
የኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ተግባር መሆኑን የተለያዩ አገሮች ወታደራዊ አታሼዎች
ገለጹ።
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሠላም ማስከበር ተልዕኮ
ውስጥ የምታደርገው ተሳትፎ የሚደነቅና ሊቀጥል የሚገባው ተግባር መሆኑን የተለያዩ ሀገሮች ወታደራዊ አታሼዎች ገለጹ።
መቀመጫቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉ የተለያዩ አገሮች ወታደራዊ አታሼዎች ማህበር አባላት ዛሬ የመከላከያ የሠላም ማስከበር
ሥልጠና ማዕከልን በጎብኝተዋል።
በወቅቱ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሦስት ሀገሮች ወታደራዊ አታሼዎች እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሠላም ለማስፈን
እያደረገች ያለው ተሳትፎ የሚደነቅ ነው።
“ኢትዮጵያ እ.አ.አ ከ1950ዎቹ ከኮሪያ የሠላም ማስከበር ተሳትፎ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለዓለም የጋራ ሠላም የበኩሏን
አስተዋጽኦ አድርጋለች” ብለዋል።
የተመድ የሠላም ማስከበር ተልዕኮ የሚያበረታታውን የሴቶች ተሳትፎ ኢትዮጵያ በተግባር ማሳየቷንም ገልጸዋል።
ይህንንም ኢትዮጵያ ከሌሎች ተሳታፊ አገሮች ጋር በትብብር መንፈስ ማከናወኗን የገለጹት ወታደራዊ አታሼዎቹ፤ ተሳትፎዋን
አጠናክራ ልትቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የዛምቢያ ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ብርጋዴር ጄኔራል ሙሶንዳ ሴንጋ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ለዓለም ሠላም ብዙ
መስዋዕትነት የከፈለች አገር ናት።
“በርካታ ሠራዊቷን ለዓለም እንዲሁም ለአፍሪካ ሠላም ስትል ገብራለች” ያሉት ጄኔራሉ፤ “ለሠላም በተደረገ ተጋድሎ ኢትዮጵያ
ሴት የሠራዊት አባላትን ጭምር አሰልፋለች” ብለዋል።
ይህም የተመድ በሠላም ማስከበር ተልዕኮ የሴቶች ተሳትፎ 30 በመቶ ይሁን ከሚለው የመርህ ውሳኔ ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑን
ነው ያረጋገጡት።
ኢትዮጵያ በዓለም የሠላም ማስከበር ተልዕኮ እያደረገች ያለውን ተሳትፎ ይበልጥ አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የኮንጎ ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ኮሎኔል ሊዊስ ሮላንድ በበኩላቸው “የኢትዮጵያ የሠላም ማስከበር ተሳትፎ የረጅም
ዓመት ልምድ ያለው ነው” ብለዋል።
በሰላም ማስከበር ተሳትፎዋ ኢትዮጵያ በፍሪካ ቀዳሚ አገር መሆኗን የሚበረታታ እንደሆነም ጠቁመዋል።
የመከላከያ የሰላም ማስከበር ሥልጠና ማዕከል አገሪቱ በሠላም ማስከበር እያደረገች ያለው ተሳትፎ ለማሻሻል የሚያደርገውን
የአቅም ግንባታ ሥራ አድንቀዋል።
በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ግሩፕ ካፒቴን አንድሪው ጊልበርትም በተመሳሳይ ኢትዮጵያ በሰላም
ማስከበር ያላትን ተሳትፎ አሞካሽተዋል።
የሀገራቸው ሠራዊት በተመድ የአፍሪካ ሠላም ማስከበር ተልዕኮ ሥር ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር አብሮ መሥራቱን ጠቁመው፤
አጋርነቱ እንደሚቀጥልና በሰላም ማስከበር ተልዕኮ አቅም ግንባታ ሥልጠና ረገድ በትብብር ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው
ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት አፍሪካ ውስጥ ተመድ ባለው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ኢትዮጵያ በአራት ሥፍራዎች ተሳታፊ ሆናለች።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m