‹‹የአውደ ውጊያ ውሎ ድል መክተቢያ የወርቅ ብዕራችን እንዳይደርቅ እንፋለማለን›› ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ

278
‹‹የአውደ ውጊያ ውሎ ድል መክተቢያ የወርቅ ብዕራችን እንዳይደርቅ እንፋለማለን›› ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 05/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪውን የትህነግ ቡድን በአጭር ጊዜ ለማጥፋት የተጀመረው ትግል በስኬት እንደሚጠናቀቅ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ፈንታ ማንደፍሮ (ዶክተር ) ገለጹ፡፡
በደቡብ ጎንደር ዞን የዓለም በር ማሰልጠኛ ማዕከል መሰረታዊ ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱ የልዩ ኀይልና ሚሊሻ አባላት የምረቃ ሥነ ሥርዓት ዛሬ ተካሂዷል፡፡
በመርሃ ግብሩ የሥራ መመሪያ የሰጡት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ትህነግን መፋለምና ማሸነፍ የአማራን ሕዝብ ከመጥፋት ኢትዮጵያንም ከመፈራረስ መታደግ እንደኾነ አስገንዝበዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ለሀገር ክብር እስከ ደም ጠብታ የመፋለም ታሪክ እንዳለው በማንሳትም ሀገርን ለማፍረስ የሚደረግ እንቅስቃሴን አጥብቆ ይታገላል ብለዋል፡፡ ለመዝመት የተዘጋጁ ተመራቂዎች በጠላት ኀይል ላይ ድል እንደሚቀዳጁም ተናግረዋል፡፡
አሸባሪውን ትህነግ እንኳን በአደባባይ አማራን እበቀለዋለሁ ብሎ ተነስቶ በድብቅ ባረቀቀው ማኒፌስቶ አማራን ለዓመታት ሲገድል፣ ሲያስር፣ ሲያፈናቅል፣ እንዳይወልድ ሲያመክን፣ ድራማ እየሠራ ሲበድል እንደነበር ዶክተር ፈንታ አንስተዋል፡፡ የማይካድራው ጅምላ የዘር ጭፍጨፋም አሸባሪው ትህነግ እየሞተ እንኳን ለአማራ ሕዝብ ያለውን ጥላቻ ያሳየበት ነው ብለዋል፡፡
በቅርቡ ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ከመንግሥት እንጂ ከአማራ ሕዝብ ጸብ የለኝም የሚል የበዳይ ተካሺ አካሄድም ይህንኑ ለመድገም ያለመ መኾኑን ነው የጠቀሱት፡፡ በእነዚሁ አካባቢዎች ሰዎችን መግደሉ፣ በርካታ የንብረት ውድመት ማድረሱ፣ ተቋማትን መዝረፉና ማፍረሱ፣ የሰዎች መኖሪያ ቤትን ሳይቀር በከባድ መሳሪያ ማፍረሱም የዚህ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ይህ ኀይል ሕዝባዊ ነኝ ማለቱ ከስላቅ እንደማያልፍ ነው የጠቀሱት፡፡
“ለሕዝብ እና ለሀገር፣ ለነጻነትና አንድነት ያለ ስስት የሚሞቱ ኢትዮጵያውያን ልጆች የታሪክ ማኅደራቸው እንዳይታጠፍና የጀግንነት አውደ ውሎ መክተቢያ የወርቅ ብዕራችን እንዳይደርቅ መፋለም ይገባል“ ብለዋል፡፡ ትውልዱ ከአባቶቹ የወረሰውን የሀገር ነጻነት እና የሕዝብ አንድነት የማስከበር ታሪክ እንደማያጓድልም አብራርተዋል፡፡
ለዓመታት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲሠራ የቆየው አሸባሪው የትህነግ ቡድን ሕዝቡን ለመለያዬት ቢሞክርም በረጨው መርዝ ወደ መቃብር እየወረደ ነው ብለዋል፡፡ መላው ኢትዮጵያውያን በአንድነት ዘምተዋልና ድሉ ከሕዝብ ጋር እንደኾነም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleInternational media outlates opened unfair and orchestrated international media attacks on Ethiopia: Ethiopia Current Issues Fact Check
Next articleየአሸባሪው ትህነግ ግፍ በተፈናቃይ ወገኖች አንደበት…