አሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን ለኢትዮጵያ የሕልውና ስጋት በማይሆንበት ደረጃ እስከሚደርስ የሚካሄደው ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አሳሰበ፡፡

119
ባሕርዳር፡ ሕዳር 29/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ በከፈተው ጦርነት ወረራ በፈጸመባቸው የአማራና አፋር ክልሎች ንጹሐንን በጅምላ ጨፍጭፏል፣ ሴቶችን ደፍሯል፣ የሕዝብ ሀብት ዘርፏል፤ መውሰድ ያልቻለውን ደግሞ አውድሟል ብለዋል፡፡
በክልሉ ከ2 ሚሊየን በላይ ወገኖች መፈናቀላቸውን እና ከ7 ሚሊየን በላይ ወገኖች ለረሀብ መጋለጣቸውንም ቢሮ ኀላፊው ጠቅሰዋል፡፡
እየተካሄደ ባለው ዘመቻም የወገን ጦር በአሸባሪው ቡድን እየወሰደበት ባለው እርምጃ የሽብር ቡድኑ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ እየደረሰበት መሆኑን አቶ ግዛቸው ገልጸዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ እየደረሰበት ያለውን ምት መቋቋም አለመቻሉን የገለጹት አቶ ግዛቸው የሽብር ቡድኑ ተስፋ ቆርጦ ሲመለስ ጉዳት እንዳያደርስ እና ዳግም እንዳያንሰራራ ኅብረተሰቡ ጠላትን ለመምታት ክንዱ መዛል የለበትም ነው ያሉት፡፡ ኅብረተሰቡ አካባቢውን ከምንጊዜውም በላይ ነቅቶ እንዲጠብቅ አሳስበዋል፡፡
እየተገኙ ያሉት ድሎች መነሻ እንጅ የሕልውና ዘመቻው ግብ የሽብር ቡድኑ ለኢትዮጵያ ስጋት በማይሆንበት ደረጃ ማጥፋት ነው ያሉት አቶ ግዛቸው ሕዝቡ እያደረገ ያለውን የሎጅስቲክ እና የደጀንነት ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ወጣቶች የሀገር መከላከያ ሠራዊትን እና ልዩ ኀይልን በመቀላቀል በቀጣይ የሀገራቸውን ሉዓላዊነት በማስከበር የአያት ቅድመ አያቶቻቸውን ታሪክ መድገም እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡
መንግሥት የወደመውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ሀብት የሚያጠና ቡድን አቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል፡፡
መልሶ በማቋቋምና በመገንባት ሂደቱ መላ ኢትዮጵያዊያን፣ ምሁራን፣ የንግዱ ማኅበረሰብ እና ዳያስፖራው ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ አቶ ግዛቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ባለ ዓለምየ
#መሪህን ተከተል!!
#ሀገርህን አድን!!
#ነፃነትህን አትስጥ !!
Previous articleየኢፌዴሪ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ደሲሳ በሳምንታዊ መግለጫቸው ከተናገሩት ዋና ዋና ሐሳቦች
Next article❝እየተመዘገበ ያለው ድል በኢትዮጵያ ላይ የሚነሱ ጠላቶች ተሸንፈውና ተዋርደው የሚመለሱ መሆኑን አረጋግጧል❞ አርቲስቶች