ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኀይልን በመደምሰስ የጀግኖች አባቶችን ታሪክ በተግባር እየደገሙ መሆናቸውን በተከዜ ግንባር የዘመቱ ፋኖዎች ገለጹ።

565
ሕዳር 12/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጀግኖች የፋኖ አባላት አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ኀይል በተለያዩ አውደ ውጊያዎች እንደ በጋ የዛፍ ቅጠል እያረገፉት ነው፡፡
የአኩሪ ጀብድ ባለቤት፣ ፈርጣማ ክንድ፣ ጽኑ ዓላማና ቆራጥ ወኔ የተጎናጸፉት ፋኖዎቹ ጋራ ሸንተረሩን እንደ ንሥር በንቃት ይቃኙታል፤ እንደ ፈጣኑ አቦ ሸማኔ ይምዘገዘጉበታል፤ በሚሰጣቸው ጥይት ልክ ጠላትን ላይመለስ እስከወዲያኛው እንደሚሸኙ አረጋግጠዋል፤ እያረጋገጡም ይገኛሉ።
“ሁልጊዜ የጠላትን ግንባር ነው የምንመታው” ሲሉ ነው የተናገሩት።
ሳጅን ዜናው ዋኘው ጠላትን ዳግም በማዋረድ የአባቶቻችንን ታሪክ በተግባር ለመድገም ወደ ፋኖ ተቀላቅያለሁ ብሏል። ፋኖ ሰፈር መለሰና ፋኖ አጋየ አድማስ ጀግንነትና ገድል ፋኖን ለመቀላቀል እንዳነሳሳው ተናግሯል።
ሽብርተኛው ትህነግን ሥልጣን ላይ እያለ ጭምር ሲታገለው እንደነበረ ያስታወሰው ሳጅን ዜናው “ልጅህን ካላመጣህ እያሉ አባቴን ሲያንገላቱትና ሲደበድቡት ነበር” ብሏል።
ማንኛውም ወጣት ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይልን አምርሮ ሊታገለው እንደሚገባም ገልጿል።
ሌላው ፋኖ ሰጠኝ ሲሳይ አማራንና ኢትዮጵያን የማዳን ወቅቱ አኹን ስለኾነ ኹሉም መነሳት እንዳለበት ተናግሯል።
ፋኖ የአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይልን ሴራ ቀድሞ በመረዳት ሲታገል ቆይቷል ያለው ፋኖ ሰጠኝ አኹን ላይ የጠላት ሴራ ለኹሉም ግልጽ ስለኾነ ሕዝቡ ጠላትን ማጥፋት አለበት ነው ያለው። በተለይ ወጣቱ ለሕዝብ የሚታገሉ ፋኖዎችን በመለየት አባል እንዲኾኑና አማራን ብሎም ሀገርን እንዲያድኑ መልዕክት አስተላልፏል።
ኅብረተሰቡ የሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይልን ሴራ መረዳት እና በሚነዛው የሐሰት ፕሮፖጋንዳ መሸበር እንደሌለበት አስገንዝቧል።
ፋኖ እናትማር አየልኝ አማራን ለማጥፋትና ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቆርጦ የተነሳውን አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይልን ለመደምሰስ በግንባር እየተፋለመች ነው።
“ፋኖ በየግንባሩ የተሰጠውን ተልዕኮ በአኩሪ ጀብድ እየተወጣ ነው” ያለችው ፋኖዋ ጠላትን ለማጥፋት የተቀጣጠለው ትግል በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ ወደኋላ እንደማትመለስ አረጋግጣለች።
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይልን ለመደምሰስ ፋኖ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ ልዩ ኃይል፣ ከሚሊሻና ከክተት ጥሪ ዘማቾች ጋር ያለው ቅንጅት እና መናበብ አስደናቂ ነው ብላለች።
ሌላው የፋኖ አባል መሰረት ወርቁ አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ኃይል ለማጥፋት መዝመቱን ተናግሯል።
ፋኖ መሰረት ከአባቱ ያገኘውን ልምድ በመጠቀም ለወገን ኀይል የመሳሪያ ጥገና በማድረግም ተጨማሪ ግዴታውን እየተወጣ እንደሚገኝም ገልጿል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ-ከተከዜ ግንባር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article❝…የተጋረጠብንን የህልውና ስጋት አንድ ሆነን ማሸነፍ እንችላለን❞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleአንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሰልፍ በካናዳ ተካሄደ።