
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዲጂታል እውቀት ግንባታ ላይ በትኩረት እንዲሠሩ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጠየቀ።
ባሕር ዳር: ሐምሌ 09/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ለትምህርት ዘርፉ በሚያደረገው አስተዋጽኦ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ሲካሄድ የቆየውና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያዘጋጀው የፓናል ውይይት ተጠናቅቋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ያኒአ ሰይድመክይ (ዶ.ር) የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት ኢትዮጵያ የያዘችው እቅድ እንዲሳካ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዲጂታል እውቀት ግንባታ ላይ በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ወደ ተግባር የሚለወጠው ዩኒቨርሲቲዎችና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የዲጂታል እውቀትና ክህሎት ላይ ሲሠሩ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርም ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ነው ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲዎችና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የቴክኖሎጂ አፍላቂዎችን በመለየት፣ ሥራዎቻቸው እንዲወጡና ወደ ማኅበረሰቡ እንዲወርዱ ማድረግ ላይ መሥራት ይጠበቅባቸዋልም ነው የተባለው።
በውይይቱ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በትምህርት ዘርፍ፣ የዲጂታል ክህሎት ፍኖተ ካርታ አተገባበር፣ መጻኢ ቴክኖሎጂዎች በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ያላቸው ፋይዳ እና ሌሎችም ጉዳዮች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በዘርፉ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ክለሳ፣ የኢኖቬሽን ፈንድ አዋጅ፣ የትራንዛክሽን አዋጅ፣ የዲጂታል ክፍያና የመሳሰሉትን ማሻሻያዎችን እያደረገ ይገኛል ተብሏል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ