
ጥቅምት 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያዊነት ረቂቅ ነው ተመርምሮ የማይዘለቅ፣ ኢትዮጵያዊነት ምሥጢር ነው ከምንም በላይ የሚልቅ፣ ኢትዮጵያዊነት ማዕበል ነው የሚያጥለቀልቅ፣ ኢትዮጵያዊነት ቅዱስ መንፈስ ነው እርኩስ መንፈስ የሚያስለቅቅ፣ ኢትዮጵያዊነት ፀጋ ነው ከአምላክ የሚሰጥ፣ ኢትዮጵያዊነት ክብር ነው ከሁሉም የሚበልጥ፣ ኢትዮጵያዊነት ቃል ነው በምንም የማይለወጥ፣ ኢትዮጵያዊነት ኀያል ነው ከሁሉም የሚበልጥ፣ ኢትዮጵያዊነት ውቅያኖስ ነው ከገቡበት የሚውጥ፣ የሚያሰምጥ።
ኢትዮጵያዊነት እሳት ነው ሲነኩት የሚያቃጥል፣ ተራራ ነው ሲገፉት የሚጥል፣ የክፋት ኃይሎች ሁሉ ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያዊነት በታች ናቸው። ኢትዮጵያዊነትን ያሸነፈ፣ ክብሩን ያለፈ የለም። የኢትዮጵያዊነት ገመድ ፅኑ ነው የማይበጠስ፣ የኢትዮጵያዊነት ቤት ዘላለማዊ ነው የማይፈርስ፣ የማይገረሰስ፣ በኢትዮጵያዊነት የሚሸነፍ እንጂ ኢትዮጵያዊነትን የሚያሸንፍ አይገኝም። አልተገኘምም።
ኢትዮጵያዊነት ቃል አለው የማይበጠስ፣ ክብርና ፀጋ አለው የማይረክስ። ፈጣሪ ኢትዮጵያን አብዝቶ ይወዳታል፣ ከሰማይ ለምድር የተሰጡ በረከቶችን ሁሉ ያለ ስስት ሰጥቷታል። በኃይሉ ይጠብቃታል፣ በበረከቱ ጥላ ሥር ያኖራታል። አስቀድሞ የመረጣት፣ በምህረቱ የሚጠብቃት፣ ለበረከትና ለምስክር ያዘጋጃት፣ ከሁሉም በላይ ያረቀቃት፣ በምስጢር ያኖራት፣ ተወዳጅ ያደረጋት ናት-ኢትዮጵያ።
የኢትዮጵያ ምስጢር የገባቸው ሁሉ ይናፍቋታል፣ በበረከቷና በተስፋዋ ምድር ይኖሩ ዘንድ ይመኟታል። ከኢትዮጵያ ምስጢር የራቁት ልባቸውን በጥቅምና በክፋት የሞሉት ደግሞ ኢትዮጵያን ያጠፏት ዘንድ ይመኛሉ። እርሷ ግን ሊያጠፏት የሚመኙትን ሁሉ በአምላኳ ልዩ ረዳትነት፣ በልጇቿ ጀግንነት እና ፅናት ታጠፋቸዋለች። የነኳት ሁሉ በየተራ ወድቀዋል፣ በየተራ አልቀዋል። ዛሬም ያልቃሉ።
ኢትዮጵያ ዝም ብላ ሀገር አይደለችም። ፍቅር፣ ክብር፣ ምሥጢር፣ ተስፋ፣ ታሪክ ናት። ጥቁሮች ተስፋ አድርገዋታል። ተመክተውባታል፣ ኮርተውበታላል፣ በጨለማ ውስጥ ሆነው ብርሃን በአሻገር ተመልክተውባታል። ተስፋቸውን በኢትዮጵያ ላይ ጥለው ሳያጓድሉ አግኝተዋል። የጨለማውን ዘመን አልፈውባታል። ተስፋ የጣሉባት ሁሉ ምኞታቸው ሰምሯል፣ ተስፋቸውም እውን ሆኗል።
ኢትዮጵያ የጥቁሮች መመኪያ፣ መከታና አለኝታ ናት። ለምድር የተሰጡት በረከቶች ሁሉ በኢትዮጵያ አሉ። ለምድር የሚላኩ መርገሞች ሁሉ ስለ ኢትዮጵያ ይቀራሉ። እርሷ ፈጣሪዋን የምታከብር፣ የፈጣሪዋን ትእዛዛት ሁሉ የምትጠብቅ እና በፈጣሪዋ የምትጠበቅ ናትና መርገምና በደል ሁሉ ስለ ኢትዮጵያ ሲል ከምድር ይርቃል። በየዘመናቱ ኢትዮጵያን የነኩ ሁሉ እንዳልነበር ሆነዋል። በዓለም አደባባይ አፍረዋል። አዝነዋል። ተዋርደዋል።
ኢትዮጵያን ያከበሩ ደግሞ በዓለም አደባባይ ተከብረዋል። በሰገነቱ በኩራት ተራምደዋል። ኢትዮጵያ በደም የፅናች፣ በአጥንት የጠነከረች፣ በጀግንነት የኖረች፣ በበረከት የተጠበቀች ናት። ልጆቿ ስለ ኢትዮጵያ ሲሉ ደም አፍስሰዋል፣ አጥንት ከስክሰዋል። ለክብሯ ሲሉ ሕይወታቸውን ሰጥተዋል። በአፈሰሱት ደም፣ በገበሩት አጥንት፣ በሰጡት ሕይወት ልክ የተከበረች፣ የታፈረች፣ የተቀደሰች ሀገር አኑረዋል።
አያሌ ጠላቶች በኢትዮጵያ ላይ ተነስተውባት ሁሉም ከኢትዮጵያዊነት በታች ሆነው አልፈዋል። ኢትዮጵያ በጀግንነት ከፍ ስትል ጠላቶቿ ደግሞ ዝቅ ይላሉ። ኢትዮጵያን የነኩ ሁሉ ተስፋ አጥተዋል። በጨለማ ውስጥ ኖረዋል። በታሪክ ተዋርደዋል። ምነዋ ይህች ሀገርስ ምን አይነት ኃያል ናት ሲሉ ተደንቀዋል። ኢትዮጵያ ፍትሕን አፅንታለች፣ ፍቅርን አስተምራለች፣ ወንበዴን ቀጥታለች፣ ግፈኛን አደብ አስይዛለች።
ከቀደሙት ጠላቶቿ ያልተማሩት፣ በጉያ የበቀሉት ጠላቶች ዛሬም በኢትዮጵያ ላይ ተነስተውባታል። ልጇቿን ሰላም አሳጥተዋል። በግፍ ገድለዋል። አፈናቅለዋል። ቀያቸውን አርክሰዋል። ለዓመታት ሀብቷን ዘርፈው፣ አዘርፈው ያልበቃቸው ጠላቶች ዛሬም እንዝረፍሽ፣ እናዘርፍሽ እያሉ ነው። የኢትዮጵያ አሁናዊ ጠላት አሸባሪው ትህነግ ሳይገባው ኢትዮጵያን ባሰተዳደረበት ዘመን ሕልቆ መሳፍርት የሌለው በደል አድርሷል።
በበደሉ ብዛት የተማረሩት ኢትዮጵያውያንም እልል ብለው መሾም እንደሚችሉበት ሁሉ እምብኝ ብለው ማውረድ ይችሉበታልና እምብኝ ብለው ከስልጣኑ አውርደው፣ ከክብሩ አዋርደው በዋሻ ውስጥ ጣሉት። እኩይ ባሕሪው እስከመቃብር አፋፍ ድረስ አብሮት የተከተለው እድሜ የማይመክረው አሸባሪው ትህነግ ከዋሻ ወጥቶ ኢትዮጵያን እየዋጋት ነው።
ኢትዮጵያን ለማፍረስና ለማሳነስ ይበጀኛል ያለውን ሁሉ እያደረገ ነው። ኢትዮጵያዊያንም በክፋቱ ሲገፋበት መቃብሩ ይፋጠን ዘንድ እየታገሉት ነው። አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ኀይል ሕዝብ አስነስቶ ሀገር ሊያጠፋ በመውተርተር ላይ ነው።
የሽብር ኀይሉ በአማራና በአፋር ክልሎች ወረራ በመፈፀም ጥላቻዬን ይወጡልኛል ያላቸውን በደሎች ሁሉ እየፈፀመ ይገኛል። የዚህን አሸባሪና ወራሪ ኀይል እኩይ ጥላቻ ለማስቆምና ወደ ቀረበው መቃብሩ ለመግፋትና አፈር ለማልበስ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች እየተዋደቁ ነው።
ልክ እንደ ቀደሙት አባቶችና እና እናቶች ሁሉ አጥንት እየከሰከሱ፣ ደም እያፈሰሱ፣ ሕይወት እየገበሩ ሀገር እንድትፀና ወገን በኩራት እንዲቃና ገድል እየፈፀሙ ነው። ይህ ብቻ አይደለም ኢትዮጵያውያን በጠላታቸው ላይ በቁጣ ተነስተውበታል። በኢትዮጵያዊነት ዝናብ የፈሰሰው ማዕበል ማጥለቅለቅ ጀምሯል። ማዕበሉ ኃያል ነው የሚያሰምጥ፣ የሚውጥ፣ የኢትዮጵያዊነት ዝናብ ዳምኖ ዳምኖ ሲጥል ምድርን በበረከት ይሞላል። በምድር ያለውን እሾህና አሚካላ ያስወግዳል፣ ምድሪቷን ያፀዳታል። በክፋትና በምቀኝነት የተነሳው ማዕበል በኢትዮጵያዊነት ማዕበል ተውጦ ወደ ሚያጠልቀው ውቅያኖስ እየታነቀ እየገባ ነው። ዋኝቶ የመውጣት እድል እንኳን የለውም። እድሉ ታንቆ መሞት፣ ጠልቆ ማለቅ ብቻ ነው።
በኢትዮጵያዊነት ዝናብ የሚፈስሰው ማዕበል ጠላቶች አይችሉትም። ሆኖላቸው አይገፉትም። በግድብ አያስቆሙትም። በየዘመናቱ የኢትዮጵያዊነት ማዕበል እንዲነሱ ያደረጉ ሁሉ አልቀዋል። በማዕበሉ ተጠርገው ሄደዋል። የኢትዮጵያዊነት ማዕበል አሜካላን ያጠፋል፣ የጎበጠውን ያስተካክላል፣ የተበተነውን አንድ ያደርጋል፣ የፈዘዘውን ያሞቃል፣ የደበዘዘውን ያደምቃል፣ የመከራውን ዘመን አሳልፎ የፍስሃውን ዘመን ያመጣል።
ዛሬም ይህን ለማድረግ የኢትዮጵያዊነት ማዕበል እያጥለቀለቀ ነው። የኢትዮጵያ ሰማይ ከተቆጣ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሆ ብሎ ከወጣ የነገር ሁሉ ፍፃሜ ይሆናል፤ ትንቢት ይፈጸማል። ሀገር ሰላም ይሆናል። ጠላትም ያፍራል። ወዳጅም በደስታ ይጨፍራል። የኢትዮጵያን ሰማይ ማስቆጣት፣ ኢትዮጵያዊውን በኢትዮጵያዊነቱ መንካት መዘዙ ብዙ ነው።
“አምላክን በመለኮትነቱ፣ መንግሥትን በመንግሥትነቱ፣ ጎልማሳን በሚስቱ አትምጡበት” እንዳሉ አበው ኢትዮጵያዊውንም በኢትዮጵያዊነቱ ከመጡበት ቁጣው የከፋ ነው። ቅጣቱ ከባድ ነው። ኢትዮጵያዊነት የማይነካ፣ የማይለካ፣ ምስጢር፣ ክብር፣ ፍቅር ነውና። አሸባሪው ትህነግ በኢትዮጵያዊነት መጥቷልና ማዕበል ተነስቶበታል። እርሱ ያስነሳው ማዕበል ታላቅ መስሎት ነበር። የኢትዮጵያዊነት ማዕበል ሲነሳ ግን የጠላት ማዕበል ምንም ነው። ጠብታ ማለት ነው።
ግፍና መከራ ያስመረራቸው ኢትዮጵያውያን በተለይ ደግሞ የአማራና የአፋር ክልል ሕዝቦች ጠላትን ቀጥተው ሀገራቸውን በፅኑ መሠረት ላይ ለማፅናት እየተመሙ ነው። ማዕበል ሆነው እየነጎዱ ነው። ደግሞም ፍትሕ ለተገፉት ታዘነብላለችና ጠላታቸውን ቀብረው በመቃብሩ ላይ የሰላም ዘንባባ ይተክላሉ።
አንተም ገስግስ ለሀገርህ ታላቅ ታሪክ አንዱ አካል ሁን። ከቀረህ ግን ዛሬ ላይ ሕያዋን ይንቁሃል። ነገ ላይ የታሪክ ድርሳናት ይዘሉሃል። የታሪክ ብዕረኞች ስምህን ይረሱሃል። ስምህ እንዳይረሳ ክብርህ ከዘመን ዘመን እንዲወሳ ከፈለክ ግን ዛሬ ተነስና የእናትህን ጠላት መንጥረህ ጣል። በውስጥ ያሉትን ጠላቶች አስወግዳቸው እና በውጭ ያሉት ይግረማቸው።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ