“ማማው ደብረ ታቦር ታላቁ ታላቁ አይታጠፍ ቃሉ አይፈታም ትጥቁ”

177

ባሕር ዳር፡ ጥር 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጀግና እንደ ምንጭ ውኃ ይፈልቅበታል፣ ልበ ሙሉ ይፈጠርበታል፣ ፅኑ እመነት ያለው ይወለድበታል፣ ያድግበታል፣ አድጎም ይኖርበታል፡፡ የቴዎድሮስ ራዕይ ሲበራ የታየበት፣ የገብርዬ ታማኝነት ጸንቶ የኖረበት፣ አባ ታጠቅ ገብርዮን አስከትሎ፣ ተዋበችን በጎኑ አድርጎ የተመላለሰባት፣ ድንኳን ጥሎ ያረፈባት፣ አንድነትን የቀመረባት፣ ግብር ያበላባት፣ የራዕዩን የማለዳ ብርሃን የፈነጠቀባት፤ መኳንንቱና መሳፍንቱ የኖሩባት፣ ንጉሡን አጅበው የተመላለሱባት፣ ሊቃውንቱ ጥበባቸውን ያፈሰሱባት፣ ከታሪክ ላይ ታሪክ የተደራረበላት ምድር፡፡

ወዳጅና ጠላቱ፣ ታናሽና ታላቁ፣ መኳንንቱና መሳፍንቱ፣ ገበሬውና ሊቃውንቱ ቴዎድሮስ! ቴዎድሮስ! እያሉ የጠሩት፣ ኃያላን ነን ያሉት በአሻገር የፈሩት፣ መከራና ክፉ ቀን የማይበግሩት፣ ገብርዬ፣ ገልሞ፣ ዓለሜን የመሳሰሉ ታማኝ የጦር አበጋዞች የነበሩት፣ ጠላቶች የሚፈሩት፣ ወዳጆች ስሙን ጠርተው የማይጠግቡት፣ የተዋበች ባለቤት፣ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት፣ ፍርሃት ያልፈጠረበት፣ ክንዱ እሳት፣ የሀገርን ክብር ጠባቂ፣ የላላውን አጥባቂ ኃያሉ ቴዎድሮስ የነበረባት ቀደምቷ ከተማ፡፡

በአድባራቱና አብያተክርስቲያናቱ ክብርና ሞገስ በክብር የሚኖሩ፣ በሠንደቃቸው የሚኮሩ፣ ለሀገር አንድነት ያለ ድካም የሚሠሩ፣ ለጠላት የማይበገሩ ጀግኖች ይኖሩባታል፡፡ ሊቃውንቱ ቅኔ ይቀኙባታል፣ የዜማ ደራሲዎች ያዜሙባታል፣ የማያውቋት ለማየት ይመኟታል፣ የሚያውቋት ባሻገር ኾነው ይናፍቋታል፣ በትዝታዋ ወጀብ እየተመቱ ይባዝኑባታል፡፡ ቀዳሚውን ኢንዱስትሪ የጀመረች፣ ሴባስቶፖልን የሠራች፣ በስልጣኔ መንገድ ለመጓዝ መንገድ የቀየሰች ከተማም ናት፡፡

ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ በወጣበት፣ ፊቱ ባበራበት፣ በእነ ጴጥሮስ ፊት በተለወጠበት፣ አስፈሪ ግርማ በታየበት፣ ግርማ መለኮቱን በገለጠበት፣ ብርሃኑን በሰጠበት፣ ሙሴንና ኤልያስን ባነጋገረበት ታለቁ ተራራ ስያሜዋን የወሰደች፣ ስሟን ከፍ አድርጋ በታሪክ መዝገብ ላይ ያሰፈረች ቀደመት ናት ደብረ ታቦር፡፡

በዘመነ አፄ ሰይፈ አርድ እንደተመሰረተች ይነገርላታል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግርማ መለኮቱን በገለጠበት ተራራ ስያሜዋን የወሰደችው ይህችው ቀደምት ከተማ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ባረፈበት ነው መሰረቷንም ያፀናችው ይባላል፡፡

ንጉሡ አጼ ሰይፈ አርድ በሀገረ እስራኤል ታቦርና አርሞን የሚባል ተራራዎች አይተው ነበር፡፡ እነዚያን ተራራዎች አይተው ፈፅመው አድንቀው፣ ተገርመውም ነበር ይባላል። ከዚያም በተመለሱ ጊዜ የኢየሱስ ቤተክርስቲያን ወዳለበት ተራራ ሠራዊታቸውን አስከትለው ወጡ፡ በተራራው አናት ላይ ወዲያና ወዲህ እየተዘዋወሩ ዙሪያ ገባውን ተመለከቱ፡፡ በመልካምድሩ አቀማመጥም ተደመሙ፡፡ አደነቁም፡፡ ይህስ የአየነውን የደብረ ታቦርን ተራራ ይመስላል አሉ፡፡ ደብረ ታቦርም ተባለች ይባላል፡፡

ምግባሯ የተመቻቸ፣ ስሟም ያማረ በታላቁ ተራራ ስም ስያሜዋን ያገኘች ድንቅ ናት ደብረታቦር፡፡ የዓድዋ እመቤት፣ የኢጣልያ ራስ ምታት፣ የኢትዮጵያውያን የድል እናት፣ ታላቋ ንግሥት፣ ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ ተወልደውባታል፡፡ እትብታቸው ተቀብሮባታል፣ ክርስትናም ተነስተውባታል፡፡ ነገሥታቱ መዳረሻ አድርገዋታል፡፡ መኳንንቱ ኖረውባታል፡፡

ከዘመናት በፊት የስልጣኔ ማዕበል ሊያጥለቀልቃት፣ የአፍሪካ ዘመናዊነት ብርሃን ሊወጣባት፣ ዘመናዊነት ሊያስጨንቃት የነበረች ባለተስፋዋ ከተማ ከአድማስ ባሻገር ያለውን የማለዳ ጀንበር ገልጦ ሊያሳያት የነበረውን ስታጣ አብዝታ አዝና ነበር። በእግርጥ ጀግነዋን ዛሬም አትረሳውም፡፡ ከአፏ አትለየውም። ቴዎድሮስ! ቴዎድሮስ! እያለች ትጠራዋለች፡፡ የእርሱን ራዕይ እውን ለማድረግ ትጥራለች፡፡
የኢትዮጵያዊነት፣ የአንድነት፣ የአሸናፊነት እምነቷን ያላጎደለችው፣ ከጀግንነቷ ልክ ያልቀነሰችው፣ ኢትዮጵያዊነት የፀናባት፣ የዘመናዊነት ሀገር ንድፍ የተነደፈባት፣ ሃይማኖት የጸናባት፣ ፀንቶም የኖረባት ናት ደብረ ታቦር ።

በታሪኳ ጉድፍ ያልተገኘባት፣ ጀግና ብቻ የሚፈልቅባት፣ ፈሪ የማይፈጠርባት፣ ጠላት የማይረግጣት፣ ሙሽሪት የመሞሸሪያዋ ቀን ደርሷል፡፡


“ማማው ደብረ ታቦር ታላቁ ታላቁ፣
አይታጠፍ ቃሉ አይፈታም ትጥቁ” እንደተባለ ደብረ ታቦር ማማ ናት የቀደመውን ከፍ ብለው የሚያዩባት፣ አኩሪውን ታሪክ የሚመሰክሩባት፣ የስልጣኔ መሠረትን የሚያገኙባት፣ የቴዎድሮስን ዘመን የሚመለከቱባት፣ የቴዎድሮስን አሻራ የሚያገኙባት፣ የገብርዬን ዱካ የሚረግጡባት፣ ቃሉ የማይታጠፍ፣ ትጥቁ የማይፈታ ጀግና የሚኖርባት ናት ደብረ ታቦር፡፡ ያሉት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ በሚለው ብሂላቸው ቃላቸውን አያጥፉም፣ ከክብራቸው አይዛነፉም፡፡

እነሆ አጅባር ልትጨነቅ፣ ደብረታቦር በታላቅ አጀብ ልትሞሸር ነው፡፡ ካህናቱ ሊዘምሩ፣ ዲያቆናቱ ሊያመሰግኑ፣ ጥበብ ሊፈስስባት፣ እልልታና ሆታ ሊያደምቃት ቀኑ ቀርቧል፡፡ ቅዱስ መንፈስ ሊወርድባት፣ ታቦተ ሕጉ ሊባርካት፣ ጊዜው ደርሷል፡፡ ታቦተ መርቆርዮስ ከመንበሩ ሲወጣ፣ ካህናቱ ሲያሸበሽቡ፣ ወይዛዝርቱ እልል ሲሉ፣ ጎበዛዝቱ ሆ ሲሉ ምድር በደስታ ልትመላ፣ ሰማይ በምድር እየሆነ ያለውን ምስጋና ልታይ ነው፡፡ እልልታና ሆታው ከዳር እስከ ዳር ሊያስተጋባ ነው፡፡ የደብረታቦር ጎዳናዎች ነጫጭ በለበሱ፣ አብዝተው በተዋቡ ምዕምን ሊሞሉ ነው፡፡

የበጌምድር ጀግኖች ፈረሶቻቸውን አስጊጠው፣ በፈረሶቻቸው ላይ በኩራት ተቀምጠው፣ ጠመንጃቸውን አሳምረው፣ በሀገርኛ ልብስ ተውበው ወደ ቀደምቷ ከተማ ይጎርፋሉ፡፡ በሀገርኛ ልብስ የተዋቡ ወይዛዝርት እንደ ማለዳ ጀንበር እየተፍለቀለቁ ከየቤቱ ይወጣሉ፣ ገና በአሻገር ሲያዩዋቸው ልብን ይሰርቃሉ፣ በውበታቸው ይጋረፋሉ፣ በትህትናቸው ቀልብን ይሰርቃሉ፡፡
ከጎራ ጎራ እየተጠራሩ ይሰባሰባሉ፣ በአንድነት ኾነው ታቦተ መርቆርዮስ ወደ አረፈበት በሆታ ይገሰግሳሉ፡፡ የልባቸው ኩራት፣ የልባቸው ሙላት አጀብ ያሰኛል።

አጅባር ተውባ እየጠበቀች ነው፣ መርቆርዮስን ልታሳደር፣ በክብሩ ልትከብር፣ በጌጡ ልታምር፡፡ ታቦተ መርቆርዮስ በታላቅ አጀብ ከመንበሩ ይወጣል፡፡ በዚያም ጊዜ ማዕዛው ልብን በሚሰርቅ እጣን አካባቢው ይታወዳል፡፡ ምድራዊ የማይመስል ድባብ አካባቢውን ይሞላዋል፡፡ የሰማይ መላእክት ክንፍና ክንፋቸውን ገጥመው፣ በበዓሉ ደስ ተሰኝተው፣ በክንፋቸው እየጋረዱ የሚሄዱ ይመስላሉ፡፡ መርቆርዮስ በታላቅ አጀብ ከደብሩ እንደወጣ ሁሉ በታላቅ አጀብ ወደ አጅባር ሜዳ ይገሰግሳል፡፡ ያን ጊዜ የደብረታቦር ጎዳናዎችን እልልታ ይሞላቸዋል፡፡ የደስታ ባሕር ይውጣቸዋል፡፡ ልብን የሚሰርቀው እጣን ያውዳቸዋል፡፡ ታቦተ ሕጉ ይባርካቸዋል፡፡

በታላቅ አጀብ አጅባርም ይደርሳል፡፡ አጅባር ትጨነቃለች፣ ቀደምቷ ከተማ በደስታ ትፈነድቃለች፣ እንግዶቿን ስሞት አፈር ስሆን እያለች ታጎርሳች፣ ታጠጣለች፣ የደከመውን ታሳርፋለች፡፡ የፈረስ ጉግሱ፣ ሽምጡ፣ አንደኛው ጀግና ከሌላኘው ልቆ ለመታዬት፣ በድል ለመወጣት የሚደረገው ትንቅንቅ አጅባርን ውብ ያደርጋታል፡፡ ነጫጭ፣ ቀያይና በልዬ ልዩ ቀለም ያሸበረቁ ፈረሶች፣ በበጌ ምድር ፈረሰኞች ጌጣጌጥ ተውበው ልክ እንደ ጌቶቻቸው ሁሉ መሸነፍ አንወድም እያሉ ከሁሉም ለመቅደም ይፋጠናሉ፡፡ ሽምጥ ይከንፋሉ፡፡ በበዓለ መርቆርዮስ ታቦቱን እያጀቡ በዚያውም ልቆ መውጣት የሚሰጠው ኩራት ከፍ ያለ ነውና እሽቅድድሙ አጀብ ነው፡፡

አጅባር እንደተጨነቀች አድራ እንደ ተጨነቀች ትውላለች፡፡ በበዓለ መርቆርዮስ አጅባርን የተመለከተ ሁሉ ንጉሡ ወደ ጦር ሜዳ ለመግባት ከፈረሰኛ ተዋጊዎቻቸው ጋር እየተመዝገዘጉ ያየ ይመስለዋል፡፡ የፈረሶቹ ፍጥነት፣ የፈረሰኞቹ ድፍረት፣ እልህና ወኔ ውብ ነውና፡፡ በዚያ ቀን ቴዎድሮስ መኳንንቱና መሳፍንቱን በግራና በቀኝ አስቀምጦ፣ የጦር አበጋዞቹን አሰልፎ፣ ከተዋበች ጋር ደምቆ የፈረስ ጉግሱን እየተመለከተ ያለ ይመስላል፡፡ ቀዳሚውን በትዝታ ለማዬት፣ ያልተበረዘውን ኢትዮጵያዊነት፣ ጀግንነት፣ አንድነትና አሸናፊነት ለመመልከት ወደ ቀደምቷ ከተማ ደብረ ታቦር ይጓዙ፡፡ በዚያች ከተማ ያልተበረዘ ባሕል እስከ ውበቱ፣ ሽንፈት የማያውቅ ጀግና እስከነ አሞቱ ይገኛል፡፡ መልካም በዓል

በታርቆ ክንዴ

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/

Previous articleየመንግስት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎትን የመረጃ ደኅንነት የሚያስጠብቅ ፖሊሲ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለጸ።
Next articleመንግሥትና ሕዝብ የሚሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃትና በድል መወጣት የሚያስችል ወታደራዊ ዝግጁነት ላይ እንደሚገኙ የምሥራቅ ዕዝ ኮር አመራሮች አረጋገጡ፡፡