ኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል እና ዓለም አቀፋዊ ድባቡ

802
ኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል እና ዓለም አቀፋዊ ድባቡ
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 13/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም ዙሪያ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ ነው፤ ኢድ አል አድሃ (አረፋ)፡፡ በዓሉ የእርድ ወይም የመስዋእትነት በዓል በመባልም ይታወቃል፡፡ የአሏህ ደግ ሰው ነብዩ ኢብራሂም ከ120 ዓመታት የመካንነት ሕይወት በኋላ በአሏህ ፈቃድ ወንድ ልጅ ተቸራቸው፡፡ ልጃቸው ኢስማኤል ለአባቱ ታዛዥ እንደነበርም ይነገራል፡፡
ነብዩ ኢብራሂም በደስታቸው ማግስት የእምነታቸው ጽናት የሚፈተንበት ወቅት ተፈጠረ፡፡ የሰባት ዓመት አንድያ ልጃቸውን መስዋእት ያደርጉ ዘንድ ከፈጣሪ ታዘዙ፡፡ የልጃቸው ፍቅር ቢያስጨንቃቸውም ትዕዛዙ የፈጣሪያቸው ነውና ሊፈጽሙ ከመካ ወደ አረፋ ተራራ ወጡ፡፡
ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸውን ሊሰው ሲዘጋጁ ከሰማይ በኢስማኤል ምትክ መስዋእት የሚሆን በግ ወረደላቸው፡፡ በዓሉም ኢድ አል አድሃ (አረፋ) እየተባለ በየዓመቱ ይከበራል፡፡
ለመሆኑ የዓለም ሀገራት ይህንን በዓል እንዴት ያከብሩታል? ሕንዳዊያን በሂጅራ የዘመን ቀመር በ12ኛው ወር በ10ኛው ቀን የሚያከብሩትን የኢድ አል አድሃ በዓል “ታላቁ ኢድ” ሲሉ ይጠሩታል፡፡ ኢድ ኩርባን ወይም ኩርባን ባያራሚ ሲሉ እንደሚጠሩትም መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ የነብዩ ኢስማኤልን ለመስዋእትነት መመረጥ እና መታዘዝ ታሳቢ በማድረግም ጠቦት፣ ጥጃ፣ ግመል ወይም ሌሎች ለእርድ የተፈቀዱ እንስሳት በቀኑ ይታረዳሉ፡፡ የታረደው ስጋም ለቤተሰብ፣ ለጓደኛ እና ማረድ ለማይችሉ ወገኖች ለሦስት እኩል ይከፋፈላል፡፡
ሕንዳዊያን በዓሉን ከሃይማኖታዊ ትሩፋቱ ባለፈ የቤተሰባዊ እሴት ማጠናከሪያ እና መሰባሰቢያ በዓል አድርገው ስለሚያዩት በተለያየ ምክንያት ተለያይተው የሚውሉ ቤተሰቦች ይሰባሰቡበታል፡፡
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሀገራት እና ሙስሊሞች በዓሉን የሚያከብሩበት ሂደት ከባሕል እና ከእሴት ልዩነት ጋር በተያያዘ የሚያከብሩበት አውድ ከቦታ ቦታም ይለያያል፡፡
ኢድ አል አድሃ (አረፋ) ከኢድ አልፈጥር በተለየ መልኩ በዓሉ የሚከበርበት ቀን የጨረቃን መታየት መሰረት አያደርግም፡፡ የተባበሩት አረብ ኤምሪትስ ኢድ አል አድሃ (አረፋ)ን ለማክበር ሦስት ተከታታይ ቀናትን ይጠቀማሉ፡፡ ከኢድ አል አድሃ በዓል ቀድማ ያለችዋን ቀን በልዩ ሲያከብሯት ስያሜዋንም “አረፋ” ይሏታል፡፡ ከዋዜማው ቀን ጀምረው “ኢድ ሙባረክ” በመባባል የደስታ መልዕክት ይለዋወጣሉ፡፡
ሕጻናት በበዓል አልባሳት ደምቀው የኢድ ስጦታ ለጎረቤቶቻቸው በማበርከት ያሳልፋሉ፡፡ እናቶች መኖሪያ ቤቶቻቸውን በኢድ አርማ ያሳምራሉ፤ ተወዳጅ እና ጣፋጭ ምግቦች በተለየ ሁኔታ ለቤተሰቡ ይዘጋጃሉ፡፡
በቱርክ በመጀመሪያው የኢድ አል አድሃ ቀን ወንዶች ለተለየ ሃይማኖታዊ ስርዓት ወደ መስጂድ በጠዋት ይሄዳሉ፡፡ አሁን አሁን በቱርክ ለመስዋእት የሚቀርበውን ገንዘብ እና እንስሳ ለበጎ አድራጎት ተቋማት ይሰጣል፡፡ ቱርካዊያን በኢድ አል አድሃ ለበዓሉ በሚመጥን አልባሳት ደምቀው ቤተ ዘመድ ይጎበኛሉ፤ ጥሪ አድርገው በቤታቸው ይጋብዛሉ፤ እንዲሁም የሃብት አቅም ለሌላቸው ወገኖች ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡
ወጣቶች በጎረቤቶቻቸው ቤት በጠዋት እየሄዱ እንኳን አደረሳችሁ በማለት እጆቻቸውን በመሳም ይዘይራሉ፡፡ አንዳንድ ቱርካዊያን ዓመታዊ እረፍታቸውንም በኢድ አል አድሃ አካባቢ ያደርጋሉ፡፡
በሞሮኮ፣ ቱኒዚያ፣ ግብጽ፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ሌሎች በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ኢድ አል አድሃ (አረፋ) በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ይከበራል፡፡ በኢትዮጵያ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በጠዋት በሃይማኖታዊ አልባሳት ደምቀው እና አምረው ወደ አደባባይ እና መስጂድ ያመራሉ፡፡ ሶላት በጋራ አድርገው እና እርስ በእርሳቸው የመልካም ምኞት ተቀያይረው ይለያያሉ፡፡ በመጡበት መንገድ ሳይሆን መንገድ ቀይረው ለፈጣሪ ምስጋና እያቀረቡ ወደቤታቸው ይመለሳሉ፡፡
ከአደባባይ ሶላት በኋላ የእርድ ሥርዓት በየቤታቸው ይኖራል፡፡ ቤተሰብ ተሰብስቦ በጋራ ያከብራል፤ ያለው ለሌለው ያካፍላል፤ እንዲሁም ከጎረቤቶቻቸው ጋር በመጠራራት ይገባበዛሉ፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ ከእርድ ስርዓት ቀደም ተብሎ የሌላ ሃይማኖት ተከታይ ወዳጆች ተጠርተው እና ተጋብዘው “ኢድ ሙባረክ” ብለዋቸው ይወጣሉ፡፡
እኛም ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ለመላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች “ኢድ ሙባረክ” ብለናል! የመረጃ ምንጮች፡- ለንደን ኒውስ ቱደይ እና አልጀዚራ ካልቸር
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleኢብራሂም፡ የነብዩሏህ ልጅ ነውና፤ እስከ መስዋዕትነት ድረስም ታዟልና ለነብይነት ተመረጧል!
Next articleበአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለመተከል ዞን ተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ።