“ሕዝብ በሰላም ወጥቶ በሰላም ይገባ ዘንድ ሠራዊታችን በዱር በገደሉ ለሚያደርገው ተጋድሎ ደም መለገስ ለነገ የማይባል ተግባር ነው” የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች

172
“ሕዝብ በሰላም ወጥቶ በሰላም ይገባ ዘንድ ሠራዊታችን በዱር በገደሉ ለሚያደርገው ተጋድሎ ደም መለገስ ለነገ የማይባል ተግባር ነው” የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በደባርቅ ከተማ በሚል የደም ልገሳ መርኃ ግብር እየተከናወነ ይገኛል፡፡ የደም ልገሳ መርኃግብሩን የሰሜን ጎንደር ዞን ሴቶችና ወጣቶች ሊግ አደረጃጀት ከጎንደር ደም ባንክ ጋር በመተባበር ነው ያዘጋጁት፡፡
የዞኑ ወጣቶች ሊግ ምክትል አስተባባሪ ገብረእግዚአብሔር ሙላው ሠራዊቱ አሸባሪው ትህነግ ለመደምሰስ እያደረገ ያለውን ትግል ማኅበረሰቡ በቁሳቁስ፣ በስንቅና በገንዘብ ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ ደም በመለገስ ደጀን መሆኑን አስቀጥሏል ብለዋል፡፡
የጎንደር ደም ባንክ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደመቀ ጥላሁን አሸባሪው ትህነግ ለመደምሰስ እየተደረገ ባለው የህልውና ዘመቻ በመደገፍ ሁሉም በሚችለው እያገዘ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የጎንደር ደም ባንክ አገልግሎትም ከማኅበረሰቡ ደም የመሰብሰብ ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በዕለቱ ደም የለገሰችው የደባርቅ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ መቅደስ ጌጡ ደም መለገስ የሚችል የኅብረተሰብ ክፍል በህልውና ዘመቻው ከፍተኛ መስዋእትነት እየከፈለ ለሚገኘው የጸጥታ ኃይል ደም መለገስ ይገባል ብለዋል፡፡
የሕዝብን ደኅንነትን ለማስከበር በዱር በገደሉ ተጋድሎ እያደረጉ ለሚገኙ ኀይሎች ደም መለገስ ለነገ የማይባል ተግባር ነው ያሉት ደግሞ በዕለቱ ደም የለገሱት የደባርቅ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ባለሙያ አቶ ሰጠኝ አዳነ ናቸው፡፡
አቶ ሰጠኝ ደም በመለገስ ህይወትን መታደግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በደባርቅ ከተማ ለሁለት ቀን በሚደረገው የደም ልገሳ መርኃ ግብር ከ300 ዩኒት በላይ ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ዘጋቢ፡- አድኖ ማርቆስ-ከደባርቅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየሲዳማ ክልል ሁለተኛ ዙር የልዩ ኃይል አባላትን ለሀገራዊ ጥሪ ሊልክ ተዘጋጅቷል፡፡
Next articleʺአሸባሪውን የትህነግ ቡድን ከምድረ ገፅ ማጥፋት አለብን” ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ