
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባስተላለፈው መልዕክት ❝አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣው የሽብርተኛው የሕወሓት አረመኔያዊ ድርጊት የሰው ዘር ኹሉ ሊቃወመው የሚገባ ነው❞ ብሏል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በጉዳዩ ላይ ያስተላለፈው መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል:-
የሽብር ቡድኑ ሕወሓት በወረራቸው አካባቢዎች ላይ እየፈጸመ ስለሚገኘው አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መንግሥት በተለያየ መልኩ ሲያሳውቅ ቆይቷል።
የአሁኑ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርትም የሽብር ቡድኑ እያደረሰ ያለው ሰብዓዊ መብት ጥሰት የባህሪው መሆኑን ያጋለጠ ነው።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በወረራቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሲፈጽም መቆየቱን የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሴቶችን አነጋግሮ ያጠናቀረውን ሪፖርት አውጥቷል።
በአማራ ክልል በተለይ ነፋስ መውጫ አካባቢ የሚኖሩ 16 ሴቶች ላይ የሕወሓት የሽብር ቡድን አባላት ሰው የኾነ ፍጡር ሊፈጽመው ቀርቶ ሊያስበው የሚይገባውን በቡድን አስገድዶ የመድፈር ወንጀል እንደፈጸሙባቸው ተጎጂዎቹ ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተናግረዋል።
ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል ምስክርነታቸውን የሰጡት ተጎጂዎች እንደተናገሩት የአሸባሪው ቡድን ሕወሓት ታጣቂዎች በመሣሪያ በማስፈራራት በአሰቃቂ ሁኔታ በቡድን አስገድዶ የመድፈር ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል፤ ቤት ንብረታቸው ተዘርፏል። ሕጻናት ልጆቻቸው አሰቃቂውን ተግባር በዓይናቸው እንዲያዩና የዘለዓለም ቁስል እንዲፈጠርባቸው ተደርጓል።
የሕክምና ጣቢያን ጨምሮ የተለያዩ አገልገሎት መስጫ ተቋማትን የሽብር ቡድኑ አባላት እንዳቃጠሉ ሪፖርቱ አረጋግጧል።
ነፋስ መውጫን ለዘጠኝ ቀናት ወርሮ የቆየው አሸባሪ ቡድን በእነዚህ ቀናት ከ70 በላይ ሴቶችን አስገድዶ ደፍሯል። ይሄንንም የጥቃት ሰለባዎቹ ለክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ማሳወቃቸውን አምነስቲ ኢንተርናሸናል አረጋግጧል።
የማይካድራ ጭፍጨፋ ሲፈጸም ዓለም ይሄንን የሽብር ቡድን ቢያስቆመው ኑሮ፣ በዚህ ሪፖርት የተገለጡትና ያልተገለጡት የሰው ልጅ ሰቆቃዎች ባልቀጠሉ ነበር።
አሸባሪው ሕወሓት በተለያዩ አካባቢዎች በሰው ዘር ላይ ሊፈጸሙ የማይገባቸውን ወንጀሎች ፈጽሟል። ይሄንንም የተለያዩ ተቋማት ቢዘገይም እየገለጡት ነው። ይህ ሪፖርት የተጠናቀረው የሽብር ቡድኑ ተሸንፎ በለቀቃቸው አካባቢዎች ነው። አሁንም በወረራቸው አካባቢዎች ከዚህ የባሰ ኢሰብዓዊ ድርጊት እየፈጸመ ይገኛል። የሰብዓዊ መብት ተቋማት ምርመራቸውን አስፍተው ይሄንን ዘግናኝ ተግባር ለዓለም እንዲያሳውቁ ኃላፊነት አለባቸው። ይህ ለሰው ዘር ሕይወት ጠላት የሆነ የሽብር ቡድን ከዚህ በላይ ወንጀል እንዳይፈጽም የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ኾኖ ሊያስቆመው፣ ዓለምም ሊያወግዘው ይገባል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት