
ጋሸና፣ እስታይሽ፣ ቀበሮ ሜዳ፣ ኮን፣ አርቢት፣ አሁንተገኝና ሐሙሲት ከጠላት ፀድተው እንደተያዙ የአማራ ልዩ ኃይል ምክትል አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር ቢሰጥ ጌታሁን ገልጸዋል።
ባሕር ዳር: ነሐሴ13/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ልዩ ኃይል ምክትል አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር ቢሰጥ ጌታሁን እንዳሉት የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ሕዝባዊ ሠራዊት የጋሸናን መስመር ቆርጦ አካባቢውን ተቆጣጥሮታል።
በወሎ ግንባር ለጋዜጠኞች መግላጫ የሠጡት የአማራ ልዩ ኃይል ምክትል አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር ቢሰጥ ጌታሁን የጋሸናን መሥመር ሠራዊቱ ተቆጣጥሮ የጠላትን እንቅስቃሴ ገትቷል ነው ያሉት። ሠራዊቱ በሰሜን ወሎ አራት ወረዳዎችን ተቆጣጥሮ ተጋድሎ እያደረገ ነውም ብለዋል።
ልዩ ኃይሉ ከመከላከያ ሠራዊትና ራሱን ችሎ በሰሜን ወሎና በደቡብ ጎንደር ደጋማ ቦታዎች ውጊያው እየተካሄደ መሆኑንም ገልጸዋል።
ጋሸና፣ እስታይሽ፣ ቀበሮ ሜዳ፣ኮን፣ አርቢት፣ አሁንተገኝና ሐሙሲት ከጠላት ፀድተው ተይዘዋል ብለዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ማኅበረሰቡ ባደረገው ትግል ነው ቦታዎችን የተቆጣጠረው።
ኅብረተሰቡ ለሠራዊቱ ስንቅ በማቀበል፣ በመዋጋትና መረጃ በመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል። የደፈጣ ውጊያ በመውጣት፣ የጠላትን መረጃ በመስጠት እያደረገው ያለው ተጋድሎ ከፍተኛ መሆኑን ነው የገለፁት።
ለጦርነቱ አስተዋጽኦ የሌላቸው ሰዎች ጠላት በዚህ ገባ በዚህ ወጣ እያሉ በውሸት ሕዝብን ከማደናገር እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።
ጠላትን የሚመራ ባንዳ መኖሩንም ተናግረዋል።
ሕዝቡም መሬቱም የእኛ ነው ያሉት ምክትል አዛዡ ማንኛውም ሰው ጠላትን ማጥቃት አለበት ብለዋል።
ሕዝቡ በመዋጋት፣ መረጃ በመስጠት፣ ስንቅ በማቀበልና በሌሎች መስኮች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ጠላትን በአጭር ጊዜ ከክልሉ ነፃ እንደምናደርገው እርግጠኛ ነኝም ብለዋል።
ከሠራዊቱ ጋር እየተዋደቁ ያሉ የአካባቢ መሪዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል።
❝አሁን የገባው ኃይል መውጣት የለበትም። ወደ ሀገሩ ሊመለስ አይገባም። መሬታችን የረገጠ ኃይል በዚያው መቅረት አለበት፤ በቂም በቀል ዘርና ሀብት ለማጥፋት የመጣ ቡድን መውጣት የለበትም። ከተቻለ መያዝ ካልተቻለ ደግሞ መውደም አለበት❞ ብለዋል።
ሁሉም የአማራ ሕዝብ ጠላትን መውጋት እንደሚገባውም አሳስበዋል።
ሠራዊቱ ከውጊያ በላይ ፈታኝ የሆኑ ተፈጥሯዊ ነገሮችን በመቋቋም የተጋረጠውን አደጋ ለመቀልበስ ያለ ረፍት እየሠራ ነው ብለዋል።
ወደ ደቡብ ጎንደር የገባው ኃይል መውጫ መግቢያው እንደተያዘም ገልጸዋል።
አሸባሪው የትህነግ ቡድን ከአማራ ሕዝብ ዘርፎ ሊወጣ የጫነበት በመቶዎች የሚቆጠር ተሽከርካሪ በጋይንት መስመር ይዞ መቆሙንም ጠቁመዋል።
የአማራን ሕዝብ አዋርዶ የሚወጣና የሚቀር ጠላት የለም፤ ሁሉም በየደረሰበት ጠላትን መደምሰስ አለበት ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ