
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 20/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ደግነት እንደዥረት የሚፈስስበት፣ እንግዳ ተቀባይነት እንደ ውቅያኖስ የሰፋበት፣ ፍቅር ተፀንሶ የተወለደበት፣ አድጎ የጎረመሰበት፣ አብሮነት ሥር የሠደደበት፣ መቻቻል ከፍ ያለበት፣ ኢትዮጵያዊነት የፀናበት ምድር። አብሽር እያሉ ጭንቀትን ያርቃሉ፣ በማያልቀው ፍቅራቸው የተጨነቀችን ነብስ ያፅናናሉ፣ በእቅፋቸው ያሞቃሉ፣ የደበዘዘ የሚመስለውን ቀን ብሩህ ያደርጋሉ። አብሮ መብላት፣ መጠጣትና ዓለምን ማዬት መገለጫቸው ነው። የወሎን ምድር የረገጠ ሁሉ ኑሮዬን ከእነርሱ ጋር ያድርገው ይላል።
ወሎዬዎች ለኢትዮጵያ ሠንደቅ ክብር፣ ለሀገር ፍቅር ራሳቸውን ይሰጣሉ። እንኳን ልባቸውና ኢትዮጵያዊ ደማቸው ጭሳቸውም በሠንደቁ ያመረ፣ ሠንደቁን ያከበረ ነው። የኢትዮጵያዊነት ምስጢር በወሎ ሰማይ ሥር ሞልቷል። ለአረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ የተሰጠው ቃላቸው፣ ጭንቅ ቢመጣ መከራው ቢበዛ አይታጠፍም። ፀንቶ ይኖራል፣ በፅናት የመከራውን ቀን ይሻገራል፣ በድቅድቅ ጨለማ እያሻገረ ያበራል።
ወሎን ለፍቅር፣ ወሎን ለክብር፣ ወሎን ለሀገር፣ ወሎን ለፅናት፣ ወሎን ለኢትዮጵያዊነት፣ ወሎን ለአንድነት፣ ወሎን ለአብሮነት፣ ወሎን ለደስታ፣ ወሎን ለነብስ እርካታ፣ ወሎን ለመከታ። ልብን በሚሰርቀው ፍቅራቸው፣ ደስታን በሚለግሰው ፈገግታቸው፣ ውቃቢን በሚያስታርቀው ጭሳቸው፣ መሬት ጠብ በማይለው ቀና ምርቃታቸው፣ አንጀት በሚያርሰው ለዛቸው፣ ተኩሶ በማይስት ጀግንነታቸው፣ በማይገመግማው ለስጦታ በተዘረጋው እጃቸው ያያቸው ይቀናባቸዋል፣ አብዝቶ ይወዳቸዋል፣ ያላያቸው ይናፍቃቸዋል፣ በአሻገር ኾኖ ይሳሳላቸዋል።

“አብሽር አቦ” እያሉ የጨነቀውን እያቀለሉ፣ ለችግር መፍትሔ እየሆኑ የተጨነቀውን አሻግረዋል፣ ያዘነውን አረጋግተዋል። ፈትፍቶ ማጉረስ፣ አቀማጥሎ ማልበስ ባሕሪያቸው ነው። በሼህ ሁሴን ትንቢት፣ በግሸን በረከት፣ በላል ይበላ ረድኤት፣ በተድባበ ማርያም ጥላነት፣ በአዛኑና እና በኪዳኑ በሚመጣው በረከት እየተመጀኑ ይኖራሉ። ወሎዬ ሙስሊሞቹ ለሶላት እየገሰገሱ፣ ክርስቲያኖቹ ቅዳሴ እያስቀደሱ፣ ኪዳን እያደረሱ፣ ከመስጊድና ከቤተክርስቲያን መልስ በአንድ ማዕድ እየቆረሱ፣ ቄሱ ለሼሁ፣ ሼሁ ለቄሱ እየተጎራረሱ፣ ቤታቸውን በፍቅር ይመላሉ፣ ለልጆቻቸው ፍቅር ያሳያሉ፣ በፍቅር ትምህርት ቤት ውስጥ ያሳድጋሉ።
“መጄን ብሎ ገዳይ መጄን ብሎ አፍቃሪ፣
እንደ እርሱ ሙሐባ መች ሰጠ ፈጣሪ” እንዳለች ከያኟ መጀን ብሎ የሚያፈቅር፣ በፍቅር የሚገድል፣ መጄን ብሎ በጠመንጃው የሚጥል፣ ከግንባር ግንባር የሚነጥል፣ ጠላቱን ከወዳጁ ለይቶ የሚገድል፣ አንድ ጥይት ለአንድ ጠላት የሚያድል እንደ ወሎዬ ማን አለ። ወሎዬዎች ቢሻቸው በፍቅር እንዲያም ቢል በጦር ማሸነፍ ያውቁበታል፣ ሁሉም ለእነርሱ ተመቻችቶ የተሰጠ ነው። ደግነት ከጀግንነት፣ የዋህነት ከአርቆ አሳቢነት ጋር ተዋሕዶ ተሰጥቷቸዋልና። ወሎዬ ሀገር በተጨነቀች፣ ክብር በተደፈረች ጊዜ ሁሉ ዘራፍ ብሎ እየዘመተ፣ ጠላቱን እያነከተ፣ ለእናት ሀገሩ ኢትዮጵያ ድል እያበረከተ የኖረ ነው።
በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ አለፍ ሲልም በዓለም ከተፈጥሮው ተራራ እጅግ የገዘፈ የጀግንነት ተራራ የቆመበት፣ የዓለም ሕዝብ የተደመመበት፣ ኃያላኑ የተሸበሩበት፣ ክፉ አድራጊዎች እቅዳቸውን የቀደዱበት፣ የእኩልነት ፀሐይ አሻግሮ የታዬበት፣ የኢትዮጵያውያን ጀብዱ የተመሰከረበት፣ ኢትዮጵያዊነት አሸናፊነት መሆኑ የተረጋጋጠበት፣ ጠላት አንገቱን የደፋበት፣ ኢትዮጵያዊ ደረቱን የነፋበት፣ ጥቁር ሁሉ አንገቱን ያቃናበት፣ የነጭ አብዮት የተንኮታኮተበት፣ የጥቁር አብዮት መሠረቱ የፀናበት፣ የነጭ የግፍ ጮራ የጠለቀበት፣ የጥቁር ጀንበር ላይጠፋ በምሥራቅ የዘለቀበት፣ የሮም አደባባይ በሀዘን የተመላበት፣ የኢትዮጵያ ጎዳናዎች በእልልታ ድምፅ የተዋጡበት፣ የሮም ነገሥታት የቆዘሙበት፣ ወይዛዝርቱ ያለቀሱበት፣ የኢትዮጵያ አርበኞች አካኪ ዘራፍ የፎከሩበት፣ ወይዛዝርቱ ጎዳናዎችን በዜማ ያደመቁበት፣ ጎበዛዝቱ በግርማ ያጋሱበት ግዙፉ ድል ዓድዋ። ዓድዋ እንዲመጣ ወሎዬው በታላቁ ሰው በደገኛው ንጉሥ በሚካኤል እየተመራ ጀብዱ ፈፅሟል። የኢትዮጵያ ምድር በደም እንዲቀደስ፣ የጠላት ሕልም በሳንጃ፣ በጦር በጎራዴ እንዲረክስ ወሎዬው ተዋድቋል። ታሪኩን ከፍ አድርጎ አድምቋል።

በዘመነ ዮሐንስ አራተኛ የጣልያን ጦር በምፅዋ ገባ። በዚያም አላረፈም ከምፀዋ አልፎ ሌሎች አካባቢዎችን ወረረ። ንጉሡ ዮሐንስም ለጣልያኑ ንጉሥ ኡምቤርቶ ደብዳቤ ፃፉ። ወታደሮቻቸውን ከሀገራቸው እንዲያስወጡላቸው ጠየቁ። ዳሩ ቀና ምላሽ አላገኙም። ለእንግሊዟ ንግሥት ቪክቶሪያም ደብዳቤ ፃፉ። ንግሥቲቱም “ከኃይለኞቹ ከጣልያናዊያን ጋር በፍቅርና በሰላም ቢኖሩ ይሻልዎታል” የሚል መልስ መለሱ። ንግሡ በብስጭት አዋጅ አወጁ። ሀገር ተሰብሰብ ተደፍረናል አሉ። በዚያ ወቅት የእናት ሀገር ጥሪ የደረሳቸው ንጉሥ ሚካኤል ሠራዊታቸውን ይዘው ወደ ጦር ግንባር ዘመቱ።
ዶክተር ምስጋናው ታደሰ “ሚካኤል ንጉሠ ወሎ ወትግሬ ” በሚለው መፃሕፋቸው ጄራርድ ፓርታልን ዋቢ አድርገው “የወሎው ሚካኤል ጦር በብዛቱም ይሁን በጥራቱ ከንጉሠ ነገሥቱ ጦር ቀጥሎ ሁለተኛው ነበር” ብለዋል። በሚካኤል የተመራው የወሎ ጦር በሰአቲ የመሸገውን የጣልያንን ጦር ሊዋጋ ሄደ። የጣልያን ጦርም ደፍሮ አልዋጋ አለ። የኢትዮጵያ እና የጣልያን ጦር እንደተፋጠጠ ቀናት ተቆጠሩ። በዚህ መካከል ኢትዮጵያን ለመውጋት የቋመጠ ሌላ ሀገር እንደመጣ ተሰማ።
በዚያ ዘመን ድርቡሾች ሀገር መውረር፣ ታሪክም ማጥፋት ላይ ተጠምደው ነበር። ይህን የሰማው የኢትዮጵያ ጦር የሰአቲውን ጠላት ባለበት ትቶ ወደ አስቸኳዩ ጦርነት ፊቱን አዙረ። በሚካኤል የሚመራው እግረኛና ፈረሰኛ ጦር ልረፍ አላለም። ሀገር ተደፈረች ወደተባለበት ንፍቅ ገሰገሰ። ድርቡሽም ተሸበረ። ጀግኖች እያገሱ መጥተውበታልና። የማይቀረው ተጀመረ። ጀግናው ክንዱን ዘረጋ። በዚህ ጦርነት ላይ ራስ ሚካኤልና ጦራቸው ጀብዱ እንደፈፀሙ ዶክተር ምስጋናው ታደሰ በመፃሕፋቸው እንግሊዛዊውን ዊልዴ አውጉስቱስ ብላንዲን ጠቅሰው እንዲህ ብለዋል።
“ሚካኤል በመተማው ጦርነት ላይ የድርቡሽን ምሽግ ሰብረው በመግባት የሠራዊታቸውን ጥንካሬ አሳይተዋል” ዳር ድንበር አስከበሩ። ጀግንነታቸውን አስመሰከሩ። ሀገር አኮሩ።

ዘመን ዘመንን አስከትሎ ሌላ ታሪክ መጣ። ዓድዋ ደረሰ። ምኒልክ ባወጁት አዋጅ፣ ኢትዮጵያ ባሰማችው ድምፅ ሚካኤል ሠራዊታቸውን ይዘው ወደ ዓድዋ ዘመቱ። ይህ ብቻ አይደለም ወረኢሉ ላይ ከተህ ጠብቀኝ የተባለውን ጦረኛ አስተናግደው ለሀገራቸው ጀግኖች ፍቅርንና ጀግንነትን አስታጥቀዋል ደገኛውና ጀግናው የጦር መሪ ሚካኤል። ሚካኤል እና ጦራቸው ከአምባላጌ ጀምሮ የጠላትን ጦር ድል እየመታ የዓድዋን ድል አብስረዋል። በዚህ የሀገር ጥሪ ዘመቻ ሚካኤል ከንጉሠ ነገሥቱ በመቀጠል በርካታ ጦር ያሰለፉ ጀብደኛ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል።
ወሎዬ እንዲዚህ ነው። ሀገር ተነካች በተባለበት ሁሉ እየዘመተ፣ ደሙን እያፈሰሰ፣ አጥንቱን እየከሰከሰ ይዋደቃል። ሀገሩን ይወዳታል፣ ይሞትላታል፣ ይመካባታል፣ ተዋድቆ ያስከብራታል። ወሎዬ ኢትዮጵያውያን ሲነኩበት በአቀፈ እጁ ሳንጃ ያነሳል፣ አልሞ ይተኩሳል፣ ምሽግ ያፈርሳል። በሀገር ድርድር አያውቅም። ዛሬም ቀደም ሲል በዓድዋ ላይ መትቶ የጣላቸው የውጭ ጠላቶቹ ተላላኪዎች ሀገር ለመውረር፣ ክብርን ለመድፈር ሲነሱ እንደቀደመው ሁሉ እምቢኝ ብለው ተነስተዋል። ሠንደቁን በልቡ አስቀምጧት፣ ከክብር በላይ ከፍ አድርጓት፣ ከነብሱ በላይ እየወደዳት አልበቃው ቢል በጭሱ ላይ ሳላት፣ በጥበብ ቀረፃት፣ በፍቅር አኖራት። ታዲያ ይህችን ሠንደቅ ሲነኩበት ክብሯን ሲጋፉበት እንዴት ዝም ይላል?
“መገን ልበል ወሎ መገን ጉራ ወርቄ መገን በል ሶዶማ፣
ይማታል በብልጅግ ያቀምሳል በክላሽ ከነካኩትማ” ትህነግ የነካካቸው የወሎ ጀግኖች ሲሻቸው በብልጅግ እንዲያም ሲል በክላሽ እያነከቱት ነው። በቀያቸው ገብቶ የሚወጣ የለም፣ ከነስሙና ከነግብሩ በቀያቸው ይቀብሩታል። የወሎ ጀግኖች በተኮሷት ጥይት ልክ ጠላት እያነጠፉ ወደፊት እየገፉ ነው። እልፍ የወሎ ጀግኖች ለጠላት እረመጥ ሆነውበታል።
“አናቱ ዱበርቴ አባቱ ቄስ ናቸው
ላገሩ የሚተርፍ ምርቃት ዱዓቸው” እንደተባለ በእናት እና በአባቱ ምርቃት፣ ምህልና ፀሎት፣ በቀደመው ታሪኩ ብርታት፣ በዘመኑ ጀግኖች ግለት ጠላቱን እየደመሰሰ ነው። በማይመጣው መጥተውበት፣ ኢትዮጵያን ነክተውበት ተቆጥቶ ተነስቶ ዋጋቸውን እየሰጣቸው ነው።
“በላይኛው ታቦት በታች ረከቦት፣
የነነየ ዱዓ ዱበርቲ ሸልሞት” ዱበርቲው ሸልሞት፣ ታቦቱ ረድቶት ለእናት ሀገሩ በእውነት መንገድ ስለ እውነት እየታገለ ነው። ድልም ከእርሱ ጋር ናት። ዘርቶ በሚያበቅልበት፣ አብቅሎ በሚያርምበት፣ እሸት በሚቆርጥበት፣ ማሳውን በአዝመራ በሚያለመልምበት ወቅት ጠላት መጥቶ ሲነካው፣ ልቡ ሸፈተ፣ አምርሮ ተቆጣ። ቀንበሩን አስቀምጦ ከትራሱ ያስቀመጠውን ነፍጥ አወጣ። ነፍጡ ከተነሳ፣ አፈሙዙ ከተወለወለ በኋላ መላሽ የለውም። ወደፊት ብቻ ነው።

“የወሎ ገበሬ ደጉ ደጉ ሰው
ያባቱን ባድማ፣
በማረሻ ሳይሆን በአፈሙዝ አረሰው” ደጉና ጀግናው ገብሬ በማረሻ በሚያርስበት ወቅት ጠላት ሲመጣበት፣ በማሳው ሲያንዣብበት መረሻውን አስቀምጦ በአፈሙዝ አረሰው። ጠላትን ሬሳ በሬሳ አደረገው። ትልሙ አምሯል፣ የአፈሙዙ እርሻ ቀጥሏል፣ እያነጣጠሩ፣ እየመነጠሩ መቀጠል ብቻ ነው። የውሎ ምድር ከዳር እስከዳር ጠላት ይቀበርበታል። የገባው አይወጣም። ለዳግም ጥፋት ጠላት አይመጣም የአፈሙዙ እርሻ ከባድ ነውና። ወሎዬን በፍቅር እንጂ በጦር ለማሸነፍ መከጀል የእነ ሚካኤልን ወኔ መቀስቀስ ይሆናል።
“ኢትዮጵያ በሚሏት የአናብስት ጎፈር የቃል ኪዳን ምድር፣
የአባቶቹን ድካ እየበጣጠሰ እየሸረሸረ ማተቡን የሚሽር፣
ይልሃል ሚካኤል በለው በምንሽር።
ጥቁር ሰው ዘመተ ምኒልክ ተነሳ ታመሰ መሬቱ፣
የጣይቱ ምጣድ የጣይቱ ማጀት ይፋጃል እሳቱ፣
ሳተናው ሚካኤል አመዱን ሳያፍሰው አይገባም ከቤቱ” እንዳለ ገጣሚው ወሎዬ ጠላቱን ሳያጠፋው ከቤቱ አይገባም። ለዚያም ይሆን ዘንድ በሠንደቋ ምሎ፣ ዝናሩን በወገቡ ድርብ አዙሮ ጠቅልሎ የወገቡን ጩቤ አሳምሮ ስሎ ምሎ ወጥቷል። መሀላውን አያፈርስም። ለቃሉ አዳሪ ነውና ያሻውን አድርጎ ይመለሳል።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ