
“በአሸባሪው ትህነግ ላይ ብርቱ ክንዳችንን እናሳርፍበታለን” የአማራ ልዩ ኃይል ተከዜ ብርጌድ
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 06/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ልዩ ኃይል በፍጹም ሀገራዊ ስሜት፣ ጀግንነት፣ ጠላትን በመደምሰስ ወኔና ሞራል ላይ ይገኛል። ልዩ ኃይሉ፣ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከሕዝባዊ ሠራዊት አባላት እና ከሚሊሻ ኃይል ጋር በመሆን በወራሪው እና ሽብርተኛው ትህነግ ላይ የማያዳግም እርምጃ እየወሰደ ነው።
ሻምበል ተሻገር ባዩ የተከዜ ብርጌድ የዘመቻ ኀላፊ ናቸው። የአማራ ልዩ ኃይል የኢትዮጵያን ህልውና ሊያጠፋ የመጣውን ሽብርተኛው ትህነግን ለመደምሰስ በአስተማማኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል። ልዩ ኃይሉ የማሸነፍ ወኔን በመሰነቅ ጠንካራ ወታደራዊ ዝግጅት ማድረጉንም ኀላፊው አስረድተዋል። ጀግናው የአማራ ልዩ ኃይል ከዚህ በፊት ሽብርተኛው ትህነግን አይቀጡ ቅጣት መቅጣቱን እና አሁንም ማድረግ የሚገባውን ለማድረግ አስተማማኝ አቅም አጎልብቶ ይገኛልም ብለዋል።

“ኅብረተሰቡ በምናደርገው ጉዞ ሁሉ ከእኛ ጋር ነው” ያሉት የተከዜ ብርጌድ የዘመቻ ኀላፊው ከሁሉን አቀፍ ድጋፉ ባሻገር ከልዩ ኃይሉ ጋር በግንባር በመሠለፍ አሸባሪውን ቡድን እየተፋለመ መሆኑንም ነግረውናል።
“በፍጹም አስተማማኝ ደጀን ውስጥ ሆነን እናሸንፋለንም” ብለዋል። ለሕዝብ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል። ሻምበል ተሻገር የህልውና ዘመቻው ሕይወት የማስቀጠልና ያለ ማስቀጠል ጉዳይ በመሆኑ ልዩ ኃይሉ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የተሻለ ብቃት እንዲኖረው ተደርጓል ብለዋል። በመሆኑም “ሽብርተኛው ትህነግን ትላንት ደምስሰናል፤ ዛሬም አቅም አለን፤ ነገም ብርቱ ክንዳችንን እናሳርፍበታለን” ሲሉ አረጋግጠዋል።

የተከዜ ብርጌድ ኦርዲናንስ መምሪያ ኅላፊ ዋና ሳጅን ክፍሌ መኮንን ሽብርተኛው ትህነግ ተራ ሽፍታ መሆኑን እና ተደብቆ እንጂ ፊት ለፊት የመዋጋት ብቃትና ሞራልም እንደሌለው ገልጸዋል። “እኛ እያለን ኢትዮጵያ አትደፈርም” ያሉት መምሪያ ኅላፊው ሽብርተኛው ትህነግ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለዓመታት በሃሰት ወሬ ማታለሉን ገልጸዋል፡፡
አሁንም ሕዝቡ ለሚነዛው የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ጆሮ ባለመስጠት የህልውና ዘመቻውን እንዲደግፍ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ደጀናችን ነው፤ ሠራዊትም ነው፤ መሣሪያ አንስቶ ጠላት የሚዋጋ ነው” ሲሉ ለሕዝቡ ያላቸውን ክብር ገልጸዋል።
የተከዜ ብርጌድ ሁለተኛ ሻለቃ ሻምበል ፍታለው ሙሉ በበኩላቸው በጥቅምት ወር በነበረው ውጊያ በአዲአርቃይ እና በማይጠብሪ ግምባር ጁንታውን በአጭር ቀን በመደምሰስ ድል መቀዳጀታቸውን አንስተዋል።

አሸባሪው በዚያን ጊዜ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቷል ያሉት ሻምበል ፍታለው ዛሬ ላይ መሬት ልሶ በመነሳት ደግሞ በአማራ ክልል የተለያዩ ቦታዎች ትንኮሳ እያደረገ ቢሆንም እየተማረከና እየተደመሠሠ መሆኑን ገልጸዋል። “ጁንታው ክንዳችንን ያውቀዋል፤ እንቀብረዋለን” ነው ያሉት ሻምበል ፍታለው፡፡
ዘጋቢ፦ አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ