
ትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አንዱ ነው። የዘርፉ ሊቃውንት እንደሚነግሩን ይህ በዓል ሰማይና መሬት የታረቁበት፣ ሰውና መላዕክት በአንድነት የዘመሩበት፣ 5 ሺህ 500 ዘመናት ሲጠበቅ የነበረው የአዳም ተስፋ የተፈጸመበት፣ የዓለም መድኃኒት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ታላቅ የደስታ ቀን ነው።
በዓሉ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው ሲሆን በኢትዮጵያም በድምቀት ከሚከበሩ ትልልቅ በዓላት አንዱ ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አከባበሩ በጥንታዊቷ ደብረ ሮሃ በዛሬዋ የቅዱስ ላልይበላ ከተማ እጅግ የላቀ፣ የደመቀ እና የተለየ ነው። የበዓሉ ድምቀት የሆኑ ምእመናን፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሊቃውንቱ በዓሉ ከመድረሱ ሳምንታት ቀደም ብለው የበረቱት በእግር፣ የደከሙት እና ከርቀት ያሉት ደግሞ በትራንስፖርት ወደ ቅድስቲቱ ከተማዋ ይደርሳሉ።
በተለይም በበዓሉ ዋዜማ በላልይበላ ከተማ ተገኝቶ ድባቡን ለተመለከተ ሰው ልዩ ግርምትን፣ አድናቆትን እና ደስታን ይፈጥራል። የሃይማኖት አባቶች እንደሚነግሩን የልደት በዓል ከሌላው አካባቢ በተለየ በላልይበላ ከተማ በድምቀት የሚከበርበት ምክንያት ደግሞ ንጉሥ እና ቅዱስ ላልይበላ የተወለደው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት የልደት ቀን በመሆኑ ነው።
በቅዱስ ላልይበላ የልደት በዓል በድምቀት ሲከበር ምዕመኑ በዋዜማው በቤተክርስቲያን ይሰበሰባሉ። ለሁለት ሰዓታት የሚቆየው የማሕሌት ሥነ ስርዓት እስከ ሚከናወን ድረስም ከአራቱም ማዕዘናት የተሰበሰቡ ምዕመናን የተለያዩ መንፈሳዊ መዝሙሮችን በመዘመር ቆይታውን ያደምቁታል። በተለይም ድንግል ማርያምን፣ ኢየሱስ ክርስቶስን እና ቅዱስ ላልይበላን የሚያወድሱ መንፈሳዊ መዝሙሮች ይዘመራሉ።
“ዐይኔ ዓለም አየ እግሬ ደርሶ፤
ዐይኔ ዓለም አየ እግሬ ደርሶ፤
የድንጋይ ወጋግራ የድንጋይ ምሰሶ።
ኧረ እንደምን አድርጎ ሠራው፤
ኧረ እንደምን አድርጎ ሠራው፤
የመጥረቢያው እንኳ እጄታ የለው።
ውስጡ አረንጓዴ ነው ባሕር፤
ውስጡ አረንጓዴ ነው ባሕር፤
ቅዱስ ላልይበላ የላስታው ደብር። …” እየተባለ ይዜማል፡፡ እንዲህ እንዲህ እየተባለ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ በእናቶች እልልታ አካባቢው ይደምቃል፡፡ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የማሕሌት ሥነ ሥርዓቱ በተለየ መልኩ ምሽት ላይ ይጀመራል። የደብረ ሮሃው የልደት በዓል የማሕሌት ሥነ ሥርዓትም የራሱ የሆነ ቀለምና ዜማ ያለው መሆኑ ነው አባቶች ሲናገሩ የሰማነው።
የማሕሌት ሥነ ሥርዓቱ በሊቀ ጳጳስ አባታዊ መሪነትና አስተባባሪነት እየተመራ መዘምራን እና ካሕናት ከቀኝና ከግራ ሆነው ተራ በተራ ሃይማኖታዊ ውዳሴውን ይከውናሉ። በማሕሌት ሥነ ሥርዓቱ ዝማሜና ሽብሸባው ልዩ ድባብ አላቸው። በከበሮ እና በፅናፅሉ ድምፅ የታጀበው የዲያቆናት፣ ካህናቱ እና ጳጳሳቱ ሕብረ ዝማሬም በዙሪያ ለሚገኙ ምዕመናን ከፍተኛ ሃሴትን ይሰጣል። በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተደረገው የቅኔ ዘረፋም በዘርፉ እውቀት ያላቸውን አባቶች ፈገግ ሲያሰኝ እና ሲያስደምም አስተውለናል፡፡
ከምሽቱ 2፡00 ጀምሮ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ዜማ ሲከናወን የነበረው የማሕሌቱ ሥነ ሥርዓት ከሌሊቱ 10፡00 ላይ ተጠናቀቀ። ከሌሊቱ 10፡00 ጀምሮ በአባቶች ቡራኬ ካህናቱ ወደ ቅዳሴ ገቡ። ሥርዓተ ቅዳሴውም ንጋት 12፡30 ላይ ተጠናቀቀ። በእነዚህ ሰዓታት ሁሉ የቤተ ማርያምን ዙሪያ የከበቡ ምዕመናን እንደቆሙ ናቸው። ሥርዓቱ አሁንም ቀጥሏል።
የልደት በዓል በሌሎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት የምሽቱ ማሕሌት ተቁሞ የሌሊቱ ቅዳሴ እንዳበቃ የበዓሉ ፍጻሜ ይሆናል። በቅዱስ ላልይበላ ግን ለየት ያለ ነው፤ ከቅዳሴው መጠናቀቅ በኋላም ሌላ እጅግ ማራኪ ትዕይንት አለ። ቀጣዩ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ቤዛ ኩሉ ይባላል።
ቤዛ ኩሉ ማለት መላዕክትና እረኞች ከላይና ከታች ሆነው የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ ሲያበስሩ የሚገልጽ ትዕይንት ነው። ጃኖ፣ ሸማ እና ካባ እንዲሁም ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናት እና ሊቃውንት ከቤተ ማርያም ዙሪያ ለቤዛ ኩሉ በሥርዓት ይሰየማሉ። በዕለቱም ሊቃውንቱ ከኰረብታው ላይና ታች ዙሪያውን በመሆን እየተቀባበሉ በመላዕክት እና በእረኞች ተምሳሌት ለኢየሱስ ክርስቶስ የተደረገውን ውዳሴ ‹‹ቤዛ ኩሉ›› ወይም ‹‹የዓለም ቤዛ ተወለደ›› እያሉ ሥርዓቱን ይከውናሉ።
የቤዛ ኩሉ ሥነ ሥርዓት ለአንድ ሰዓት ያክል በምእመናን እልልታና ጭብጨባ ታጅቦ የሚከናወን ነው። ይህ ሥነ ሥርዓት ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት በኢየሩሳሌም የተከናወነውን መንፈሳዊ ክዋኔ ወደ ኋላ ተመልሶ ያስገነዝባል። የሊቃውንት እውቀትና ጥበብም እንዲሁ ይደመጣል። ይህ ሥነ ሥርዓት ሲጠናቀቅ የበዓሉ ፍፃሜ በመሆን የሃይማኖት አባቶች፣ የክብር እንግዶች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ያስተላልፋሉ።
እንኳን አደረሳችሁ!
በአዳሙ ሽባባው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/