
እንጅባራ፡ ጥር 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አገው ምድር ላይ ነኝ። ልምላሜ እና ደግነት ድር እና ማግ ኾነው ከተዋሃዱበት የደጋ ስር ገነት እንጅባራ ገባሁ፡፡ እንኳን ሰዎቹ ፈረሶቻቸው እንኳን በኹለት እግሮቻቸው ቆመው እና ቀሪ ኹለት እግሮቻቸውን ከፍ አድርገው “አዲናስ” እያሉ የክብር ሰላምታ ይሰጣሉ፡፡ ከመራ ተክለ ሃይማኖት የተወረሰው ጀግንነታቸው አኹንም ድረስ ወዘናው አልነጠፈም፡፡ ከቀደመ ከፍታው ያልወረደ ኢትዮጵያዊ ማንነት ከደጋማው የአገው ምድር ስር እየፈሰሰ ኢትዮጵያዊነትን ለተጠማ ኹሉ በፍቅር ያረሰርሳል፡፡
አገዎች ስለፍቅር ሲሉ ኹሉን ይችላሉ፤ የማይችሉት ነገር ቢኖር በኢትዮጵያዊነታቸው እና በሰንደቃቸው ክብር የመጣን ብቻ ነው፡፡ ሰንደቅ የደፈረን፤ ሀገር የወረረን ጠላት እንኳን ሰዎቹ ፈረሶቻቸው እንኳን አይታገሱም፡፡ ከዓድዋ እስከ ማይጨው ድረስ ዘልቀው የመጡ፤ ከጣሊያን እስከ ደርቡሽ ኢትዮጵያን ጦርነት የገጠሙ ኹሉ አገዎችን ቀርቶ ፈረሶቻቸውን እንኳን ለይተው ያውቋቸዋል፡፡ ለነገሩ አገዎች የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ፣ የመቻቻል እና በፍቅር የማሸነፍ ሚዛን ማስጠበቅ ከጥንት ጀምሮ የተካኑበት ባህሪያቸውም ነው፡፡

ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌዴሌቦ 2010 ዓ.ም ላይ ባሳተሙት እና “የኢትዮጵያ ታሪክ ከዳአማት እስከ አዲስ አበባ” በሚለው መጽሐፋቸው ከ1095 እስከ 1365 ዓ.ም በምዕራብ አውሮፓ ሀገራት እና በአፍሮ ኤዢያ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሰሜን አፍሪካ ሀገራት መካከል ለ300 ዓመታት ገደማ በዘለቀው የመስቀል ጦርነት የዛጉዌ ሥርዎ መንግሥት መሪዎች ገለልተኛ እና ፍትሐዊ አቋም በመያዝ በኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት ለዘለቀው እና ስር ለሰደደው የሃይማኖት መቻቻል እርሾ ያተረፉ በሳሎች ናቸው ብለውናል፡፡
በ1189 ዓ.ም የኢየሩሳሌምን ጥንታዊ እና ታሪካዊ ከተማ ከአውሮፓ ወራሪዎች ነጻ ያወጣው ሱልጣን ሳልሃዲን ከኢትዮጵያ አፄ መንግሥታት የቀረበለትን ጥያቄ ተቀብሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በቅድስቲቱ የኢየሩሳሌም ከተማ የአምልኮ ስፍራ እንዲኖራት ያደረጉት የዛጉዌ ነገሥታት እንደነበሩ ፕሮፌሰር ላጲሶ ገልጸዋል፡፡ አገዎች እንኳን በወንዛቸው ባሕር ማዶ ተሻግረውም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እና ሚዛን ማስጠበቅ ሥሪታቸው ነው ማለታችን ነው፡፡
ጥንታዊት ኢትዮጵያ ለዘመናት ማንነቷ ታፍሮ እና ድንበሯ ተከብሮ ለትውልድ እንድትደርስ አገዎች ከቀሪ ኢትዮጵያዊ ወንድሞቻቸው ጋር በጋራ በመኾን ውድ መስዋእትነትን ከፍለዋል፡፡ ነጻዋ ኢትዮጵያ በነጻ አልተገኘችም ካልን የአገዎቹ ፈረሶች እንኳን ውለታ አለብን ማለታችን ነው፡፡ አገዎች ፈረሶቻቸው ጫንቃ ላይ ለፍልሚያ ሲወጡ ኢትዮጵያን እና አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቃቸውን አንግበው ነበር፡፡ ለሀገራቸው እና ለወገናቸው ፍጹም ታማኝ በኾኑት አገዎች ዘንድ ፈረሶቻቸውም ለጌቶቻቸው ፍጹም ታማኞች ነበሩ፡፡
በኢትዮጵያ የመከራ እና የፈተና ዘመናት ኹሉ በታማኝነት እና በጀግንነት ከቆሙት አገዎች እግር ስር የታማኝ ፈረሶቻቸው ዱካም በላቀ ጀብዱ አብሮ መዝለቁን ታሪክ ደጋግሞ ነግሮናል፡፡ ከፈረስ ጫንቃ ላይ ዝም ብሎ አይወጣም፡፡ ፈረስም ዝም ብሎ ጫንቃውን ለእኔ ቢጤ ጋላቢ አይሰጥም፡፡ ፈረሱም ፈረሰኛውም እምቢተኞች፣ ጀግኖች እና ስልጡን ባለሙያዎች ናቸው፡፡

ፈረስ እና ፈረሰኛ በአገዎች ዘንድ የክብር እና ጀግንነት ምልክቶችም ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ ፈረሰኛ ለመባል ፈረስ፣ ኮርቻ፣ ፋርኒስ፣ ለኮ፣ ወዴላ፣ ምቹና ግላስ ለፈረሱ ያስፈልገዋል። ፈረሰኛውም አለንጋ፣ ዘንግ፣ ገንባሌ፣ ሳርያን ኮት፣ ጀበርና ያሟላል። ጦር እና ጋሻማ የአባቶቻቸው የዘመቻ መሳሪያዎች ናቸውና በአገዎች ዘንድ አብዝተው ይታወቃሉ፡፡ ጀግኖች ስለመኾናቸው አብዝቶ የሚመሰከርላቸው አገዎች ደግ እና የፍቅር ሰዎችም ናቸው ይባላል፡፡ ወዳጄ! አገው ከሰው አልፎ ለእንስሳት እንኳ ክብር ይሰጣል! በአገው ፈረሰኞች ማኅበር በዓል ላይ ለታደመ የእኔ ቢጤ እንግዳ ይህ የአገዎች ክብር አሰጣጥ በቀላሉ ይገለጥለታል፡፡
በኢትዮጵያ የጭንቅ ወቅት ዋጋ የከፈሉ ፈረሶች እና ፈረሰኞች ይኸው እስከዚህ ዘመን ድረስ በድምቀት ይዘከራሉ፤ ይታዎሳሉ፡፡

ዛሬ 82ኛው የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ዓመታዊ በዓል በእንጅባራ እየተከበረ ነው፡፡ ከተማዋ አረንጓዴ ቀለም ዘርታ፣ ቢጫ ቀለም ተቀብታ እና ቀይ ስጋጃ ዘርግታ ሰንደቅ ዓላማ ተጎናጽፋለች፡፡ ከማኅበሩ ዓመታዊ በዓል ጎን ለጎን አገውን በባህል፣ በታሪክ፣ በማንነት እና በኢትዮጵያዊነቱ ለማጥናት ይህ አጋጣሚ ውብ እድልንም ፈጥሯል፡፡ ይህንን በዓል በዓለም የሳይንስ፣ የትምሕርት እና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተሠራ ነው፡፡
ዘጋቢ፡-ታዘብ አራጋው -ከእንጅባራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ። https://ameco.bankofabyssinia.com/