በየጊዜው ማዘመን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ባንኮች ለግብርናው ዘርፍ የሚመድቡትን የብድር መጠን በማሳደግ፣ በግብርናው ዘርፍ ላይ የሚሰማሩ ባለሀብቶች እንዲበረታቱና የታክስ ማበረታቻ በመስጠት ችግሩን በዘላቂነት መቅረፍ እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ጠቁመዋል።
ኢንዱስትሪዎች ጥሬ ዕቃና ሸማቹ ማኅበረሰብ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያገኙበትን የገበያ ሥርዓት እንዲፈጠር ለማድረግም ምርታማነትን ማሳደግ መፍትሔ መኾኑን ጠቅሰዋል።
እንደ አቶ አማንይሁን ገለፃ፣ 80 በመቶ የሀገሪቱ አርሶ አደር በግብርናው ዘርፍ የተሰማራ ነው። ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልከው ምርት 70 በመቶ የሚኾነው የግብርና ውጤት በመኾኑ ለዘርፉ ተገቢውን ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የአፍሪካና የእስያ ታዳጊ ሀገራት ባለፉት 30ና 40 ዓመታት ለግብርና ዘርፉ ትኩረት በመስጠታቸው በርካታ ለውጦችን እንዳስመዘገቡ ጠቅሰዋል፡፡ ኢትዮጵያም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ የመጣውን ዓለም አቀፉን ዋጋ ጭማሪ ለመቋቋም የግብርናውን ዘርፍ በተገቢው መንገድ መደገፍና ማሳደግ ይኖርባታል ብለዋል።
ኢንዱስትሪው በቂ ጥሬ ዕቃ አግኝቶ መሠረታዊ የኾኑ የፍጆታ ምርቶችን እንዲያመርት በማድረግ የተስተካከለና ጤናማ የኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከሰሞኑ በሩሲያና ዩክሬን መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት የዓለም የነዳጅ ዋጋ 25 በመቶ መጨመሩን ገልጸዋል። የድፍድፍ ዘይት ዋጋ 95 በመቶ ማደጉና የማጓጓዣ ዋጋ እስከ 400 በመቶ መጨመሩ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት መሠረታዊ ፍጆታዎች ዋጋ መናር ሌላኛው ምክንያት መኾኑን ተናግረዋል።
የዶላር ዋጋ ምንዛሪ መጨመርና በተለያዩ ምክንያቶች ለባለሀብቱ የሚደረጉ ድጎማዎች በዶላር እጥረት ምክንያት መቀነሳቸው ተደራራቢ የኾነ የዋጋ ንረት ሊያስከትል እንደሚችል ጠቁመው እነዚህ እና ሌሎች ምክንያቶች በዓለም አቀፍ ደረጃና በኢትዮጵያ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ማስከተላቸውን ጠቅሰዋል።
በቂ የኾነ የምርት አቅርቦት በገበያ ውስጥ አለመኖሩ፣ ምርትን ከውጭ ለማስገባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት በመኖሩ የሚቀርበው ምርት የኅብረተሰቡን ፍላጎትና አቅም ያላገናዘበ ችግር ነው ብለዋል።
ወቅትን እየጠበቀ የሚስተዋሉ ተገቢ ያልኾኑ የዋጋ ጭማሪዎች ለማስወገድም ገበያውን የሚቆጣጠር አቅም ያለው የመንግሥት ተቋም እንደሚያስፈልግም መግለጻቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/