
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 14/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የደባርቅ ከተማ ወጣቶች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ ልዩ ኀይል፣ ከሚሊሻና ፋኖ ጎን ተሰልፈው ሽብርተኛው ትህነግን መፋለም የሚያስችል ወታደራዊ ስልጠና መውሰዳቸውን አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን መዘገቡ ይታወሳል።
ስልጠና የወሰዱ ወጣቶችም ቃላቸውን በተግባር ለመፈጸም ወደ ግንባር በመሄድ የፀጥታ ኀይሉን በማገዝ ላይ ይገኛሉ።
ወጣት ልዑል መስፍን የሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ አስተዳደር ነዋሪ ነው። በአሁኑ ወቅት ሽብርተኛው ትህነግ በሀገር ላይ የደቀነውን የህልውና አደጋ ለመመከት ግንባር ተሰልፎ እየተፋለመ መሆኑን ገልጿል፡፡
በማይጠብሪ ግንባር አሸባሪው ትህነግ በፈጸመው ወረራ ወጣቶቹ ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ፋኖ ጋር በመሆን ቡድኑን በመደምሰስ መሣሪያ ማርከው መታጠቃቸውን ተናግሯል፡፡

ወጣት ልዑል “ይህ የታጠኩት መሣሪያ ከወገን ጦር ጋር በመሆን የሽብርተኛው ትህነግ ኀይልን በመደምሰስ የተማረከ ነው” ሲል አረጋግጧል።
የደባርቅ ከተማ ወጣቶች ለፀጥታ ኀይሉ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ከማቅረብ በተጨማሪ በአካባቢው ከተሠማራው የፀጥታ ኀይል ጋር በመሆን የሕይወት መስዋእትነት ጭምር እየከፈሉ መሆናቸውን አስተያየት ሰጪው ተናግሯል፡፡
ሌላኛው ወጣት ነጋ ተገኘ ከዚህ በፊት ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ፋኖ ጋር በመሆን አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ ቃል በገባው መሠረት በክተትና መክት ሀገራዊ ጥሪ ወደ ግምባር ማቅናቱን ተናግሯል። እሱን ጨምሮ ሌሎች ወጣቶች ደግሞ ከጠላት ጋር አንገት ለአንገት በመተናነቅ ትልቅ ጀብድ እየፈጸሙ መሆናቸውን ነው የገለጸው።
በተሰለፉባቸው ግንባሮች የሀገር መከላከያ ሠራዊትን፣ የልዩ ኃይሉን፣ የሚሊሻውን እና የፋኖን ጀግንነት እና የሚፈጽሙትን ጀብድ በማየቱ ከፍተኛ ወኔ እንደፈጠረበትም ተናግሯል።

ማሕበረሰቡም የሽብርተኛው ትህነግ ተቀላቢ ሚዲያዎች ለሚያወሩት የውሸት ወሬ ጆሮ ባለመስጠት ለፀጥታ ኀይሉ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያጠናክር እና አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ ጥሪ አስተላልፏል።
ለአሚኮ አስተያየት የሰጠው ሌላው ወጣት የሺበር መብራቱ ደባርቅ ከተማ አስተዳደር በሁለት ዙር ወጣቶች በቂ ወታደራዊ ስልጠና በመውሰድ ወደ ግንባር ዘምተዋል ብሏል። ወጣቱም በተቆርቋሪነት ከፀጥታ ኀይሉ ጋር በመሆን የሚያኮራ ሥራ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የክተት ጥሪውን ተቀብለው እና ተደራጅተው ስልጠና የወሰዱ ወጣቶች የሚጠበቅባቸውን ሀገራዊ ግዴታ እየተወጡ እንደሆነም ወጣት የሺበር ተናግሯል፡፡ አኩሪ ድል እየተመዘገበ ነውም ብሏል።
በማይጠብሪ ግንባር የተሰለፉ ወጣቶችም ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ጠላትን በመደምሰስ ዘመናዊ መሣሪያ መማረካቸውን ነው የተናገረው። በቀጣይም ሌላ ጀብድ ለመፈጸም መዘጋጀታቸውን አስረድቷል።

ዘጋቢ፦ አዳሙ ሽባባው-ከማይጠብሪ ግንባር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ