
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 16/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ኀላፊዎች እና ሠራተኞች በህልውና ዘመቻው ግንባር ድረስ በመሄድ በሙያቸው ለማገልገል ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ተወካይ አቶ ሳላህ ሁሴን የሀገር መከላከያ ሠራዊት በኢትዮጵያ ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመቀልበስ እየከፈለ ላለው መሰዋእትነት ከ3 ሚሊዮን በላይ የጥሬ ገንዘብና የዓይነት ድጋፉ አድርገዋል ብለዋል። በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኀላፊዎችና ሠራተኞች የአንድ ወር ደሞዛቸውን መስጠታቸውን እና ደም መለገሳቸውን ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ካደረገው ድጋፍ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በጥሬ ሲሆን የተቀረው 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ደግሞ ምግብ እና የህክምና ቁሳቁስ መሆኑን አቶ ሳላህ ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ለሀገር ህልውና ዘመቻው ድጋፍ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ሠራተኞቹ በህልውና ዘመቻው ግንባር ድረስ በመሄድ በሙያቸው ለማገልገል ቁርጠኛ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ ከተሳተፉት መምህራን መካከል አቶ አብዱራህማን መክተል እንዳሉት አሸባሪው ትህነግ ባለፉት 30 ዓመታት የሶማሌ ክልል ተወላጆች ላይ ብዙ ግፍ ሠርቷል፤ ክልሉም በልማት ወደ ኋላ እንዲቀር አድርጓል፡፡
“እኔ ሽብርተኛው ትህነግ በሠራው ግፍ ቁስለኛ ነኝ” ያሉት አቶ አብዱራህማን ሽብርተኛው ትህነግ በሠራው ግፍ ከሶማሌ ክልል ውስጥ ሰው ያልሞተበት ቤተሰብ እንደሌለም ተናግረዋል፡፡

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ መምህር ሰለሞን ጓዴ ሁኔታዎች ከተመቻቹ የሁለት ወራት ደሞዛቸውን ለመለገስ እንዲሁም ስልጠና በመውሰድ ግንባር ድረስ ሄደው ሠራዊቱን በመቀላቀል ደጀን ሆኖ የማገዝ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
“የዕለት ተዕለት ሥራችንን የምንሠራውና ልጆቻችንን የምናሳድገው ሀገር ሰላም ስትሆን ነው” ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው መምህር የሆኑት አያሌው ንጉሴ (ዶ.ር) ናቸው፡፡ “ችግሩን አሳንሶ ከማየት ይልቅ ሁላችንም መሰረታዊ የውትድርና ስልጠና ወስደን ለማንኛውም ሁኔታ ራሳችንን ማዘጋጀት ይኖርብናል” ብለዋል፡፡

ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ በመማር ማስተማር፣ በጥናትና ምርምር መስኮች ከሚያከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ ሀገራዊ ተልዕኮዎችን ለማሳካት የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ መረጃውን ዩኒቨርሲቲው አድርሶናል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ