
ከ15 በላይ ሊቀጳጳሳትንና በርካታ ሊቃውንትን ያፈሩት መምህር አክሊለ ብርሃን ኃይለሥላሴ ከዚህ ዓለም ድካም አረፉ፡፡
ባሕር ዳር: ሐምሌ 03/2013 ዓ.ም (አሚኮ) መምህር አክሊለብርሃን ከእናታቸው ከወለተሩፋኤል ዘርፉ እና ከአባታቸው ከመምህር ኃይለሥላሴ ዘነበ በተንቤን ዐቢይ አዲ አውራጃ በእንዳ እጨጌ በአፄ እያሱ አድያም ሰገድ ኪዳነ ምህረት ገዳም አካባቢ ነሐሴ 22 /1926 ዓ.ም ተወለዱ፡፡
መምህር አክሊለብርሃን እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በእንዳ እጨጌ የንባብ መምህር ከነበሩት መምህር አባ ገብረማርያም ትምህርት ጀመሩ፡፡ መምህር አክሊለብርሃን ከመምህር ገብረማርያም ንባብ፣ ዳዊት፣ ውዳሴ ማርያም እና አንቀጸብርሃን፣ መልክዓማርያም እና መልካ ኢየሱስን ተምረዋል፡፡ መምህር አከሊለብርሃን በልጅነት ዘመናቸው ከአካባቢያቸው በመራቅ ወደ ቆላ ተንቤን ወርቅአምባ ሚካኤል ወርደው የቅዳሴ፣ የጾመ ድጓ እና የአቡሻሕር ሊቅ ከነበሩት ከመርጌታ አብርሃ በመሄድ ከውዳሴ ማርያም ዜማ እስከ ክስተት እንዲሁም ከጾመድጓ እስከ ኒቆዲሞስ ተምረዋል፡፡

መምህር አክሊለብርሃን በ1949 ዓ.ም ቅኔ ለመማር ወደ ሰሜን ጎንደር አቅንተው ደምቢያ ጉንትር በዓለእግዚአብሔር ከመሪጌታ መንግሥቱ ቅኔ ተቀኝተዋል፡፡ ወደ ጭልጋ አቅንተውም ከየኔታ አክሊሉ ቅኔን አደላድለዋል፡፡
መምህር አክሊለብርሃን አንገረሚካኤል ከመሪጌታ ዘካሪያስ አቋቋም ለ6ወር ያክል ክብረበዓል ተምረዋል፡፡ በ1951 ዓ.ም ከመምህር ክፍሌ ይመር የሐዲሳት ትምህርታቸውን አስኪደው የማቲዎስ ወንጌልን አጠናቀቁ፡፡
መምህር አክሊለብርሃን ዲቁናን በ1938 ዓ.ም፣ ቅስናን በ1941 ዓም ከዓድዋ አዲ አቡሃ ተክለ ሃይማኖት ከአስመራው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ተቀብለዋል፡፡ ምንኩስና በገዳመ ዋልድባ በ15 ዓመታቸው አግኝተዋል፡፡
ቁምስናን በ1974 ዓ.ም በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ከአቡነ መቃሪዎስ ተቀብለዋል፡፡
መምህር አክሊለብርሃን ለ23 ዓመታት ተዘዋውረው ዕውቀትን ቀስመዋል፡፡ ከ1951 ዓም እስከ 1974 ዓ.ም ጎንደር ደብረብርሃን ሥላሴ ወንበር ተክለው አስተምረዋል፡፡

የአብነት ትምህርቱን ሳያስተጓጉሉ በጎንደር ተናኘ ወርቅ ትምህርት ቤት በግብረገብ መምህርነት ለ18 ዓመታት አገልግለዋል፡፡
መምህር አክሊለብርሃን በተናኘወርቅ ትምህርት ቤት እና የደብረ ብርሃን ሥላሴ የነበራቸውን ወንበር በፈቃዳቸው ለቀው በ1974 ዓ.ም ክቡራን ገብርኤል ገዳም በመግባት መናንያንን አስተምረዋል፡፡ ገዳሙንም በአበምኔትነት እና በልዩ ልዩ ሥራዎች አገልግለዋል፡፡
መምህር አክሊለብርሃን በ1979 ዓ.ም በምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ መቃሪዎስ ፈቃድ የሀገረ ስብከቱ የአብነት መምህር በመሆን ተቀጥረው በጽርሐ አርያም ደብረ ሲና በዓታ ለማርያም የቅዳሴ ጉባኤ ቤት ጀምረው ለ34 ዓመታት አስተምረዋል፡፡
ጉባኤ ቤታቸው በአሁኑ ወቅት 30 የተማሪ ጎጆዎች እና ከመቶ በላይ ደቀ መዛሙርት ነበሯቸው፡፡ መምህር አክሊለብርሃን በደብረ ዓባይ ለ6 ዓመታት፣ በጎንደር ደብረ ብርሃን ሥላሴ ለ23 ዓመታት በክብራን ገብርኤል ለ5 ዓመታት እንዲሁም በደብረሲና በዓታ ለማርያም ገዳም ለ34 ዓመታት በአጠቃላይ ለ68 ዓመታት በአብነት መምህርነት አገልግለዋል፡፡ አሁን ላይ በዓታቸው እንዳይዘጋ ያስተማሯቸውን ደቀመዝሙር በባሕር ዳር ሀገረስብከት ሊቀጳጳስ በአቡነ አብርሃም መልካም ፈቃድ ወንበሩን እንዲረከቡ አድርገዋል፡፡
መምህር አክሊለብርሃን በመምህርነት ዘመናቸው ከ15 በላይ ሊቀጳጳሳትን አፍርተዋል፡፡ ያስተማሯቸው መምህራንም በተለያዩ አህጉረ ስብከቶች እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
መምህር አክሊለ ብርሃን ለክቡራን ገብርኤል ሁለት የብራና መጻሕፍትን፣ ለደብረሲና በዓታ ለማርያም ገዳም አምስት መጻሕፍትን፣ ለክርስቶስ ሠመራና ለሰልቸን ቅዱስ ሚካኤል መጻሕፍትን አበርክተዋል፡፡
ለሰልቸን ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የአስተዳዳሪ መኖሪያ ቤት ሠርተዋል፡፡ በጎንደር ደብረብርሃን ሥላሴ ቤተ-ክርስቲያን ህንጻ ገንብተው አስረክበዋል፡፡
መምህር አክሊለብርሃን በእርጅና ዘመናቸው ባደረባቸው ህመም ለተወሰኑ ወራት በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ87 ዓመታቸው ሐምሌ 2 /2013 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል፡፡ ሥርዓተ ቀብራቸው በባሕር ዳር ሀገረ ሥብከት ደብረሲና በዓታ ለማርያም ገዳም የባሕር ዳር ሀገረሥብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አብርሃምን ጨምሮ ብፁዓን አበው ሊቀ ጳጳሳት የገዳማት እና የአድባራት አስተዳዳሪዎች ልዩ ልዩ የመንግሥት ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ተፈጽሟል፡፡
በትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ