“ጠላት ሀገር ሲደፍር ዝም ይባላል እንዴ፣ ከእኛ በላይ ላሳር የአተኳኮስ ዘዴ”

209
ጥቅምት 26/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከተራራ የገዘፈ፣ ዘመናትን በዝና ያለፈ፣ በደማቅ ቀለም የተፃፈ ታሪክ ያለህ፣ ዘመን ያከበረህ፣ ጠላት የሰገደልህ፣ ጀግንነት ያደመቀህ፣ በአይደፈሬነት የታወቅህ ነህ። የደምህ ጠብታዎች ሀገር አፅንተዋል፤ የአጥንትህ ፍላጮች ሀገር ገንብተዋል፤ በአንተ ሞት ብዙዎች ቆመው ኖረዋል። የታሪክ ጸሐፊዎች በታሪክህ ተደንቀዋል፤ ታሪክህን ለማስፈር ተቻኩለዋል፤ ተዝቆ ከማያልቀው ታሪክህ ከትበዋል፤ ዝናህን የሰሙ ሁሉ አጀብ ሲሉ ተገርመዋል። የልጅ ልጆችህ በአንተ ኮርተዋል። እንደ አለት የጠነከረ ጀግንነት፣ እንደ አልማዝ የደመቀ ኢትዮጵያዊነት፣ እንደ ውቅያኖስ የጠለቀ ታጋሽነት፣ እንደ ገሞራ የሚፋጅ አትንኩኝ ባይነት፣ ሕግ አክባሪነት፣ አልሞ ተኳሽነት የተሰጠህ፣ በጀግንነት መኖር፣ በክንድ መከበር የተቸረህ ሕዝብ ነህ።
የገፉህ ወድቀዋል፤ የነኩህ በክንድህ እሳት እየተቃጠሉ አልቀዋል፤ ሊቀድሙህ የቋመጡት ከኋላ ቀርተዋል፤ አንገትህን ሊያስደፉ የከጀሉት አንገታቸውን ደፍተዋል፤ በጨለማ ውስጥ ሊያኖሩህ የፈለጉ ራሳቸው በጨለማ ውስጥ ኑሮ መሥርተዋል። ከአንተ ጋር የገጠሙት ሁሉ ተረትተዋል።
የሚስማማህ ማሸነፍ፣ መከራውን በጥበብ፣ በጀግንነት ማለፍ ብቻ ነው። በታሪክህ ዘንግ ውስጥ ጉድፍ ያልተገኘብህ፣ ታሪክ በመልካም ነገር የሚያወሳህ፣ የጀግንነት፣ የነፃነት ተምሳሌት የሆንክ ጀግና ሕዝብ ነህ። ጀግናው ስምህ፣ ኢትዮጵያዊነት ክብርህ፣ ማዕረግህ ውበትህ፣ ጌጥህ መገለጫህ የሆነክ፣ በዘመናት የታሪክ ጉዞ ሁሉ ሽንፈት ያልፈጠረብህ ነህ አንተ። የስምህ መጠሪያ፣ መከበሪያ፣ የዘመንህ መዋቢያ፣ የደስታህ ማያ፣ የሁሉም ነገር የበላይ የሆነችው ኢትዮጵያ በተነካች ቁጥር እንደ ነብር ተቆጥተህ፣ እንደ አንበሳ አግስተህ፣ እንደ አሸዋ በዝተህ፣ እንደ አለት ፀንተህ፣ እንደ ውኃ ሙላት አስፈርተህ፣ እንደ ገደል ከብደህ ተነስተሃል።
እናትህን የነካውን ሁሉ ቀጥተሃል። ሀገር በደምና በአጥንት አፅንተሃል። አዎን አንተ “አማራ” ነህ፤ ታሪክ ያከበረህ፤ ከፍ ያለ ስም ያለህ። “አማራ” ማለት ለክብሩ የሚሞት፤ ለሀገሩ የሚዘምት ነው፡፡ “አማራ” ማለት ለተጨነቀ የሚደርስ፤ የተራበን የሚያጎርስ፤ የታረዘን የሚያለብስ፤ በየዘመናቱ በድል ላይ ድል የሚያድስ ነው። አማራ ፍርሃት የማያውቀው፣ ታሪክ ያደመቀው፣ በጥበብ የተራቀቀ ነው።
አማራ ለነፃነት፣ ለአንድነት፣ ለኢትዮጵያዊነት፣ ለሉዓላዊነት የሚሰለፍ፣ ከሰንደቅ ዓላማው በፊት የሚሞት፣ ከራስ በላይ ሀገር የሚያስቀድም ሕዝብ ነው። አማራ ከፍቶት ከተነሳ፣ ነፍጡን ወልውሎ ካነሳ ማዕበል ነው፤ ግድብ የማይመልሰው ፅኑ ነው ማንም የማይገረስሰው፤ ውሽንፍር ነው ጋራ የማይመልሰው፤ እሾህ ነው ፈሪ የማይጥሰው። ስለ አማራ ጀግንነት ጠላቶቹ ይመስክሩ።
ጀብዱ የሠራባቸው፣ ጠላትን ምጥ ያስያዘባቸው፣ ባንዳን የቀበረባቸው ተራራዎች፣ ሸለቆዎች ይናገሩ፤ ያውሩ። ጀግንነቱን አይተውታል፤ ወንድነቱን ተመልክተውታልና። የውጭ ጠላት ያልቻለህ የውስጥ ባንዳ እንዴት ሊችልህ ይቻለዋል? የውጭ ጠላት ያልገፋህ፣ ገፍቶ ያላነቃነቀህ እንዴት ባንዳ ሊገፋህ ይችላል? አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል ደጅህን ረግጧል፤ ሀብትህን ዘርፏል፤ ወገኖችህን ገድሏል፤ አፈናቅሏል። ዝም ከተባለ ሕዝብን ባሪያ ሊያደርግ፣ ሀገርን ሊበትን ነው የሚሯሯጠው።
ከነብስህ በላይ የምትወዳትን፣ እንደ ዓይንህ ብሌን የምትጠብቃትን፣ ከምንም ከማንም ጋር የማታነፃፅራትን ሀገርህን ሊያፈርስ፣ ቀዬዋንም ሊያረክስ ነው ፍላጎቱ፤ ምኞቱ። አንተ ደግሞ ሀገር ስትደፈር፣ ከቀዬው ሲበረበር ተኝቶ ያደረ ሀገሩን ያስወረረ አባት የለህም። አባትህ እና እናትህ አያት ቅድመ አያቶችህ ወራሪን የሰበሩ ሀገርን በክንዳቸው ያስከበሩ ናቸው። አሸባሪው የትግራይ ወራሪና ዘራፊ ቡድን በደሎችን እየፈፀመ ነው። የተከበረው ታሪክህን ሊያረክስ የመጣውን ሆ በልና ቅጣው፤ ከቀዬህ፣ ከመንደርህ አስወጣው፤ የማትደፈር መሆንህን አሳየው። አንተ ትከበራለህ እንጂ አትደፈርም፤ ታሸንፋለህ እንጂ አትሸነፍም፤ ሀገር ታፀናለህ እንጂ ሀገር ለባንዳዎች አሳልፈህ አትሰጥም። ባንዳ በምድርህ ይቀበራል፤ ትውልድ በክንድህ ይኮራል።
አንተ አሸባሪው የትግራይ ወራሪና ዘራፊ ኀይል ወደ መጣበት ሁሉ ትመም። ከፊት ቅደም። አሸባሪው የትግራይ ወራሪና ዘራፊ ኀይል ከሚያዋርድህ፣ ትውልድ ከሚስቅብህ ባሩድ በልቶህ ታሪክ ያክብርህ። “ስደደኝና ከጥጉ ድረስ፣ አቧራ አልብሸው ቶሎ ልመለስ” እንዳሉ አቧራ አልብሰኸው፣ ከአፈር ቀላቅለኸው ቶሎ ተመለስ። አንተ ጠላት የሚያከብርህ እንጂ የሚያሸንፍህ አይደለህም። አትጠራጠር በመሬትህ ጠላት ይቀበርበታል እንጂ አይኖርበትም። አንተ ብቻ ነፍጥህን አንሳ። ክንድህን አበርታ። ጠላትህ ዛሬ ላይ ዘርፎህ ሊስቅ ይችላል። አንተ ግን ጠላትህን ቀብረህ ለዘላለም ትስቃለህ። በደስታ ትኖራለህ።
“ጠላት ሀገር ሲደፍር ዝም ይባላል እንዴ፤
ከእኛ በላይ ላሳር የአተኳኮስ ዘዴ፤” በለው። ከአንተ በላይ አተኳኮስ፣ ላሳር ነው። ተኩሶ መሳት በዘርህ አልተፈጠረብህም። አንድ ጥይት ለአንድ ጠላት፤ ስትፈልግ ግንባሩን፣ ሲያሻህ እግሩን፣ ወይም ደረቱን፣ ወይም የእግር ባቱን እየመታህ እሳዬው። በችግር ጊዜ መተኮስ፣ በሰላም ጊዜ ማረስ፣ ነጭና ጥቁር ማፈስ፣ ማጉረስ ለአማራ መታወቂያው ናቸው።
የአተኳኮስ ዘዴህን ከግንባሩ ላይ አሳየው። የአማራን ምድር ለአሸባሪው የትግራይ ወራሪና ዘራፊ ኀይል መቀበሪያ አድርገው። ሀገር ወዳድ እንጂ ሀገር አፍራሽ ባንዳ አይኖርበትም። ተነስ ለሠንደቁ ተዋደቅ፤ የጠላትህን አንገት እነቅ፤ የተያዘውን መሬትህን አስለቅቅ።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article❝ራሳችንን ነፃ ለማውጣት፣ ክብራችንና ታሪካችንን ለመጠበቅ የምንሰስተው ሕይወት አይኖርም❞ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አብዱ ሁሴን
Next article❝መዝመት፣ አካባቢን ነቅቶ መጠበቅ፣ ጸጉረ ልውጦችን መከታተል እና ለወገን ጦር ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክሮ በመቀጠል በአጭር ጊዜ ሽብርተኛውን የትግራይ ወራሪ ኃይልን ማጥፋት ይገባል❞ ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ ማሞ