
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 22/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በኢትዮጵያ ላይ የሕልውና አደጋ ደቅኖ ሕዝብን ለስደት እና ለሞት፣ ንብረትን ለውድመት እያጋለጠ ይገኛል፡፡ ከዚህ ባሻገር ወረራውን በዚህ ወቅት ማድረጉ አርሶ አደሮች ማሳቸውን በዘር ሸፍነው በቂ ምርት እንዳያመርቱ ለማድረግና ሕዝቡን ለረሃብ ለማጋለጥ መሆኑን የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
ወጣት ዮሴፍ አዳነ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በዚህ ወቅት ጦርነት መክፈቱ አርሶ አደሮችን ከእርሻ ሥራቸው እንዳደናቀፋቸው ተናግሯል፡፡ አሸባሪው ቡድን እድሜያቸው ለሥራ ያልደረሱ ሕጻናትን እና ነፍሠ ጡር እናቶችን ለጦርነት ማሠለፉ ሕዝባዊ ጦርነት ስለመክፈቱ ማረጋገጫ እንደሆነ ኅብረተሰቡ መረዳት አለበት ብሏል፡፡
መንግሥት የትግራይ ሕዝብ ወደ ግብርና ሥራው እንዲመለስ የተኩስ አቁም ውሳኔ ቢያሳልፍም አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ግን ጦርነት መክፈቱ ጠላትነቱ ለአማራ ብቻ ሳይሆን ለትግራይ ሕዝብም ጭምር መሆኑን ማሳያ ነው ብሏል፡፡
ወጣት ዮሴፍ በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች የተሻለ ምርት ለማምረት ጥረት ማድረግ አለባቸው፤ የተጀመረው የዘማች ቤተሠቦችን ማሳ የመንከባከብ እና የማገዝ ሥራም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያለው፡፡

የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው ሶፎኖያስ ማሞ እንዳለው አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ዓላማው የአማራን ሕዝብ ሀብት በመዝረፍና በማውደም ለረሃብ ማጋለጥና ሀገርን ማፍረስ ነው፡፡
ሽብርተኛው ቡድን የአማራ አርሶ አደር እንዳያርስ፣ አምርቶ ቤተሠቡን እና ሌሎችን እንዳይመግብ ለማድረግ የሚያደርገው ወረራ ሕዝብን እና መንግሥትን ለችግር ለማጋለጥ ነው፤ ይኽ አይሳካለትም፤ በቀጣይም ተሎ የሚደርሱ ሰብሎችን በመዝራት ዓላማውን ማክሸፍ ያሥፈልጋል ብሏል፡፡ ይኽን አሸባሪ ቡድን ለመደምሰስ አንድነት መፍጠር፣ መተባባር እና ለአንድ ዓላማ መቆም ተገቢ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡
ይህን ችግር ለማለፍ እያንዳንዱ ሰው የሌላውን መስዋእትነት መጠበቅ የለበትም በተሠማራበት የሥራ መሥክ ሁሉ እራሱን ለመስዋእትነት ማዘጋጀት አለበት ነው ያለው፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ