
ደባርቅ፡ ሕዳር 18/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በማይጠብሪ ግንባር ለሚገኘው የወገን ጦር ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቁም እንስሳትና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
ግንባሩ ላይ ተገኝተው ድጋፉን ያስረከቡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የወገን ጦር በሠራችሁት ጀብድ ኮርተንባችኋል ብለዋል። “ዛሬ የተገኘነው ታላቅና ታሪካዊ በኾነው የጀግናው አፄ ቴዎድሮስ ምድር ነው። እናንተ ጀግኖቻችን የአሁኑ ትውልድ የአባቶቹን ታሪክ ብቻ የሚያወራና የሚኮራ ብቻ ሳይኾን አዲስ ታሪክ የሚያስመዘግብም እንደኾነ በተግባር ሠርታችሁ ባለ ታሪክ አድርጋችሁናልና እናመሰግናለን” ብለዋል።
ወደ ግንባር ስንመጣ ታላቅ ተጋድሎ የተፈጸመበት የጭና ተራራን ተመልክተን ፈርጣማ ክንዳችሁን በጠላት ላይ እንዳሳረፋችሁበትና አኩሪ ድል እንደተገኘ ለመገንዘብ ችለናል ነው ያሉት።
ዛሬም ኾነ ነገ ኢትዮጵያን አሸናፊ የሚያደርጋት የእርስ በርስ ትብብር እንደኾነ አስረድተዋል።
አኹን በድል ላይ ድል የሚመዘገብበት ወቅት ነው፤ የድል ዜና እየተሠማ ነው ብለዋል።

“ጀግኖቻችን ክንዳችሁን በየ ግንባሩ እያሳያችሁ ኢትዮጵያ አንገቷን ቀና እንድታደርግና ነጻነቷን ጠብቃ እንድትኖር እያደረጋችሁ ነው” ብለዋል።
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል ዳግም ሕዝብን መበደልም ኾነ መዝረፍ በማይችልበት ምእራፍ ላይ ደርሷል ነው ያሉት።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሠራዊቱ ከጎን መሆኑንም ገልጸዋል።
“በቅርብ ቀን የህልውና ዘመቻውን በድል አጠናቅቀን በጋራ እጅ ለእጅ ተያይዘን የኢትዮጵያን ብሔራዊ መዝሙር በጠላት #መቃብር ላይ ቆመን እንዘምራለን” ብለዋል።

በድጋፉ ላይ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የአዲስ አበባ ሕዝብ ጠንካራ የሠራዊቱ ደጀን ነው ብለዋል። የከተማ አስተዳደሩና የሥራ ኀላፊዎች እያደረጉ የሚገኙት ድጋፍ በታሪክ ተመዝግቦ ይቀመጣል ነው ያሉት።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለአማራ ሕዝብ የጭንቅ ቀን ደራሽ መኾኑን ያነሱት አቶ አገኘሁ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለክልሉ ድጋፍ እያደረገ በመሆኑ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል።
የሰሜን ጎንደር ሕዝብ ከወገን ጦር ጋር በመኾን ጠላትን አዋርዶታል ያሉት አቶ አገኘሁ ለነፃነት ሲባል ወጣቶች መስዋእትነትን እንደከፈሉም ጠቁመዋል።
ድጋፉን የተረከቡት ኮሎኔል ንጉሤ ለውጤ በቅርቡ ጠላትን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት የሚመዘገበው ድል በተግባር ይታያል ብለዋል።
መላው ሕዝብ ከሠራዊቱ ጎን ተለይቶ አያውቅም ያሉት ኮሎኔሉ ለዚህም ምስጋና ይገባል ነው ያሉት። ከዕለት ጉርሱ ቀንሶ ድጋፍ ለሚያደርገው ሕዝብ እንባውን ለማበስ ቁርጠኛ እንደኾኑም ኮሎኔሉ አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ:-ቡሩክ ተሾመ-ከደባርቅ